Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Wednesday, November 4, 2015

'Never internet freedom' “ፍሪደም ሃውስ” ኢትዮጵያ ውስጥ የኢንተርኔት ነጻነት ፍጹም የሌለበት ሀገር እንደሆነ በ2015 ሪፖርቱ አስታወቀ





በኢንተርኔት ነጻነት ከ12 የአፍሪካ አገራት የመጨረሻውን ደረጃ ይዛለች ቻይና የኢንተርኔት ነጻነት በመገደብ 1ኛ ናት
የኢንተርኔት ነጻነት በአለማቀፍ ደረጃ ለአምስት ተከታታይ አመታት እያሽቆለቆለ እንደሚገኝና ኢትዮጵያም የኢንተርኔት ነጻነት ከሌለባቸው የአለማችን አገራት አንዷ መሆኗን “ፍሪደም ሃውስ” የተባለው አለማቀፍ ተቋም ሰሞኑን ባወጣው አመታዊ ሪፖርት አስታወቀ፡፡ተቋሙ በ65 የአለማችን አገራት ላይ ያካሄደው የ2015 የኢንተርኔት ነጻነት ጥናት ሪፖርት፣ ከአለማችን አገራት የከፋ የኢንተርኔት ነጻነት የተንሰራፋባት ቻይና መሆኗን ጠቁሞ፣ ጥናቱ ካካተታቸው 12 የአፍሪካ አገራት መካከልም ኢትዮጵያ በኢንተርኔት ነጻነት የመጨረሻውን ደረጃ ትይዛለች ብሏል፡፡
2.9 በመቶ የኢንተርኔት አገልግሎት ሽፋን ባለባት ኢትዮጵያ፣ የማህበራዊ ድረ ገጾችና የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ አፕሊኬሽኖች እንዲሁም ፖለቲካዊና ማህበራዊ ይዘት ያላቸው ጽሁፎች ይታገዳሉ፣ ጦማርያንና የኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ተጠቃሚዎችም ይታሰራሉ፣ ፕሬሱም ነጻ አይደለም ብሏል፡፡
በአገሪቱ የኢንተርኔት አቅርቦትና ተደራሽነት ችግሮች እንዳሉ የጠቆመው ሪፖርቱ፣ የአገልግሎት መቆራረጥና አዝጋሚነት በስፋት እንደሚያጋጥምና በአይሲቲው ዘርፍ ለሚሰማሩ ገለልተኛ ተቋማትና ስራ ፈጣሪዎች የሚሰጠው ዕድልም እጅግ ውስን ነው ብሏል፡፡የ2007 አገራዊ ምርጫ መቃረቡን ተከትሎ በርካታ ተጽዕኖ ፈጣሪ ዜናዎች እንዳይሰራጩ ታግደዋል፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ድረገጾችም አገልግሎት እንዳይሰጡ ተደርገዋል ያለው ሪፖርቱ፤ ከ100 በላይ ድረገጾችም አሁንም ድረስ ታግደዋል፤ መንግስት በኢንተርኔትና በሞባይል በሚደረጉ ግንኙነቶች ላይ የሚያደርገውን ክትትልና ስለላ አጠናክሮ ቀጥሏል ብሏል፡፡መንግሥት በበኩሉ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚሰነዘሩ ተመሳሳይ ትችቶችን ማስተባበሉ ይታወቃል፡፡ የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን በቅርቡ እንደገለፀው፤ የኢንተርኔት ስርጭትና አጠቃቀምን ለመቆጣጠር የሚያስችል ህግ ይፀድቃል፡፡
ኢትዮጵያ በርካታ ጋዜጠኞችን በማሰር ቀዳሚ ከሆኑት የአለማችን አምስት አገራት አንዷ ናት ያለው ሪፖርቱ፣ ከ2014 እስከ 2015 ባለው ጊዜም፣ መንግስት ሃሳባቸውን በገለጹ ጦማርያንና በድረገጽ ጋዜጠኞች ላይ የሚያደርሰውን እንግልትና እስራት አጠናክሮ ቀጥሏል ሲል ገልጿል፡፡የ2015 የኢንተርኔት ነጻነት ሪፖርት እንደሚለው፤ ጥናት ከተደረገባቸው 65 የአለማችን አገራት መካከል ነጻ የተባሉት 18 ሲሆኑ፣ 28 አገራት የተወሰነ የኢንተርኔት ነጻነት እንዳለባቸው፣ 19 አገራት ደግሞ የኢንተርኔት ነጻነት እንደሌለባቸው ተረጋግጧል፡፡


https://freedomhouse.org/report/freedom-net/freedom-net-2015

No comments:

Post a Comment

wanted officials