Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Saturday, September 20, 2014

ከ የኢትዮጵያ መምህራን ድምፅ ይሰማየተሰጠ መግለጫ የኢህአዴግ ስልጠና ላይ

በሰሞኑ የኢህአዴግ ስልጠና ላይ የመምህራኑ ምላሽ
ከ የኢትዮጵያ መምህራን ድምፅ ይሰማየተሰጠ መግለጫ
ከመስከረም 5,2007 አ.ም ጀምሮ መንግስት የአቅም ግንባታ እያለ የጠራው ስልጠና እየተካሄደ ይገኛል:: ገዢው ፓርቲ ስልጣን ከያዘበት 1983 አ.ም ጀምሮ የተለያዩ ስልጠናዎችን ሲሰጥ መቆየቱ የሚታወቅ ሲሆን የዘንድሮውም ከበፊቶቹ ምንም የተለየ ሀሳብ ያለተነሳበት እና ድግግሞሽ የበዛበት ብሎም ገዢው ፓርቲ ለኢትዮጵያዊነት እና ለመምህርነት ሙያ ያለውን አይን ያወጣ ጥላቻ ያሳየበት ነበር::
ስልጠናው እንደተጀመረ መምህራኑን የማሰልጠን ድፍረቱን እና እድሉን ያገኙት አቶ ኤፍሬም ግዛው የተሰኙ የአዲስ አበባ ከተማ አሰተዳደር ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ሀላፊ ናቸው:: አቶ ኤፍሬም በንግግራቸው ወቅት በተደጋጋሚ ሀገሪቷ ከየትኛውም ዘመን በተለየ በኢኮኖሚያዊ እድገቱ እና ሰላም በማረጋገጡ ዘንድ ስኬታማ መሆን እንደቻለች ለማስረዳት ሞክረዋል::
እንደ የኢትዮጵያ መምህራን ድምፅ ይሰማ ጊዜያዊ ኮሚቴ እምነት ከሆነ የኢህአዴግ ትልቁ ችግር እራሱን ሞቶ ከተቀበረው የደርግ ስርአት ጋር እያነጻጸረ ህዝቡን ለመሸወድ የሚያደርገው ቀቢጸ ተስፋ ነው:: እድገት ውድድር መሆኑን እናምናለን ሆኖም ይህ ስርአት መወዳደር ካለበት ባላፉት 24 አመታት በእነጋና ቦትስዋና እና ደቡብ አፍሪካ ከታዩት ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ እድገቶች ጋር እንጂ ከሞተ ስርአት ጋር ሊሆን አይገባውም:: ሌላው የሰላም ጉዳይ ሰላም አንድ አይነት ትርጓሜ የለውም የጥይት ድምጽ ወይም የቦንብ ፍንዳታ አለመስማት ብቻውን ሰላም አለ ሊያስብል የሚችልበት ምንም አይነት መርህ አይኖርም::
ማሰብ ለቻለ እና ህሊና ላለው ሰው አዛውንቶች እና ህጻናት ጎዳና ወድቀው መመልከት ሰላምን ይነሳል, በሀገራቸው መኖር ስላልቻሉ በስደት አለም የበረሀው ሙቀት የባህር ራት የሆኑት ኢትዮጵያዊያንን ጉዳይ መስማትም ሰላምን ይነሳል, አንድ የሚበላው ያጣ ህጻን ከውሻ ጋር ተሻምቶ ሲመገብ መመልከትም ሰላምን ይነሳል:: በአጠቃላይ በግልጽ የጥይት ድምስ አለመስማት እንደስኬት ልንቆጥረው የሚገባ አይደለም ድምጽ ሳይሰማ የተገደሉ ኢትዮጵያውያንን ጊዜ ይቁጠራቸው::
ከአቶ ኤፍሬም በመቀጠል መምህራኑንን ለማሰለጠን እድሉን ያገኙት አቶ ይስሀቅ ግርማይ የተሰኙ ከትምህርት አለም ብዙ እንደራቁ እና ቀጥታ ከጫካ መጥተው የመንግስት ቢሮ እንደገቡ ፊታቸው የሚያሳብቅባቸው ምንም አይነት እውቀትም ሆነ ስነምግባር የሌላቸው ግለሰብ ናቸው::
እኚህ ግለሰብ በተደጋጋሚ ነፍጠኛ, ጠባብ ትምክህተኛ እና ጨለምተኛ በማለት መምህራኑን ብሎም ሰፊውን የሀገራችንን ህዝብ ሲሳደቡ ውለው ከርመዋል ነገር ግን እንደ የኢትዮጵያ መምህራን ድምፅ ይሰማ ጊዜያዊ ኮሚቴ እምነት ከሆነ በአሁኑ ወቅት በሀገራችን ያለው ብቸኛው ነፍጠኛ, ጠባብ ትምክህተኛ እና ጨለምተኛ ለእኔ ብቻ ተዉት እያለ ያለው ኢህአዴግ ብቻ እና ብቻ ነው::
ከዚህ ስልጠና ለመታዘብ እንደቻልነው ገዢው ፓርቲ ትልቅ የተማሩ ሰዎች እጥረት አለበት ይህንንም እራሱ ኢህአዴግ ሆን ብሎ ያደረገው በመሆኑ እነደ መምህር የዚህችን ሀገር የነገ እጣ ፋንታ ስንመለከት ያስፈራል::
በመጨረሻ እ|ኛ መምህራን ትግላችንን አጠናክረን እንቀጥል ሲል የኢትዮጵያ መምህራን ድምፅ ይሰማ ጊዜያዊ ኮሚቴ ጥሪውን እያስተላለፈ ሌሎች አካላትም ከመምህራኑ ጊዜያዊ ኮሚቴ ጋር ይቆሙ ዘንድ ጥሪውን ያቀርባል::
ድል ለመምህራን
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ
የኢትዮጵያ መምህራን ድምፅ ይሰማ ጊዜያዊ ኮሚቴ
መስከረም 10,2007 አ.ም
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ

No comments:

Post a Comment

wanted officials