- ከሚመስሏት አገሮች ዝቅተኛ ተወዳዳሪነት አላት
- መንግሥት የገንዘብ ምንዛሪ ተመን አላስተካክልም አለ
- መንግሥት የገንዘብ ምንዛሪ ተመን አላስተካክልም አለ
የዓለም ባንክ ለሦስተኛ ጊዜ ባካሄደው የቅርብ ጊዜ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ጥናት፣ ኢትዮጵያ በአሥር ዓመት ውስጥ አስከፊ የተባለውን የወጪ ንግድ አፈጻጸም ማስመዝገቧን አመለከተ። መንግሥት የኤክስፖርት ዘርፍ መዳከሙን አምኗል።
በባንኩ ዋና ኢኮኖሚስትና የፕሮግራም መሪ የሆኑት ዶ/ር ላርስ ክርስቲያን ሞለር፣ «ባለፉት 18 ወራት በተለይ አገሪቱ እያሽቆለቆለ የመጣ የወጪ ንግድ ውጤት አስመዝግባለች» ብለዋል። ቀድሞውንም ለውድድር ተጋላጭ በሆኑ የግብርና ውጤቶች ላይ የተመሠረተው የአገሪቱ ኤክስፖርት ዘርፍ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በዓለም ላይ በታየው የሸቀጦች ዋጋ መቀነስ የተነሳ፣ አጣብቂኝ ውስጥ በመግባቱ ነው አስከፊ የተባለውን አፈጻጸም ያስመዘገበው። ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ ያሳየው ለውጥ ከሁለት እስከ ሦስት ከመቶ ዝቅ ያለ መሆኑን፣ ዓምና ጭራሽ ከዜሮ በታች አሽቆልቁሎ እንደነበርም ባንኩ አስታውሷል።
87 በመቶ የሚደርሱት ጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ከአነስተኛ ገንዘብ አቅራቢዎች የብድር አቅርቦት እንደሚያገኙ፣ ከ94 በመቶ በላይ የሚሆኑት ትልልቅ ድርጅቶች ደግሞ ባንኮች ፋይናንስ እንደሚያደርጓቸው የባንኩ ጥናት ያመለክታል። በሁለቱ መካከል የሚገኙት አነስተኛና መካከለኛ ድርጅርቶች ግን ብድር እያገኙ እንዳልሆነ ተጠቁሟል። መሀል ላይ የተረሱ ወይም «ዘ ሚሲንግ ሚድል» በሚል በባንኩ የተገለጹት ድርጅቶች ከባንክ የሚያገኙት ፋይናንስ ስድስት በመቶ ብቻ መሆኑን፣ ከአነስተኛ የገንዘብ ድርጅቶች ብድር የሚያገኙ ጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ደግሞ 11 ከመቶ ናቸው። ይህ በመሆኑም አነስተኛና መካከለኛ ድርጅቶች ወደላይ እንዳያድጉና ኤክስፖርት ዘርፍ ላይ እንዳይሳተፉ ችግር ሆኖባቸዋል ተብሏል።
«ተወዳዳሪነትን በማሻሻል የኤክስፖርት አፈጻጸምን ማጠናከር» የሚል ርዕስ የተሰጠው የባንኩ ጥናት ይፋ የተደረገው ሐምሌ 15 ቀን 2006 ዓ.ም. በሸራተን አዲስ ነበር። ላለፉት ዘጠኝ ወራት ሲጠናቀር የቆየው የባንኩ ኢኮኖሚክ ሪፖርት፣ አገሪቱ ያላት የኤክስፖርት ዘርፍ በጣም ዝቅተኛ በመሆኑ ምክንያት ለመዋቅራዊ ለውጥ አስተዋጽኦ ማድረግ እንዳልቻለና በአንፃሩ በምሥራቅ እስያ ላሉት አገሮች የአምራች ኢንዱስትሪው የኤክስፖርት ዕድገት መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት መቻሉን ያስገነዝባል።
«የአገሪቱ የሸቀጥ ምርቶች በፋብሪካ ሳይቀነባበሩ ለውጭ ገበያ ይቀርባሉ» ያለው ባንኩ፣ በዚህ የተነሳም ከጥራትና ከምርት ውስብስብነት ይልቅ ዘርፉ በዋጋ ላይ ጥገኛ እንዲሆን እንዳስገደደውም ገልጿል። «ለአብነት ለውጭ የምታቀርበው ቡና በፀሐይ ከሚደርቅ ይልቅ በውኃ ታጥቦ የሚደርቅ በመሆኑ በዓለም ገበያ ታገኝ የነበረውን ጥቅም እያሳጣት ይገኛል» ያሉት ዶ/ር ሞለር፣ የተቆላ ቡና ለውጭ ገበያ ማቅረብ ቢቻል ደግሞ 200 ፐርሰንት የዋጋ ጭማሪ ሊገኝ ይችል እንደነበርም ይፋ አድርገዋል። የአበባ ዘርፍ ከፍተኛ ጥራት ባላቸው ማሸጊያዎች ቢጠቀም ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ማግኘት የሚችልበት ዕድል እንዳለው ሲገለጽ፣ ቆዳ በእጅ ከሚለፋ ይልቅ በማሽን እንዲለፋ ቢደረግ ከ20 እስከ 30 በመቶ የዋጋ ጭማሪ ያስገኝ ነበር ተብሏል።
በባንኩ ጥናት መሠረት በኢትዮጵያ ኤክስፖርት የሚያደርጉ ድርጅቶች ብዛት 1,825 ነው። ከዚህ ባሻገር ወደ ኤክስፖርት ዘርፉ የሚገቡ ድርጅቶች ጋሬጣ የሚበዛባቸው በመሆኑ፣ ዘርፉ በፍጥነት እንዳይለወጥ ምክንያት መሆኑን ባንኩ በጥናቱ አስታውቋል። «አነስተኛ ድርጅቶች በቂ የፋይናንስ አቅርቦት ሊያገኙ አለመቻላቸው አንዱ ጋሬጣ ነው» ያሉት ዶ/ር ሞለር፣ ከነባር ድርጅቶች ይልቅ ከታች በፍጥነት እያደጉ የሚመጡ ድርጅቶች ዕድሉን ቢያገኙ፣ አዳዲስ የሥራ ዕድል በመፍጠር ረገድ የተሻሉ ይሆኑ እንደነበርም አስታውቀዋል። ባንኩ የንግድ ሎጂስቲክስ ትልቁ ችግር ሆኖ መቀጠሉን ሲያትት፣ በአሁኑ ጊዜ ከጂቡቲ ወደብ ወደ መሀል አገር ዕቃዎችን ለማጓጓዝ ከ40 ቀናት በላይ እየወሰደ እንደሚገኝና የንግድ ተወዳዳሪነትም በዚህ ችግር ምክንያት አረንቋ ውስጥ መግባቱን አስፍሯል። ባንኩ ከለያቸው ችግሮች ውስጥ የፋይናንስ አቅርቦት፣ መሬት፣ የኤሌክትሪክ ኃይል፣ የንግድ ቁጥጥርና ታክስ ዋና ዋና የሚባሉት መሆናቸውን አመልክቷል።
የኤክስፖርት ዘርፉን ለማሻሻል መንግሥት ከትክክለኛው ዋጋው በላይ የሆነውን የምንዛሪ ተመን እንዲያስተካክል ባንኩ ጥሪ አቅርቧል። መንግሥት ለዚህ ጥሪ ምላሹ አጭር ነበር። የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር ዴኤታው አቶ አህመድ ሺዴ እንደተናገሩት፣ መንግሥት የዋጋ ግሽበትና የአገሪቱ ዕዳን ስለሚያባብስበት የገንዘብ ምንዛሪ ተመንን ለገበያ ክፍት እንደማያደርግ አስታውቀዋል። ባንኩ በሚያቀርበው መከራከሪያ መሠረት ኢትዮጵያ ያለባትን የውጭ ምንዛሪ ችግር ለመፍታትና በኤክስፖርት ገበያው ተወዳዳሪ ለመሆን፣ ምርቶቿን በርካሽ ለመሸጥ የብርን የመግዛት አቅም ከሌሎች መገበያያ ገንዘቦች አኳያ ዝቅ እንዲል ማድረግ ይጠበቅባታል።
ይህም ማለት አንድ ዶላር ለማግኘት አሁን ከሚከፈለው ሃያ ብር ይልቅ ይበልጥ እንዲሆን ማድረግ ማለት ነው። ለአብነት አንድ ዶላር ለማግኘት የሚወጣውን ሃያ ብር ወደ 30 ብር ከፍ እንዲል በማድረግ የኤክስፖርት ሸቀጦችን በርካሽ ዋጋ አብዝቶ ለመሸጥ ያስችላል። በሌላ በኩል እንዲህ ያለው የምንዛሪ ለውጥ የገቢ ንግድን ውድ ከማድረጉም በላይ በዋጋ ግሽበት ላይ የሚያደርሰው ተፅዕኖ ቀላል ባለመሆኑ፣ መንግሥት ይህንን በመፍራት ከኤክስፖርት ይልቅ በማክሮ ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖዎች ላይ ማተኮርን እንደመረጠ ሚኒስትር ዴኤታው አስታውቀዋል። ሪፖርቱ ይፋ ሲደረግ የተገኙ የመንግሥት አካላት፣ ባለሙያዎችና ሌሎች ተሳታፈዎች ባንኩን የሚሞግቱ ጥያቄዎችን አቅርበዋል።
የኤክስፖርት ዘርፍ ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት አኳያ የሚያደርገው አስተዋጽኦ 14 በመቶ ሲሆን፣ ይጠበቅ የነበረው ግን 24 በመቶ ነበር። ምንም እንኳ ባንኩ የኤክስፖርት ዘርፉ ከዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አኳያ ያለውን አፈጻጸም የመዳሰስ ዳራ ባይኖረውም፣ አገሪቱ ባለፉት ሦስት ዓመታት ያሳየችው ዝቅተኛ አፈጻጸም፣ በአሥር ዓመት ውስጥ ከታየው ይልቅ ዝቅተኛው ነው ተብሏል። መንግሥት በዚህ ዓመት ከአምስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ከወጪ ንግድ ይጠብቅ የነበረ ቢሆንም፣ በአሥር ወራት ውስጥ የተገኘው ግን ከ2.6 ቢሊዮን ዶላር አልዘለለም። ይህም ቢሆን ግን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከአገሪቱ የኤክስፖርት መጠን ውስጥ አንድ ሦስተኛውን አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ የዓለም ባንክ አስታውቋል።
በዚህ መደሰታቸውን የገለጹት የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማርያም፣ የአየር መንገዱ አስተዋጽኦ በአግባቡ ሲታይ እንዳልቆየና ምሥጋና እንደማይቸረው ተናግረዋል። የዓለም ባንክ ይፋ ያደረገውን ጥናት ተከትሎ በርካታ ጥያቄዎችና ክርክሮች ተደምጠዋል።
No comments:
Post a Comment