አባ ማቲያስ - በሃይማኖት ዲፕሎማሲ የለም!
-------------------
ዘንድሮ መቼስ የማይሰማ ጉድ የለም:: ከአስር ሚሊዮን የሚበልጥ ሕዝብ በረሃብ ምክንያት በሞት አፋፍ ላይ ሆኖ እርዳታ በሚጠብቅበት ወቅት : ፓትርያርኩ ከትግራይ ጉብኝታቸው ሲመለሱ ደስ ብሏቸው ሰርፕራይዝድ ይሆኑ ዘንድ በግማሽ ሚሊዮን ዶላር የቤት እቃቸው በአዲስ ሞዴሎች ሊቀየር እንደሆነ ተዘግቦ ጉድ ስንል ነበር::
በዚህ ጉዳይ መቼስ ፓትርያርኩ እጃቸው አይኖርም ሲመለሱም ይነግሩናል ብለን ስንጠብቅ ደሞ ሌላ ነገር መጣ::
ፓትርያርካችን የኦርቶዶክስና የካቶሊክ ሃይማኖት ልዩነቱ ጠባብ ነው የሚል ትምህርት እያስተማሩ ነው::
በምን ስሌት ይሆን የሁለት ባህርይና አንድ ባህርይ አስተምህሮ አንድ የሚሆነው:: የኦርቶዶክስ ትምህርተ ሃይማኖት ተዋህዶ ነው:: የክርስቶስ ስጋና መለኮት ፍጹም ተዋህደዋል:: መዋሃዱም እንደ ወተትና እንደ ውሃ በመቀላቀል ወይም ደግሞ እንደማርና እንደ ውሃ በመባረዝ ሳይሆን :-- ባህርይና ባህርይ ሳይጣፉ : ሳይባረዙ እንደ ነፍስና ስጋ አንድ አካል አንድ ባሕርይ በመሆን ተዋህደዋል::
ይህም ተዋህዶ መንታነት ( ሁለትነት) የለውም:: ቃል ስጋ ሆነ:: ሰው አምላክ ሆነ:: በተዋህዶም የቃል ገንዘብ ለስጋ : የስጋ ገንዘብ ደግሞ ለቃል ሆነ::
የካቶሊክ ትምህርት ግን ከዚህ የተለየ ነው:: ተዋህዶን አይቀበልም:: የሚያራምዱት ሁለት ባሕርይን ነው:: ስጋና መለኮት አልተዋሃዱም ክርስቶስም ሁለት ባህርይ ነው ይላሉ::
ይህም የአስተምህሮ ልዩነት ሰፊ ስለሆነ አባቶቻችን ገና በአራተኛው ክፍለ ዘመን ተወያይተዋል:: ልዩነቱም እንዲህ ቀላል ስላልሆነ ተወጋግዘዋል:: ከዚያን ግዜ ጀምሮ አንድነት የለንም:: በሃይማኖት ተወጋግዘን ተለያተናል::
ሊቃውንት አባቶቻችንም በሃይማኖት አበው ያስተማሩን ይሄን ነው:: እነ ዲዮስቆሮስ: እነ ባስሊዎስ ዘቂሳርያ, እነ ቄርሎስ ...ወዘተ
የኛም አባቶች ሲያስተምሩን የቆዩት ይሄንን ነበር:: ገናናው ሊቅ መልዓከ ብርሃን አድማሱ ጅምበሬ " መድሎተ አሚን " በሚለው መጽሓፋቸው ዳር እስከዳር በሚባል ሁኔታ ያስተመሩት ይሄንን ነው:: አራት አይናው አለቃ አያሌው ታምሩም " መች ተለምደና ከተኩላ ዝምድና" ብለው ለአባ አየለ የጻፉት ይሄንኑ ነው:: ከጳጳሳቱም እነ አቡነ ጎርጎርዮስ : በቤተ ክርስትያን ታሪክ እና በዓለም መድረክ መጽሓፋቸው የጻፉት ይሄንኑ ነው:: ስንቱን መጽሃፍ ዘርዝሬ እዘልቀዋልሁ::
አባ ማቲያስ ከየት አምጥተው ነው ልዩነታችን ጠባብ ነው የሚሉት? በሃይማኖት ዲፕሎማሲ አለ አንዴ? ኦርቶዶክሳውያኑ መሰረቶቻችን አነ ዲዮስቆርዮስ ያስተማሩን ይሄንን ይሆን እንዴ?
በነገረ መለኮት ላይ ብቻ ሳይሆን በብዙ ነገር ላይ ከካቶሊክ ጋር አንድነት የለንም:: ስለ እመቤታችን እኛና እነሱ የምናምነው የተለየ ነው:: ጾማችን ብዙ ልዩነት አለው:: ቁርባናችንም እንዲሁ:: ቢዘረዘረ ብዙ የሆነ የማንስማማባቸው ጉዳዮች አሉ::
እንዴት ነው ልዩነታችን ጠባብ የሆነው?
http://www.addisadmassnews.com/images/Issue-826.pdf
No comments:
Post a Comment