Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Friday, November 27, 2015

የፕ/ር ብርሃኑ ነጋ ከአስመራ ወደ ብራሰልስ መጠራት | ዜና ትንታኔ


ከብስራት ወልደሚካኤል
ፕሮፌሰሩ ለረቡዕ ህዳር 22 ቀን 2008 ዓ.ም. (December 2, 2015) ከአስመራ ወደ ቤልጄየም ብራሰልስ የተጠሩት በሀገራችን ኢትዮጵያ ድርቅን ተከትሎ በተከሰተው ፖለቲካዊ የፖሊሲ ውድቀት ወለድ ርሃብ ጉዳይ ላይ ለአውሮፓ ህብረት ፓርላማ ንግግር፣ ምክክር እና ውይይት ለማድረግ እንደሆነ ይነገራል፡፡ የኢህአዴግ የ11 በመቶ የቁጥር ኢኮኒሚ ዕድገት ጋጋታ ገደል የከተተውና በምግብ ራሳችንን ችለናል መዝሙር ከአዳራሹ ነፋስ እንደወሰደው የሚያሳብቀው ከ15 ሚሊዮን በላይ ህዝብ በርሃብ አለነጋ ከመገረፍ አልፎ አስቸኳይ የምግብ ርዳት እንደሚያስፈልገው የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተራድዖ ድርጅቶች እና የተባበሩት መንግሥታት ይፋ አድርገዋል፡፡
ይሄንን እውነታ ለመደበቅ መንግሥት ከፍተኛ ወጪ በማውጣት ለማስተባበልና በርሃቡ ወደተጎ ዜጎች አካባቢ ሚዲያ ድርሽ እንዳይል እና እንዳይዘገብ በውስጥ መመሪያ መተላለፉንም ከሰማን ሰነበትን፡፡

ይሄ ሁሉ የራስን የጥፋት ገመና ለመሸፈን ሲባል ህዝብ ርሃቡ ከእኛ ቁጥጥር ውጭ አይደለም ሲባል ለሀገሬው ዜጋ በቋንቋው ሲነገር፤ ለዓለም አቀፍ ለጋሽ ሀገሮች ደግሞ በእንግሊዘኛ በሀገሪቱ ከፍተኛ የርሃብ አደጋ መከሰቱን እና በሀገሪቱ የእርዳታ ማስተባበሪያ የጠገኘው እህል ከአንድ ወር እንደማያልፍ በመግለፅ ተማፅኖውን ማሰማቱን ቀጥሏል፡፡ ይህንን ስንሰማ የኢህአዴግ መንግሥት አስተዳደር ኃላፊነቱ ለነጮች ነው ወይስ ለኢትዮጵያውያን የሚል ጥያቄ ቢያጭርም ከተለመድ የተለየ ነገር ግን የለም፡፡ ለዓመታት የተለመደ የመረጃ (ዳታ) ጋገራ መግለጫና ፕሮፖጋንዳ በተጨማሪ በግልፅ መረጃ ለማፈን ከፍተኛ በጀት መድቦ መንቀሳቀስ ከጀመረ እነሆ ከ10 ዓመታት በላይ ሆኖታል፡፡ ልዕለ ኃያሏ አሜሪካም ብትሆን ከስርዓቱ ያላትን የፀጥታ ጉዳይ ትብብር (ወታደሮችን ለአላስፈላጊ እልቂት ማገዳ ካላት ስምምነት) አኳይ እንደ ጥሩ አጋር ብትቆጥርም የስርዓቱን አምባገነንነት፣ ዘረኛ አገዛዝ፣ ዴሞክራሲያዊ ተቋማት አለመኖር፣ የፍትህ እጦት፣ ሙስና እና ተጠያቂነት የሌለው አሰራር የሚከተለው ስርዓት እንደሆነ ልትሸሽገው አልቻለችም፡፡
ይሁን እንጂ የአውሮፓ ህብረት የተለመደ ሰብዓዊ እርዳታውን በስሱም ቢሆን መለገሱን ባያቆምም የምንጊዜም የስርዓቱ ቀኝ እጅ የሆኑት እንግሊዝ፣ ጣሊያን እና አየርላንድ እንደድሮ ለስርዓቱ ሰዎች ፊት መስጠቱን የቀነሱ ይመስላሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ኢትዮጵያን በሚመለከት በአውሮፓ ህብረት አሊያም በአውሮፓ ኢኮኖሚ ቅንጅት የጋራ አባል ሀገሮች በኩል ውሳኔ እንዲያልፍ እየተደረገ መሆኑን እየታዘብን ነው፡፡ ወቅታዊውን ርሃብ ለማስታገስና ለተጎዱ ወገኖች የሚደረው ሰብዓዊ እርዳታ እንኳ እንደቀድሞ በቀጥታ ለመንግሥት ከመስጠት ይልቅ በእርዳታ መልክ የተሰጠው ገንዘብ በሌሎች በጎ አድራጎት ድርጅቶች በኩል በቀጥታ ለተጎጂዎች እንዲደርስ የሚያስችል አሰራር እየተከተሉ እንደሆነ የስርዓቱ አጋር አሜሪካ እና በቅርቡም ስውድን የወሰደችው እርምጃ አንዱ ማሳያ ነው፡፡ ይህ የሚያሳየው ስርዓቱ በተለያዩ ለጋሽ ሀገሮች እንኳ እምነት እንደታጣበት እና የተለመደው የመረጃ ጋገራ ሪፖርትና ጋጋታ ፋይዳቢስ መሆኑን የተገነዘቡ ይመስላል፡፡
እነሆ አሁን ደግሞ የኢትዮጵያውን ርሃብ በተመለከተ ህዝባዊ ዓመኔታና ቅቡልነት ባይኖረው ኃላፊነት ያለበት መንግሥት እያለ ስርዓቱን ለመገርሰስ ከሚታገሉት መካከል ተዓማኒና ትክክለኛ መረጃና ትንታኔ ይሰጣሉ ተብለው ከታመኑት መካከል በአውሮፓ ህብረት ፓርላማ አማካኝነት ከአስመራ የትግል ሜዳ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ተጋብዘዋል፡፡ በርግጥ ፕሮፌሰሩ ካላቸው የፖለቲካ ስብዕና በተጨማሪ በሙያቸው ከፍተኛ የምጣኔ ሃብት ባለሙያና ተመራማሪ እንደመሆናቸው መጠን በስፍራው መጋበዛቸው የህብረቱ ትክክለኛ ምርጫ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ይሄ ደግሞ የስርዓቱን ሰዎች የበለጠ ምክንያታዊ መሸሸጊያ የሚያሳጣ ወቅታዊ የመረጃ ጉዳይ ሆኗል፡፡ የሚገርመው በኢትዮጵያ ስም ስርዓቱን ወክሎ በቤልጀየም ከፍተኛ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር እያሉ ስለ ኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳይ መረጃና ትንታኔ እንዲሰጡ ከበረሃ የትግል ሜዳ የፕሮፌሰሩ መጋበዝ ለስርዓቱ ትልቅ ራስምታት ነው፡፡ ምክንያቱም ፕሮፌሰሩን እና የሚመሩትን የፖለቲካ ድርጅትና አባላት በሽብርተኝነት ለማስፈረጅ ለዓመታት በተለመደ የመረጃ ጋገራ ቢሞከርም በአሜሪካም ሆነ በአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት ተቀባይነት አላገኘምና፡፡
Birhanu nega photo
በተለይ በመረጃ እና ሐሳቡን ለመግለፅ ለታፈነው የኢትዮጵያ ህዝብ ትልቅ አጋጣሚ ሲሆን፤ ለፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ እና ለሚመሩት ድርጅት እንደ አንድእመረታ ሊታይ ይችላል፡፡ እንደ አንዳንድ የስርዓት ቅርበት ያላቸው ምንጮች ጥቆማ ከሆነ መንግሥት ርሃቡን ከሀገሬው ሰው በመደበቅ ለጋሽ ሀገራት በተማፅኞ በማጨናነቅ ዕርዳታቸውን በጥሬ ገንዘብ ወይም ዶላር እንዲሆን እየሰራ እንዳለ እና ለዚህም ያቀረበው ምክንያት ገንዘቡ ከተሰጠኝ ከሀገር ውስጥ ነጋዴዎች እህሉን ራሴ ገዝቼ በማከፋፈል ጊዜና ጉልበት መቆጠብ እችላለሁ ማለቱ ተሰምቷል፡፡
ይህ ለተጎጂዎች ታስቦ ሳይሆን መንግሥት በሀገሪቱ ከደረሰበት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት የተነሳ አጋጣሚውንም እንደ ጥሩ ዕድል ሊጠቀምበት እንዳሰበና እስካሁንም እንዳልተሳካለት ለስርዓቱ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ተጠቁሟል፡፡ በአሁን ወቅት ከአስከፊው ርሃብ በተጨማሪ በሀገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት በመከሰቱ የተለያዩ አስመጪዎች እና ኢንዱስትሪዎች ለአብነትም ቴክኖ ሞባይል የስልክ መገጣጠሚያን የመሳሰሉት ስራ ማቆማቸውም መነገር ከተጀመረ ሰነባብቷል፡፡ በዚህ ሁሉ የስርዓቱ አጣብቂኝ ውስጥ ፕሮፌሰሩ የበለጠ ተዓማኒነትና ተቀባይነት አግኝነተው በአውሮፓ ህብረት መጋበዛቸው በቀጣይ ምን ሊያሳየን ይሆን የሚለውን ወደፊት አብረን የምናየው ነው ሚሆነው፡፡

ቸር ወሬ ያሰማን፡፡

No comments:

Post a Comment

wanted officials