ኢሳት ዜና ፦ የሰብአዊ መብቶች ጉባኤ ባወጣው መግለጫ ፍትህ ሚኒስቴር ሃምሌ 28፣ ቀን 2006 ዓም በፋክት፣ ሎሚ፣ ጃኖ፣ አዲስ ጉዳይ፣ እንቁ መጽሄቶችና አፍሮ ታይምስ ጋዜጣ ላይ ያቀረበው ክስ በህገመንግስቱ የሰፈረውን ሃሳብን የመግለጽ ነጻነት ፣ ኢትዮጵያ በፈረመቻቸው የሰብአዊ መብቶች አለማቀፍ መግለጫ አንቀጽ 19 ፣ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች አለማቀፍ ቃልኪዳን አንቀጽ 19 እንዲሁም የአፍሪካ የሰዎችና ህዝቦች ቻርተር አንቀጽ 9ን የሚጥስ ሆኖ እንዳገኘው ገልጿል። «ህዝቡ የመንግስትን ጠንካራና ደካማ አሠራር በግልጽ እንዲከታተል፣ በዜጎች ላይ የመብት ጥሰት ከተከሰተ በወቅቱ እንዲታረሙ፣ የዲሞክራሲያዊ አሰራርና ልምድ በሀገሪቱ እንዲዳብር የሚያበረታቱ የዜጎች መነጽር» ሆነው ሳለ «የድርጅቶቹ መዘጋት ጉዳቱ የድርጅቶቹ ብቻ ሳይሆን ይልቁንም የመላ ዜጎች» በመሆኑ ፣ በተፋጠነ ህጋዊ ሥነ ሥርዓት ተጣርቶ የሚመለከተው የመንግስት አካል አስፈላጊውን መፍትሄ እንዲሰጥበት ሰብአዊ መብት ጉባኤ አጥብቆ ጠይቋል።
ኢህአዴግ በበኩሉ በኦፊሻል የፌስቡክ ድረ–ገጹ ባሰፈረው ሀተታ የተከሰሱት ሚዲያዎች ቀድሞውኑ ቪዛ ለማግኘት አቅደው ሲሰሩ የነበሩ ናቸው ብሏቸዋል። እነዚህ የሕትመት ውጤቶች ላይ ሲሰሩ የነበሩ ግለሰቦች ቀድሞውንም በሙያው ሽፋን ከአገር ለመውጣት ሁኔታዎችን ሲያመቻቹ የቆዩ የነበሩና በእቅዳቸው መሰረት ምንም አይነት ክስ ሳይቀርብባቸው ልንከሰስ፤ ልንታሰር ነው በሚል ከአገር የወጡ መሆናቸውን ገልጿል።
የተከሰሱት የሕትመት ውጤቶች በአገሪቱ ሽብርተኝነትንና አክራሪነትን ለመዋጋት የሚደረገውን ትግል ከማውገዝ ይልቅ «ለአክራሪነትና ሽብርተኝነት ጥብቅና ቆመዋል» በማለት ክስ የሚያቀርብ ሲሆን የሕትመት ውጤቶቹ ድብቅ አጃንዳቸውን ለማሳካት ከሃይማኖት አክራሪዎች ጋር ተቀናጅተው አማኙን ወደ ተሳሳተ አቅጣጫ ለመምራት ጥረዋል፤ የህትመት ውጤቶቹ የአገሪቱን ብሔሮች፤ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በመከፋፈል ዕቅዳቸውን ለማሳካት ጥረት ከማድረግም አልቦዘኑም በማለት አስፍሯል።
በፅንፈኛዎቹ የሕትመት ውጤቶች ላይ በጸሃፊነት ወይም በአምደኛነት የሚያገለግሉ ግለሰቦችም ራሳቸውን «ተቃዋሚ ጋዜጠኛ» ብለው እንደሚጠሩና መንግስትን በዓመፅ ለማስወገድ እንደሚሰሩ በግልፅ እንደሚናገሩ ጠቅሶ እዚህ ላይ ልብ ማለት የሚያስፈለግው ነጥብ ምንም እንኳን ፀሃፊዎቹም ሆኑ አምደኞቹ በራሳቸው ባስተላለፉት ህገ ወጥ መልዕክት ሊጠየቁ የሚችሉበት አጋጣሚ ቢኖርም አቃቤ ሕግ ግን በህትመት ውጤቶቹ አሳታሚዎችና ባለቤቶች ላይ እንጂ በግለሰቦቹ ላይ ክስ አልመሰረተም ይላል።
ከ17 በላይ የሚሆኑ ጋዜጠኞች ሀገር ጥለው ከወጡ በኋላ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት አስተያየት ኢህአዴግ መራሹ መንግሥት ወከባ እንግልት፣ ማስፈራራት እንዲሁም የሚዲያ ተቋሙን እንዲዘጉ አሳታሚዎችን በግልጽ ማስፈራራት፣ ማተሚያ ቤቶችን በማስፈራራት እንዳይታተሙ የማድረግ ሥራዎችን በማከናወን ችግሮች እንደደረሱባቸውና በዚህ ምክንያት ሀገር ለቀው ለመውጣት መገደዳቸውን መግለጻቸው ይታወሳል።
No comments:
Post a Comment