Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Wednesday, May 7, 2014

“በግድቡ ምክንያት ግብጽ 'የማይቀር አደጋ' ውስጥ አይደለችም” ፤ አል-ሲሲ

“ውሃ የህይወትና የሞት ጉዳይ ነው”፤ መፍትሔ መፈለግ “የግድ” ነው፤ አል-ሲሲ

“በግድቡ ምክንያት ግብጽ 'የማይቀር አደጋ' ውስጥ አይደለችም”
el sisi
በቅርቡ በግብጽ ለሚካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ያሸንፋሉ እየተባለ የሚጠበቁት ዕጩ ተወዳዳሪ አብዱል ፈታህ አል-ሲሲ “የውሃ ነገር” ለግብጽ “የህይወትና የሞት ጉዳይ” ሲሉ ገለጹ፡፡ ከኢትዮጵያ ጋር በመሆን መፍትሔ መፈለጉ “የግድ” እንደሆነ አስታወቁ፡፡ በቅርቡ በግድቡ ዙሪያ ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረቡ በውጭ የሚገኙ ሦስት ኢትዮጵያውያን ምሁራን የግድቡ መሠራት ግብጽን “በማይቀር አደጋ” ላይ እንደማይጥላት አስረዱ፡፡
በግብጽ በተላለፈ የቴቪ ስርጭት ትላንት ቃለመጠይቅ የሰጡት የቀድሞው የግብጽ ጦር መሪ ፊልድ ማርሻል አል-ሲሲ ግድቡን አስመልክቶ ሰፊ ትንተና እንዳልሰጡ አልሃራም የቲቪ ስርጭቱን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡ ሆኖም ዕጩ ፕሬዚዳንታዊ ተወዳዳሪ “የሌሎችን ፍላጎትና ጥቅም የምንረዳ መሆናችንን ማሳየት ይገባናል፤ (የዚያኑ ያህልም) የራሳችንን ጥቅም ለማስጠበቅ ጽኑ መሆን አለብን፤ (ምክንያቱም) ውሃ ማለት ለእኛ የህይወትና የሞት ጉዳይ ነው” ብለዋል፡፡
አል-ሲሲ በአባይ ጉዳይ ከኢትዮጵያ ጋር ሊደረግ የሚገባው ንግግር ትኩረት ሳይሰጠው ለረጅም ጊዜ የቆየ መሆኑና ውይይቱም የተጀመረው ዘግይቶ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ “ለኢትዮጵያና ለሌሎች አፍሪካ ወንድሞቻችን ተገቢውን ጥረትsisi አለማድረጋችንን ማመን አለብን፤ በዚህ ዓይነቱ ጉዳይ ለመተባበርና መፍትሔ ለማግኘት ድርድርና የጋራ መግባባት ቁልፍ ናቸው” በማለት አል-ሲሲ የግብጽን ፍላጎት አስረድተዋል፡፡
በሌላ በኩል በዚሁ የአባይ ግድብ ዙሪያ በቅርቡ ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረቡና በውጭ የሚገኙ ሦስት ምሁራን የግድቡ መሠራት ግብጽን “የማይቀር አደጋ” ላይ እንደማይጥላት አስታውቀዋል፡፡ ፕሮፌሰር ሚንጋ ነጋሽ፣ ፕሮፌሰር ሰይድ ሃሰንና ፕሮፌሰር ማሞ ሙጬ “Misplaced opposition to the Grand Ethiopian Renaissance Dam” በሚል ርዕስ ባቀረቡት በዚህ ጥናታዊ ጽሁፍ ላይ ታላላቅ ግድቦችን በተመለከተ የሚቀርቡ የተቃውሞ ሃሳቦች መኖራቸውን ዓለምአቀፋዊ መረጃዎችን በማጣቀስ ይተነትናሉ፡፡ ከእነዚህም ሃሳቦች መካከል ጥቂቶቹ የሕዝብ መፈናቀል፣ ሙስና፣ ከኮትራት ውሎች ጋር በተያያዘ ሊኖር የሚገባ ግልጽነት፣ የግንባታና የጥገና ወጪ፣ ወዘተ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ ይህም በመሆኑ ኢትዮጵያውያን በግድቡ ዙሪያ ያላቸውን ሕጋዊ ጥያቄ የማንሳትና የመጠየቅ መብት እንዳላቸው ምሁራኑ ያስረዳሉ፡፡
በመቀጠልም በቅርቡ ከዓለምአቀፍ የባለሙያዎች ፓናል አምልጦ የወጣ መረጃ በመጥቀስ ግድቡ ከኢኮኖሚ አንጻር መቀጠል የሚችል መሆኑን፣ ዲዛይኑ አንዳንድ መጠነኛ “ማስተካከያዎች” ሊደረግበት የሚገባ ቢሆንም ዓለምአቀፍ ደረጃን የጠበቀ መሆኑን፣ ሥራውን እያካሄደ ያለው ኮንትራክተር ታላላቅ ግድቦችን በመሥራት ዓለምአቀፋዊ ዕውቅና ያለው መሆኑን፣ ወዘተ በመጥቀስ የግድቡ ሥራ በግብጽ ላይ መቅሰፍትን የሚያመጣ አለመሆኑን ኢትዮጵያውያኑ ምሁራን ባለ 48 ገጽ ምሥጢራዊ ሰነዱ በመጥቀስ ማጠቃለያ ሰጥተዋል፡፡ የግድቡ ሥራና መጠናቀቅ ግብጽን “የማይቀር አደጋ” ውስጥ እንደማይከታትም ሦስቱ ምሁራን ይናገራሉ፡፡abay and church
በ“ህዳሴው” ግድብ ዙሪያ በግብጽና ኢትዮጵያ መካከል ያለው መካረር ቀጥሎ ከጥቂት ቀናት በፊት ለሁለተኛ ጊዜ ግብጽን ለመጎብኘት ቀጠሮ ተይዞላቸው የነበረው አቡነ ማቲያስ የግብጹ አቡነ ታዋድሮስ ዳግማዊ በላኩላቸው መልዕክት ምክንያት ጉብኝቱ መሠረዙን ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ ዘግቦ ነበር፡፡ የግድቡ ጉዳይ ወደ ሃይማኖት መንደር መዝለቁ የሁኔታውን አሳሳቢነት የሚያሳይ መሆኑንጎልጉል በወቅቱ የገለጸ ሲሆን በሥራው ላይ የሚገኙ መሃንዲስ ኢህአዴግ የአገር ሃብት የሆነውን ግድብ ሥራ ለራሱ ርካሽ የፖለቲካ መሣሪያነት መጠቀሙ አግባብ የሌለው መሆኑን መናገራቸውን ጠቅሶዘግቧል፡፡
ግብጽን በፕሬዚዳንትነት ይመራሉ እየተባለ የሚጠበቁት አል-ሲሲ በመፈንቅለ መንግሥት ከሥልጣናቸው የተባረሩትን ሙርሲን የሚተኩና የምዕራባውያን ከፍተኛ ድጋፍ ያላቸው “ሥዩመ-ፕሬዚዳንት” የመሆናቸው ጉዳይ የበርካታዎችን ትኩረት የሳበ ነው፡፡ ፊልድ ማርሻል አል-ሲሲ የአባይን ግድብ በተመለከተ ከኢትዮጵያ ጋር መፍትሔ መፈለጉ “የግድ” እንደሆነ ቢጠቅሱም ውሃ ለግብጻውያን “የህይወትና የሞት ጉዳይ” ከመሆኑ አንጻር የግብጽን ጥቅም አስጠብቃለሁ ብለው መናገራቸው እንዴት ሊታረቅ እንደሚችል ወደፊት በሂደት የሚታይ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያና ግብጽ በአባይ ጉዳይ ገና ብዙ የሚቀራቸው መሆኑን የሚያመላክት ነው፡፡

No comments:

Post a Comment

wanted officials