Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Sunday, November 8, 2015

ቤተክህነት በታሰሩት መምህር ግርማ ላይ ተጨማሪ ክስ ደረበች * ፖሊስ ቤታቸው የተገኘውን 8 ሲምካርዶች እያጣራሁ ነው አለ







(ዘ-ሐበሻ) ፖሊስ በማታለል ወንጀል ጠጥርሬ አስሬያቸዋለሁ ያላቸው መምህር ግርማ ላይ ተጨማሪ ክሶች እየተደራረቡ ይገኛሉ:: ፖሊስ ከሰው ሕይወት መጥፋት ጋር በተያያዘ ወንጀል ተጠርጥረዋል በሚል ክስ ለመመሥረት እየተዘጋጀ እንደሆነ በተነገረበት በዚህ ወቅት ቤተክህነት ዛሬ ተጨማሪ ክስ ደርባባቸዋለች::

ዛሬ ፍርድ ቤት የቀረቡት መምህር ግርማ ከዚህ ቀደም ዘ-ሐበሻ እንደዘገበችው ተጨማሪ 14 ቀናት የጠየቀ ቢሆንም ፍርድ ቤቱ ግን 5 ቀን ብቻ ፈቅዷል:: ፖሊስ 14 ቀን የጠየቀበትን ምክንያት ለፍርድ ቤቱ ሲያስረዳ ያልተያዙ ተጠርጣሪዎች አሉ፤ ከቤት ሽያጭ ጋር በተያያዘ ተጠርጣሪው ከሚኖሩበት ወረዳ የሰነድ ማስረጃ አልቀረበልኝም፤ ቤታቸው ላይ በተደረገው ብርበራ ስምንት ሲም ካርዶች የተገኙ በመሆኑ ሲም ካርዶቹ በማን ስም የወጡ ናቸው? እና በስልኩ ውስጥ የሚገኙ መረጃዎችን ኢትዮ ቴሌኮም አጥርቶ እንዲልክልን ደብዳቤ ጽፈን ውጤቱን እየተጠባበቅን ነው የሚሉት ይገኙበታል።

ሌላው እና ዛሬ በፍርድ ቤት የተሰማው ክስ ቤተክህነት ያቀረበችው ክስ ነው:: በዚህም መሠረት መምህር ግርማ ወንድሙ በሐሰተኛ ሰነድ ቤተክህነት እንደፈቀደችላቸው በማስመሰል ቤተክርስቲያኒቱ ስም በሃገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሃገር ሲያስተምሩና ሲያጠምቁ ቆይተዋል የሚል ክስ ነው:: የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ለመምህር ግርማ ወንድሙ የተፃፉ ያላቸውን ባለ ሰባት ቅፅ ደብዳቤዎችን ጠቅላይ ቤተክህነት ለፖሊስ እንደማስረጃ ልኳል:: ፖሊስ ይህንን ምርመራ ለማከናወን 14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ቢጠይቅም በዚህኛው ክስ 7 ቀን ብቻ ተፈቅዶለታል::

በ እስር ላይ የሚገኙት ተጠርጣሪው መምህር ግርማ ወንድሙ በበኩላቸው ደቡብ ወሎን ጨምሮ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ቤተክህነት ደብዳቤ እየፃፈልኝ ነው ሳገለግል የሰነበትኩት የሚል መከራከሪያ አቅርበዋል:: ጠበቆቻቸውም እሳቸው በቋሚነት በሚያገለግሉባቸው የረር ስላሴ እና ጀሞ ሚካኤል እንኳን ህገ ወጥ ናቸው የሚል በቤተክህነት የተላከ አንዳችም ደብዳቤ ያለመኖሩን እንዲሁም መንፈሳዊ አገልግሎት መስጠት ወንጀል ስላልሆነ ፍርድ ቤቱ የተጠየቀውን የጊዜ ቀጠሮ አቤቱታ ውድቅ አድርጎ ደንበኛችን የዋስትና መብታቸው ይከበርላቸው ሲል ጠይቋል። ፖሊስም መምህር ግርማ የተከሰሱት በሃሰተኛ ሰነድ መገልገል ከፍተኛ ወንጀል በመሆኑ ዋስትና እንዳይፈቅድ ተከራክሯል::

ፍርድ ቤቱ ፖሊስ አቶ ግርማ ቤት ስበረብር አገኘኋቸው ያላቸውን 8ሲምካርዶች ለመመርመርና ከኢትዮ ቴሌኮም መረጃ ለማግኘት 14 ቀን ይሰጠኝ ላለው ጥያቄ የ5 ቀን ብቻ ቀነ ቀጠሮ ሰጥቷል::

በዚህም መሠረት መምህር ግርማ በመጀመሪያውና አሁን የተጨመረው ክስ ጉዳይ ጥቅምት 30 እና ህዳር 3 ቀን 2008 እንዲታይ ተለዋጭ ቀጠሮ ይዟል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከዘ-ሐበሻ ምንጮች መረዳት እንደተቻለው መምህር ግርማን አስሮ ለረጅም ጊዜ ለማቆየት ተጠርጥረው የታሰሩበትን ጉዳይ ከሰው ሕይወት መጥፋት ጋር ለማያያዝ ፖሊስ ምስክሮችን እያፈላለገ ይገኛል::

Zehabesha

No comments:

Post a Comment

wanted officials