ለሌባ ባለሥልጣናት መጦሪያ ቤት?
ለ6 ጡረተኛ የኢህአዴግ ባለስልጣናት የ154 ሚሊዮን ብር ተዘጋጅቶዋል
ለ6 ጡረተኛ የኢህአዴግ ባለስልጣናት የ154 ሚሊዮን ብር ተዘጋጅቶዋል
በ1967 የወሎ ሕዝብ በድርቅ ሲረግፍ ንጉሱ ለልደታቸው ከእንግሊዝ አገር በመጣ ኬክና ከእስኮትላንድ በተጫነ ውስኪ ይራጩ ነበር የሚል ዜና ደርግ ሲያስነግር አገሪቷ በሰላማዊ ሰልፍ ቀውጢ ሆነች። ይህም የቀዳማዊ ኃይለስላሴን አገዛዝ ለመገርሰስ ግብዓት ሆነ።
በ1977 የትግራይና የወሎ ሕዝብ በረሃብ ሲረግፍ ደርግ አስረኛ የልደት በአሉን ለማክበር ከኮሪያ ባስመጣው ርችት ታጅቦና አገሪቷን በቀለም አዥጎርጉሮ ያረግዳል የሚል ዜና ሲያስተጋባ ምእራባውያን ለሕወሃት/ኢህአዴግ ከፍተኛ እርዳታና ይሁንታ ሰጡ። ይህም ለደርግ መውደቅ የራሱን አስተዋጽኦ አበረከተ።
በ2008 ድርቅ አስር ሚሊዮን የሚሆን ወገናችንን ሲያጠቃ ኢህአዴግ ሰፋ ብላ የድርጅቶቿን ልደት በሚሊዮን በሚቆጠር ብር እያከበረች ነው።
ይህ ሁሉ ወገን በሚራብበትና በሚቸገርበት አገር ውስጥ ከሰሞኑ የተነገረው ዜና ደግሞ ጆሮ ጭው ያደርጋል።
“ጡረታ ለሚወጡ ስድስት ከፍተኛ የኢህአዴግ ባለስልጣናት በመቶ ሃምሳ አራት ሚሊዮን ብር (እያንዳንዳቸው ከ25 ሚሊዮን ብር በላይ) መጦሪያ ቤቶች ተገንብተው እየተጠናቀቁ ነው” የሚል ዜና ተነገረ።
እነዚህ ቤቶች ለባለስልጣኖቹ በስጦታ መልክ የሚተላለፉት ሲሆኑ ሊሸጡት ወይም ሊለውጡት ይችላሉ ተብሏል።
ሃላፊው አቶ ተክለጻዲቅ ተክለአረጋይ (አቡነአረጋይ) ለሸገር ሬድዮ እንደተናገሩት አገራችን እነዚህን ቤቶች ለባለስልጣኖች መገንባቷ ከአፍሪካ አንደኛ ያደርጋታል ብለዋል። የመዋኛ ገንዳ (ስዊሚንግ ፑል) ያላቸው እነዚህ ቅንጡ ቤቶች የሚገነባላቸው ባለስልጣኖች ተለይተው መታወቃቸውን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ከጠቅላላ ሕዝቦቿ ውስጥ ከ2 ፐርሰንት በታች ለሆኑ አዛውንት ሕዝቦቿ የጡረታና የማህበራዊ ዋስትና የሌላት አገር ብትሆንም በስልጣን ዘመናቸው በሚሊዮን የሚቆጠር ብር ለዘረፉ ሌባ ባለስልጣኖቿ ግን ቅንጡ መጦሪያ ቤት የምትገነባ አገር ሆናለች።
አንድ ቤት በ25 ሚሊዮን ብር ተገንብቶ በስጦታ ሲታደል ሕዝቡ ተጠይቋል?
የዜጎችን ኑሮ ትርጉም ባለው መልኩ ለውጠው ቢሆን ኖሮ መጦሪያ ቤት መውሰዳቸው አያስፈርድባቸውም ነበር።
ሆኖም ግን እውነታው:-
* ጧሪ ቀባሪ ያጡ ሽማግሌዎች በየመንገዱ ወድቀው በሚለምኑበት አገር
* መንግስት አንድ መጠለያ ጣቢያ ሰርቶ አዛውንቶችን በማይጦርበት አገር
* በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች እየተራቡ ባለበት አገር
* በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ተበድረው ኮንዶሚኒየም ለመግዛት ለአመታት ሰልፍ በሚጠብቁበት አገር
* ወጣቶች በጅምላ አገራቸውን ትተው በሚሰደዱበት አገር
* በድህነቷ የአለም አገሮች ውራ በሆነች አገር
ሰርቀው የሰሩትን ቤት በሚሊዮኖች ለሚያከራዩ ሞሳኝ ባለስልጣኖች ከዜጎች ጎሮሮ ላይ ነጥቆ የተንጣለለ መጦሪያ መገንባት ምን ማለት ይሆን?
በርካታ ገንዘብ ሰርቀው ላልጠረቁ ባለስልጣናት ተጨማሪ ቤት ማደል ምን ያህል ነውር መሆኑን ያውቁት ይሆን?
ከመንግስት ባለስልጣናት እጃቸው በሙስና ያልተጨማለቁ ካሉ ቢሰጣቸው አይከፋም ነበር።
ሆኖም ግን እውነታውን እነሱም ያውቁታል፤ እኛም እናውቀዋለን።
(ጽሁፉ ከነፎቶው ከYona Bir ፌስቡክ የተወሰደ)
*********************************
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ፡፡ ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው፡፡
*********************************
“ጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ የሕዝብ” እንደመሆኑ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ ሥር የድርጅቶችና የማንኛውም ግለሰብ ነጻ ሃሳብ የሚስተናገድ ሲሆን ከአንባቢያን የሚላኩልን ጽሁፎች በጋዜጣው የአርትዖት (ኤዲቶሪያል) መመሪያ መሠረት ያለ መድልዖ በዚህ ዓምድ ሥር ይታተማሉ፡፡ ይህ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በ“የኔ ሃሳብ (Opinion)” ዓምድ የታተመ ጽሁፍ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® አቋም ሳይሆን የጸሃፊው ነው፡፡
No comments:
Post a Comment