ርዮት አለሙ፣ እስክንድር ነጋ፣ በቀለ ገርባ …….እያልን ስሞችን መዘርዘር እንችላለን። በብዙ ሺሆች የሚቆጠሩ ዜጎች ሕገ ወጥና ኢፍትሃዊ በሆነ መንገድ የታሰሩ ወገኖቻችን፣ ከእሥር እንዲፈቱ ስንጠብቅ ፣ ሌሎች እየተጨመሩ ነው። ከቃሊት ዉጭ ሆነው እነ ርዪትን ሲጎበኙ የነበሩ አሁን እነ ርዮት አለሙን እየተቀላቀሉ ነው።
ዞን ዘጠኞች ፣ እነ ጋዜጠኛ ተስፋአለም፣ የሚጽፉትን ፣ የሚጦምሩትን እኛም አንብበነዋል። በድብቅና በሚስጠር አልነበረም ሃሳባቸውን ሲያካፍሉን የነበሩት። የኛ አካል ናቸው። እነማን እንደሆኑ እናውቃቸዋለን። የታሰሩት ወንጀል ስለፈጸሙ አይደለም። ሕግን ስለጣሱ አይደለም። ወንጀላቸው አገራቸውን መዉደዳቸው ነው። ወንጀላቸው ለፍትህ መቆማቸው ነው። ወንጀላቸው ዶር መራራ ጉዲና እንዳሉት፣ ከጫካ የወጡ ግን ጫካ ከነርሱ ያልወጣ፣ ከበስተጀርባ ሆነው እነ ኃይለማሪያም ደሳለኝ እያዘዙ የሚፈልጡና የሚቆርጡ፣ ከሕግ በላይ የሁኑና ለሕግ ደንታ የሌላቸው፣ ጥቂቶች እንዲጽፉ የማይፈልጉት ስለጻፉ ነው። «እነዚህን የሳይበር ስፔስ አርበኞች ልክ ብናገባቸው፣ ሌሎችም ፈርተው አርፈው ይቀመጣሉ» የሚል የተሳሳተና እንጭጭ አስተሳሰብ ስላላቸው ነው።
እንግዲህ ጥያቄዉ «የኛ ምላሽ ምንድነ ነው የሚሆነው ? » የሚለው ነዉ። የአለም አቀፍ ድርጅቶች፣ በግለሰብ ደረጃ በርካታ ኢትዮጵያዊያን የተሰማንን ሐዘንና ንዴት ገልጸናል። ተገቢም ነው።
እንግዲህ ጥያቄዉ «የኛ ምላሽ ምንድነ ነው የሚሆነው ? » የሚለው ነዉ። የአለም አቀፍ ድርጅቶች፣ በግለሰብ ደረጃ በርካታ ኢትዮጵያዊያን የተሰማንን ሐዘንና ንዴት ገልጸናል። ተገቢም ነው።
ነገር ግን ከዚያ አልፈን መሄድ መቻል ያለብን ይመስለኛል። አገዛዙ ዋና ግቡ እኛን ተስፋ ማስቆረጥ ነው። ገዛ ተጋሩ በሚባል የፓልቶክ ክፍል አንዲት የአገዛዙ ካድሬ ትሁን ደጋፊ፣ አገዛዙ ላይ ችግር ያለንን ሰዎች »ፓፕ ኮርኖች» (ፈንድሻውች) ነበር ያለችን። ለጊዜ ቡፍ ብለን ጸጥ የምንል !!!!!!
እንግዲህ ምርጫዉ የኛ ነው። እኛ ሚሊዮኖች ነን። እነርሱ ጥቂቶች ናቸው። እኛ ፍቅርን ፣ ሰላምን፣ እኩልነትን አንድነት እንፈልጋለን። እነርሱ ዘረኝነትን፣ ጭካኔን፣ ግፍን፣ መከፋፈልን ይሰብካሉ። እኛ አገራችን በፍቅር እንገባ እንላለን። እነርሱ ግን «እኛ ስልጣን ላይ እንቅይ እንጂ አገር ብትፈልግ ትፈራርስ» ይላሉ። እኛ የዘር፣ የሃይማኖት የጾታ፣ የእድሜ ልዩነት ሳይኖር እያንዳንዱን ዜጋ፣ አዎ ከጠ/ሚኒስተሩ ጀመሮ እስከ ሊስትሮዉ ፣ በስብእናዉና በኢትዮጵያዊነቱ የከበረ ነው እንላለን። እነርሱን ግን« ሁሉንም አዋቂዎች፣ ፖሊሱም ፣አቃቢ ሕጉም፣ ዳኛዉም፣ ሕግ አውጭዉም፣ ሕግ አስፈጻሚዉም፣ ኢኮኖሚስቱም፣ ኢንጂነሩም እኛ ብቻ ነን። ሌላዉ ከጫማችን በታች ተረግጦ መቀመጥ ነው ያለበት» ይላሉ።
እንግዲህ ምርጫው የኛ ነው። እንደ እንስሳ አንገታችን ላይ ማነቆ ታስሮ፣ ጥቂቶች እየጎተቱን እና እንደፈለገ እየተጫወቱበን መኖር፣ ወይም ነጻነታችንን ማወጅ። ዝም ብለን ለጊዜው ብቻ የምንጮህ ፓፕኮርኖች መሆን ወይም አለትን የሚሰባብር ዳይናሚት መሆን። እነርሱ እንደሚፈልጉትና እንደሚመኙት፣ ዝምታን መርጠን፣ አፋችን ዘግተን መቀመጥ፣ ወይም ዳግማዊ ዞን ዘጠኖች በመሆን የዞን ዘጠኝ አባላት ቁጥርን ከስድስት፣ ወደ 6 ፣ ስድሳ ሚሊዮን ማሳደግ። የናንተን አላውቅም እኔ ግን፣ ከዛሬ ጀመሮ የዞን ዘጠኝ ኩሩ አባል መሆኔን አረጋግጣለሁ።
መርዛማ እባብ ከመንደፍ ዉጭ፣ ሌላ ነገር አያውቅም። እነርሱም ማሰር እንጂ መፍታት አያውቁም። ዜጎችን ማሸበር እንጂ ማረጋጋት አያውቁም። ኢትዮጵያዉያንን ማዋረድ እንጂ ማክበር አያውቁም። ይህ ለሃያ አመታት የዘለቀ ግፍ አንድ ቦታ ላይ መቆም አለበት። አሁን መቆም አለበት። ሊያስቆሙት የሚችሉት ደግሞ እነ ጆን ኬሪ አይደሉም። እኛ ብቻ ነን።
ሚያዚያ 26 (ሜይ 3 ቀን) በአንድነት ፓርቲ የተዘጋጀ የእሪታ ቀን ሰላማዊ ሰልፍ በአዲስ አበባ ይደረጋል። ከብዙ ግፊትና ትግል በኋላ አስተዳደሩ ለሰልፉ እውቅና ሰጧል። ሰልፉ ሰላማዊና ሕጋዊ ሰልፍ ነው። የምንፈራበትም፣ የምንሸሽበት ምንም ምክንያት የለም። ሰልፍ የምንወጣዉ ለፖለቲከኞች ወይንም ለአንድ ፓርቲ ፣ ወይንም ለሌሎች አይደለም። ሰልፍ የምንወጣው ለራሳችን ስንል ነው። «በአዲስ አበባ እድገት አለ። ዴሞክራሲ አለ። ስርዓቱ መቀጠል አለበት። ኢሕአዴ ጥሩ እያደረገ ነው። የታሰሩትም መታሰራቸው ተገቢ ነው» የሚሉ እነ ሚሚ ስብሀቱ ሰልፍ ባይወጡ ብዙ አያስገርምም። ግን በልባችን ለውጥ እየፈለግን፣ መሰረታዊ የመብትና የኢኮኖሚ ጥያቄዎች እያሉን፣ ዝምታን ከመረጥን ግን፣ ይሄን የሚያዚያ 26ቱን ሰልፍ እንደ አንድ መድረክ ተጠቅመን ድምጻችንን ማሰማት ካቃተን ግን፣ ታዲያ እንዴት እንዘልቀዋለን ?
እንግዲህ ከሚሊዮኖች አንዱ እንሁ እላለሁ። እንዉጣ። ድምጻችንን እናሰማ። መብታችንን እናስከበር። የሕዝብ ጉልበትና አቅም ምን ማለት እንደሆነ እናሳይ። ለታሰሩ አጋርነታችንን እንግለጽ። ስድስት ዞን ዘጠኖች ቢታሰሩ ሚሊዮኖች እንደተወለዱ እናስመስክር።
No comments:
Post a Comment