Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Saturday, July 19, 2014

ድምፃችን ይሰማ እገታውና አፈሳው አሁንም ቀጥሏል! ህገ ወጥ እርምጃ እልኽና ቁጭትን እንጂ መፍትሄን አይወልድም!

ድምፃችን ይሰማ
‪#‎ExemplarySolidarity‬ ‪#‎JumaDemonstration‬
እገታውና አፈሳው አሁንም ቀጥሏል!
ህገ ወጥ እርምጃ እልኽና ቁጭትን እንጂ መፍትሄን አይወልድም!
አርብ ሐምሌ 11/2006
የመንግስት ወታደሮች ሰላማዊው ህዝበ ሙስሊም ላይ ጭካኔ የታከለበት ጥቃት ከፈፀሙ በኋላ በአንዋር መስጊድ ቅጥር ግቢ ውስጥ ያገቱትን ሰው ወደተለያዩ ማጎሪያ ካምፖች ማጋዛቸውን በምሽቱም ቀጥለዋል፡፡ እስካሁን አፍነው የወሰዷቸውን ሙስሊሞች በጨው በረንዳ፣ በጅንአድ፣ በአራተኛ ፖሊስ ጣቢያ፣ በኮልፌ 18 ማዞሪያ እና በሌሎችም ቦታዎች ወስደው እያንገላቱ ይገኛሉ፡፡ በማጎሪያ ካምፕ ያሉትንም አንድ ዳቦ እና ውሃ ብቻ በመስጠት ስፖርት በማሰራትና በመደብደብ ላይ እንደሚገኙ ምንጮች ጠቁመዋል፡፡
ወታደሮች ጾማቸውን እንኳ እንዲያፈጥሩ እድል ያልሰጧቸውን ሙስሊሞች በመኪና ጭነው ሲያልፉ አላፊ አግዳሚው ሰው ማፍጠሪያ ተምር እና ብስኩት ሲወረውርላቸው መመልከት በእጅግም የመንግስትን ጭካኔ እና የህዝቡን ተምሳሌታዊ አብሮነት አቃርኖ ለማነጻጸር የሚያስችል አስገራሚ ክስተት ነው፡፡ የመንግስትን ኢ-ሰብአዊነት በራሱ ሰብዓዊነት እያበሰ ያለው ህዝበ ሙስሊም በእርግጥም ታላቅ ክብር ይገባዋል!
እስካሁን የህዝቡን ስቃይ ከምንም ያልቆጠሩት ፖሊሶች በመስጂዱ የተያዙትን ሴቶች ‹‹እናስፈታለን›› እያሉ ከቤተሰቦች 2 ሺህ ብር እና ከዚያም በላይ ጉቦ በመጠየቅ ላይ መሆናቸው በእርግጥም መንግስታዊ ስርአቱ የደረሰበትን የዝቅጠት ደረጃ የሚያመለክት ነው፡፡ አንዳችም ወንጀል ያልሰራን ህዝብ ከበው፣ ደብድበውና አስረው ‹‹እንድንፈታ ገንዘብ ስጡን›› ማለታቸው ‹‹እንጥፍጣፊ የሚሞላ ኢትዮጵያዊ ርህራሄ የላቸውምን?›› ያስብላል፡፡
በዚህ ሁሉ በደል መሃል ደግሞ ኢቲቪ በዜናው ‹‹በዒድ ሰላት ላይ የተነሳ ሁከት በቁጥጥር ስር አውያለሁ›› የሚል ዜና ማሰማቱ ሺዎችን አስገርሟል፤ አሳዝኗልም፡፡ ያለፈውን ዓመት የፕሮፓጋንዳ ዜና እየደገሙ እያነበቡ የሚመስሉት የኢቲቪ ሐሰተኛ ጋዜጠኞች ህዝበ ሙስሊሙን ከነጭራሹ የማያውቁት ይመስላሉ፡፡ ረመዳን ባለተጠናቀቀበት ወቅት ‹‹በዒድ ሰላት ላይ ረብሻ ያስነሱ ሰዎችን በህዝበ ሙስሊሙ ድጋፍ በቁጥጥር ስር አውያለሁ›› ማለታቸው በደበደቡት ህዝበ ሙስሊም ላይ ንቀት የተሞላበት ሹፈት መሆኑ ሳያንስ የቅጥፈት በሬ ወለደ ዜናዎቻቸውን በምን መልኩ እየሰሩ እነደሆነም የሚያሳብቅ ክስተት ነው፡፡ በተዛዋሪ ‹‹እንደበድብህ ዘንድ ስላገዝከን እናመሰግናለን›› እያሉ ላሾፉበትም በፍትህ ፊት የሚቀርቡበት ጊዜ ሩቅ አይደለም!
አንድ ነገር ግልጽ ነው! ሰላማዊ ዜጎች ሕገ መንግስታዊ መብታቸው ይከበር ዘንድ በሰላማዊ መንገድ የሚያሰሙትን ድምፅ ኹከትና ብጥብጥ በመፍጠር በኃይል ለማኮላሸት የሚደረገው ህገ ወጥ እርምጃ እልኽና ቁጭትን እንጂ መፍትሄን እንደማይወልድ በተደጋጋሚ የተስተዋለ ጉዳይ ነው፡፡ ሰላማዊ ዜጎች ለሚያነሱት አግባብ ያለው ሮሮ ምላሽ ለመስጠት ብቸኛና አዋጭ የመግባቢያ ቋንቋ ዜጎችን ቀርቦ በመግባባት መንፈስ ውይይት ማድረግ እንጂ ብረት እና ዱላ ሊሆን አይችልም፡፡
ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ላነሱት ሃይማኖታዊ የመብት ጥያቄ እየተሰጣቸው ያለው ምላሽ ማን አለብኝነትና አጉል ጀብደኝነት የተጠናወተው ቢሆንም ይህንኑ ተቋቁመው ዓለም አቀፋዊ ተምሳሌትነት የተጎናፀፈውንና ፍፁም ሰላማዊ መርህ የተከተለ ተቃውሟቸውን መቀጠልን ብቸኛ አማራጫቸው አድርገው እነሆ ዛሬም በተቃውሞ አደባባይ ላይ ይገኛሉ! ታሪክ የተበዳዩን ህዝብ ትግል፣ የበዳዩንም በደል ይመዘግባል! ሩቅ ያልሆነው ድልም ይመጣል! አላህም ከበደለኞች ስራ ዘንጊ አይደለም!
መላ የአገራችን ህዝቦችና የመገናኛ ብዙሃን ሆይ!
እኛ ኢትዮጵያዊያን ሙስሊሞች ሦስት ዓመት ሊሞላው የተቃረበውን ሰላማዊ ትግላችንን በቅርብ ሆናችሁ በመከታተል ስታደርጉት ለቆያችሁት ሁለንተናዊ ድጋፍ የላቀ ምስጋናችን ይድረሳችሁ እያልን መንግስት ዛሬም ካለፈው ስህተቱ ሳይማር በንፁሃን ወገኖቻችሁ ላይ የሚወስደውን ኃላፊነት የጎደለው እርምጃ በፅኑ እንድታወግዙና የመገናኛ ሚዲያዎችም የህዝቡን ድምጽ ታሰሙ ዘንድ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን!
ትግላችን በአላህ ፈቃድ እስከ ድል ደጃፎች ድረስ ይቀጥላል!
ድምጻችን ይሰማ!
አላሁ አክበር!

No comments:

Post a Comment

wanted officials