የአለም ምግብ ፕሮግራም (FAO) በድርቁ ለተጎዱ ኢትዮጵያውያን የሚያቀርበው የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ ዕርዳታ ከሁለት ሳምንት በኋላ ሊያልቅበት እንደሚችል ትናንት ረቡዕ አሳሰበ። የተረጂዎች ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ ምክንያት የሚያደርገው የእርዳታ አቅርቦት ከፍተኛ እጥረት አጋጥሞት እንደሚገኝ የገለጸው ድርጅቱ፣ የምግብ አቅርቦቱ በተያዘው የፈረንጆች ወር መጨረሻ ላይ ሊቋረጥ እንደሚችል ይፋ አድርጓል። የአለም የምግብ ፕሮግራም እስከፊታችን ሰኔ ድረስ ከሚያስፈልገው የ228 ሚሊዮን ዶላር መደበኛኛ የአልሚ ምግቦች አቅርቦት መካከል ሰባት በመቶ የሚሆነው ብቻ እስከአሁን ድረስ ሊገኝ መቻሉን አመልክቷል። ከተለያዩ አለም አቀፍ ድርጅቶችና ሃገራት የተገኙ እርዳታዎች በአብዛኛው በምግብ እጥረት ክፉኛ ለተጎዱ ሰዎች በተለይ ለህጻናት እየዋለ እንደሚገኝም ድርጅቱ ገልጿል። በየወሩ የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ ፈላጊዎች ቁጥር ኣየጨመረ በመሄዱ ምክንያት የእርዳታ አቅርቦቱና ፍላጎቱ ያልተመጣጠነ ሲሆን በቀጣዮቹ አራትና አምስት ወራቶች ውስጥ የተረጂዎች ቁጥር በእጥፍ ያድጋል ተብሎ ተሰግቷል። ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግስትና አለም አቀፍ ድርጅቶች የተረጂዎችን ቁጥር በአግባቡ ለማወቅና የእርዳታ ጥሪን ለማድረግ የዳሰሳ ጥናት እያካሄዱ እንደሚገኝም ለመረዳት ተችሏል። በድርቅ በተጎዱ አካባቢዎች እርዳታን እያደረገ የሚገኘው የአለም የምግብ ፕሮግራም ባለፈው ወር በሶማሌ ክልል ብቻ ለ 1.5 ሚሊዮን ሰዎች የእርዳታ አቅርቦት ማድረጉን በረፖርቱ አመልክቷል። ይሁንና ድርጅቱ በእጁ የሚገኘው የምግብ አቅርቦት ውስን በመሆኑ ምክንያት የእርዳታ ስራው ከሁለት ሳምንት በኋላ ሊቋረጥ እንደሚችል አሳስቧል። የተባበሩት መንግስታትን ጨምሮ የአሜሪካ፣ ካናዳ፣ ስዊዘርላንድ፣ ስዊድንና፣ ኖርዋይ መንግስታት ከ50 ሚሊዮን ዶላር በላይ የዕርዳታ ድጋፍ ለአለም የምግብ ፕሮግራም ማድረጋቸውንም ከድርጅቱ የተገኘ መረጃ አመልክቷል። አለም አቀፍ የግብረ-ሰናይ ድርጅቶች በድርቅ የተጎዱ ሰዎችን ለመታደግ አፋጣኝ ርብርብ ማድረግ እንደሚጠበቅበትም ይኸው የዓለም የምግብ ፕሮግራም አሳስቧል።
No comments:
Post a Comment