Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Saturday, September 13, 2014

የዩክሬይን ክራሚያና የሩስያ ጉዳይ ስለኢትዮጵያና ኤርትራ ያልተዘጋ አጀንዳ ምን ያሰተምረናል?

የዩክሬይን ክራሚያና የሩስያ ጉዳይ ስለኢትዮጵያና ኤርትራ ያልተዘጋ አጀንዳ ምን ያሰተምረናል?

(አክሊሉ ወንድአፈረው – የግል አስተያየት)
መስከረም 2, 2007 (ስፕተምበር 12 2014  )

ukrባለፉት ጥቂት ወራት በዩክሬንና ክራሚያ ውስጥ የተቀሰቀሰው ሁኔታ እና አሁን የደረሰበት ደረጃ ከኢትዮጵያ የፖለቲካ ምህዳር አንጻር ብዙ ዕድምታዎች አሉት፡፡ እነዚህን ዕድምታዎች መመርመር  በሀገራችን ውስጥ ያለፉና የወደፊት ጉዞ ላይ የተከሰቱ፤ እና ሊከሰቱም የሚችሉ ጉዳዮችን  ከወዲሁ በግምት ውስጥ በማስገባት  ሀገራዊ ራዕያችንን ፣ የትግል አቅጣጫችንን አና አጋርና ተቀናቃኝ ሊሆኑ የሚችሉትን ሃይሎች ለይቶ ለማወቅ ያግዛል ብዩ አሰባለሁ።  ይህን ማወቁ ደግሞ በሀገራችን እና በብሑራዊ  ጥቅማችን ላይ ጉዳት ሊያስከትሉ ከሚችሉ ተግባሮች እንድንቆጠብ ዕድል ይሰጠናል። የዚሀ ጽሁፍ ዓላማም በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ውይይት ለመጫር ነው።

ለመንደርደሪያ ያህል፦ ለመሆኑ በታሪክ ክራሚያ ዩክሬን ወይስ ሩሲያ ነበረች?
ጠቅለል ባለ ሁኔታ የክራሚያን ያለፉት 200 ዓመታት ታሪክ ስንመለከት በዋናነት የሩሲያ አካል ሆና መቆየቷን እናያለን። በሌኒን የሚመራው የሶሻሊስት አብዮት ከተቀጣጠለ ከ 1917 በሁዋላም ቢሆን ክራሚያ በሶቭየት ህብረት ዕቅፍ ውስጥ አንድ ራስ-ገዝ አስተዳደር ሆና ቆይታለች።

ክሬሚያ የዩክሬን አካል የሆነችው ባውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ1954 በወቅቱ የራሽያ ኮሚኒስት ፓርቲና ያገሪቱ መሪ በነበሩት በኒኪታ ክሩስቼቭ ሲሆን፤ እኘህም ሰው የትውልድ ቦታቸውና የፖለቲካ አጋራቸው ለሆነችው ዩክሬን በስጦታ መልክ ከሰጡ በሁዋላ ነበር፡፡ በወቅቱ ይህ ጉዳይ ለሶቭየት ፖለቲካ መሪዎችም ሆነ ለክራሚያ ነዋሪዎች አስጨናቂ ጉዳይ አልነበረም፡ ለምን ቢሉ ዩክሬን የሶቭየት ህብረት አንድ ክፍለ ሀገር (ሪፐብሊክ) የነበረች ሲሆን የክራሚያ ዩክሬን ውስጥ መግባት ለአስተዳደር አመቺነት ካልሆነ በስተቀር በጊዜው ሌላ ሰፊ የፖለቲካ እንደምታ አልነበረውምና ነው። ከዚያም አልፎ በተለይ በምስራቅ አውሮፓ ይገኙ የነበሩት ሁሉም ሶሻሊሰት ሀገሮች  በሶቭዬት ሶሻሊስት ሪፐብሊክ የበላይነት ጥላ ስር  እንዳንድ ሀገር ሆነው  (በሶሻሊስት ዓለማቀፋዊነት መርህ) ይመሩ ስለነበርም እንኳንስ በአንድ ሀገር ስር ያሉ ያስተዳደር ክልሎች በተለያዩ ሶሻሊስት ሀገሮችም መካከል ቢሆን ድንበርና ድንበርተኘነት ታላቅ ቁምነገር ያለው ተደርጎም ይወሰድ እንዳልነበር ማሰታወስ ያስፈልጋል።

የክራሚያ ነዋሪዎች በማንነት አንጻር ራሳቸውን እንዴት ይመለከታሉ?
ይህ ጉዳይ አጅግ አወዛጋቢና በዪከሬን ግጭት ውስጥ ተፋላሚ የሆኑ ክፍሎችም የግል አቌማቸውን የብዙሃኑን ፍላጎት እንደሚንጸባርቅ አድርገው የሚሟገቱበት ዕውነታ ነው::

በዩክሬይን ስልጣኑን የጨበጡት ክፍሎች እና ደጋፊዎቻቸው “የክራሚያ ነዋሪዎች ራሳቸውን የሚያዩት ከሁሉም በላይ  ከራሽያ የተለዩና ዩከሬንያዊ አድርገው ነው የሚቆጥሩት”  የሚለውን አመለካከት ሁሉም ስው እንዲቀበለው ይፈልጋሉ:: ክራሚያ የዩክሬን አካል ሆና የቆየችበትን ጊዜ በማጣቀሰም በተለይም አዲሱ ትውልድ የተማረውም፤ ያደገውም ስለዩክሬን እየተነገረው ስለሆነ ስለ ራሽያዊነት የሚሰማውም የሚያውቀውም  ቅንጣት ያህል ነገር እንደሌለና ይህም በመሆኑ  ከራሽያ ጋር  የሚያገናኝው ስንሰለት እንደተበጣጠስ ደጋግመው ሲናገሩ ይደመጣሉ::

በክራሚያ ውስጥ የሚታየውና የሚጨበጠው  እውነታ ግን ሌላ ነው:: ከ 60 ዓመታት የዩክሬን አካልነት እና ከ23 አመታት ሙሉ ለሙሉ መለያየት በሁዏላም የከሬሜያም ሆነ ሌላው የምሥራቅና ደቡብ ምሥራቅ ዩክሬን ነዋሪዎች የሚሰማችው ስሜት ግን ከሩሲያ ጋር ያላችው የቀደመ ትስስር አንጅ የዩክሬን አካልነት ሆኖ አልተገኘም:::

ከዚህ በታቸ የሚታየውና በቅርቡ የተካሄደ  አንድ ጥናት  እንደሚያሳየው  ከ 70%  (ሰባ ከመቶ) የማያንሱ ክራሚያዎች ራሳቸውን የሚቆጥሩት ብቻ ሳይሆን ትስስርንም ቢሆን የሚሹት ከሩሲያ ጋር እንደሆነ ያመለክታል::

Data: Razumkov Center; Figure: Grigore Pop-Eleches and Graeme Robertson/The Monkey Cage

ይሀ ሁኔታ የሚያሳየው ከአቅመቢሷ ዩክሬን ጋር ከመዳበል ይልቅ ሰፋና ጠንከር ካለችው ሩሲያ ጋር መሆኑ ምን ያህል ጠቀሜታ እንዳለው መገንዘብን ብቻ ሳይሆን የረጅሙ ጊዜ ትስስር የፈጠረውን ማንነትንም በቀላሉ መበጣጠስም  እንደማይቻል ነው::

በዚህም ምክንያት ይመስላል ክራሚያዎች በተለያየ ሁኔታ በዩክሬን ውስጥ ማንነታቸውን ሊያሰከብሩ ሲጥሩ ቆይተውና ሳይሳካላቸው ባሉበት ሁኔታ ዩክሬን ጓዟን ጠቅልላ በአውሮፓ ማህበረሰብ ዕቅፍ ስር ለመግባት ርምጃ መውሰድ ስትጀምር ሁኔታው ስላልጣማቸው ከገቡበት ፈተናና አጣብቂኝ እንድትታደጋቸው ሩሲያን የተማጸኑት።
ቀደም ሲል በምዕራቡ ዓለም ፖለቲካ ተንታኞች  ክራሚያወች ወደ ራሽያ መዋሀድን አይፈልጉም፤  ፍላጎታቸው ከሌላው አውሮፓ ጋር ይበልጥ መተሳሰር ነው በማለት ደግመው ደጋግመው ይናገሩ ወይም ያስተጋቡ እንጂ በማርች 2014  ሬፈረንደም ሲካሄድ ግን  97%  የሆነው ህዝብ ነበር ዩክሬንን ትቶ ወደ ራሽያ መቀላቀልን የመረጠው። ይህ ሁኔታ የክራሚያ ተወላጆች ከሩሲያ ጋር  ለረጅም ዘመናት ከነበራቸው የታሪክ፣ የፖለቲካ፤ የቤተሰብ፣ የባህል፣ የስነ ልቦናና፣የማሕበራዊ ግንኙነት   ሙሉ በሙሉ  መለያየት ችለናል፤  በራሸያና በክራሚያወች  መካከል የነበረውን የአንድነትና የትስስር ስሜት አጥፍተነዋል፤  ብለው ሲያስቡ ለነበሩ ሁሉ መርዶና የራስ ምታት ነው የሆነባቸው::
ክራሚያውያን ከሩስያ ጋር መልሶ ለመቀላቀል ከ 90 በመቶ በላያ በሆነ ድምጽ  ፍላጎታቸውን ገልጸው ደስታቸውን ሲገልጹ )  Mike Collett-White and Ronald Popeski SIMFEROPOL/KIEV Sun Mar 16, 2014 SIMFEROPOL/KIEV (Reuters) – Russian)
ባሁኑ ሰአት በክሬሚያ የሚታየው ሁኔታ በሻቢያ ስር የወደቀውን ህዝብ የማንነት ጥያቄ በተመለከተ ብዙ ጉዳዮችን እንድናገናዝብ ያስገድዳል። ላለፉት 23 አመታት “የኛ ሀገር ነች; የማንነታችን  መግለጫ ነች”; ብለው ከሚመለከቷት እና ከሚወዷት ኢትዮጰያ ተነጥለውና በኤርትራ ውስጥ ከነመሬታቸው ተገደው ከሚገዙት የአፋር፤ ኩናማ፤ ኢሮብ፤ የሀማሴን፣አካለጉዛይ እና ሌሎችም ወገኖቻችን ሁኔታ ጋር እጅግ ይመሳሰላል። ታላቁ የአፋር ተወላጅ የተከበሩት ቢትወደድ ዓሊ ሚራህ፣ “እንኳንስ ህዝቡ ግመሎቻችንም ቢሆኑ የኢትዮጵያን ባንዲራ ያውቃሉ” ሲሉ የተናገሩት ታላቅ መሪ ቃል  ስለአፋር ህዝብ የማይናጋ ጥልቅ ኢትዮጽያዊነት በቂ ማስረጃ ነው። ከዚህም ሌላ ቅድመ ሻቢያ/ወያኔ ከኢትዮጵያዊነት ውጭ ምንም አናውቅም ብለው ስለቆሙ በሻቢያ ሰራዊት በተደጋጋሚ የተደበደቡት የኩናማ፤ የሳሆ ወዘተ ወገኖች ታሪክ  ኢትዮጰያዊነትንና የትዮጵያዊነትን ስሜት ከነዚህ ህዝቦች መለየት እንደማይቻል ወይም እጅግ ረጅም ጊዜ እንደሚወስድ ያመላክታል።
በመሀል ብዙ ቅሬታ እንደተከሰተ አጠያያቂ ባይሆንም ኤርትራን ከኢትዮጵያ ጋር ለማሰተሳሰር ስለታገሉትና ስለወደቁት አርበኞች፣በልጆቻችውና በልጅ ልጆቻቸው አዕምሮ ውስጥ በአሁኑ ሰአት ምን አይነት ስሜት እንደሚመላለስ  የክራሚያ ተመክሮ ፍንጭ ሊሰጥ ይችላል:: በተለይም ደግሞ የክሬሚያ አዲስ ትውልድ አሁንም ከአማሪጮች ሁሉ ወደ ራሸያ ማዘንበሉን እንደመረጠ ስንመለከት አበረታች ሁኔታ ቢፈጠር በሻቢያ ስር በምትገኘው ኤርትራ ውስጥ ሊከሰት የሚችለውን ዕውነታ መገመት አይከብድም::

የክራሚያን ሁኔታና ዕውነታ ስንመለከት፤ የህወሀት መሪወች ሲሰብኩት የቆየውና አሁን ደግሞ ባንዳንድ  ተቃዋሚወች ውስጥም እየሰረጸ ያለው “የኤርትራ ጉዳይ ያለቀለት ጉዳይ ነው” የሚለው  አመለካከት የህዝብን ሰነልቦናዊ ጥንካሬ ወደሚቦረቡር እና ብሄራዊ ጥቅምንም ወደሚጎዳ ተግባር እንዳያነጉደን ያሰጋል። የሀገር ጥቅም የሚጠበቀው ጽናት እና ጥራት ባለው ራዕይ ላይ በተመሰረተ ትግል እንጂ  ጊዚያዊ ጥቅምን ለማሳደድ ሳያላምጡ በመዋጥ ወይም ደግሞ መሰረታዊ የሀገር ጥቅምን “እሱን አሁን እርሱት”  በሚል  ራእይ የለሽ አካሄድ ከቶውንም ሊሆን አይችልም::

ሩሲያ ስለ ክራሚያ ምን ያስጨንቃታል?
ሩሲያ በኢኮኖሚም ሆን በወታደራዊ ሃይል በዓለም አቀፍ ደረጃ ተፈላጊነትና ተደማጭነት ያላት ታላቅ ሀገር እንደመሆኑዋ በቆዳ ስፋቱዋም ቢሆን አሁንም ባንደኘነት ደረጃ ላይ ትገኛለችል። ባንጻሩ ደግሞ ክራምያ በህዝብ ቁጥርም ሆነ በኢኮኖሚ ለሩስያ እዚህ ግባ የማይባል አስተዋጽኦ ነው የሚኖራት። በኢኮኖሚ አንጻር ብቻ ካየነው በዋናነት ተጠቃሚዋ ከራሚያ እንጂ ሩሲያ አትሆንም፡፡ ሆኖም ግን የዘር ሓረግና ታሪክን የሚገዛው ገንዘብ ብቻ አደለምና  ክራሚያ በሩስያ  (ሩስያም በክሬምያ) በታሪክም ሆነ በህዝቡ ሥነ-ልቦና ላይ እጅግ ቁልፍ ቦታ አላቸው፡፡ይህ ሁኔታ ምን ያህል መሰረት ያለው እንደሆነ ለመገንዘብ የሚቀጥሉትን ታሪካዊ ሁኔታዎች እንመልከት፡

  • በጊዜው በመዳከም ላይ የነበረው የኦቶማን ኢምፓየር እና ራሸያ በኦክቶበር 1853 ውጊያ ውስጥ የገቡት በክሬምያ ጉዳይ ነበር፡፡ ውጊያው የተቀሰቀሰው ሩሲያ በክራሚያ የነበሩ የኦርቶዶክስ ክርስትና ተከታዮችን ከጥቃት ለማዳን በወሰደችው እርምጃ ነው ።
  • ይህን ተከትሎ ከ 1853–1856 ባንድ በኩል በራሸያ በሌላ በኩል ደግሞ በፈረንሳይና እንግሊዝ ጥምር ጦር መሀል የተካሄደው ጦርነት በክሬምያ ውስጥ ነበር፡፡
  • የቦልሽቪኮችን ወደ ስልጣን መምጣት ተከትሎ ነጩ ሰራዊት ( the white army) እየተባለ የሚጠራውና ሶሻሊዝምን በሚቃወሙ የምዕራብ ሃይሎች ይደገፍ የነበረው የተቃዋሚዎች ሀይል በ1920 የመጨረሻውንና ወሳኙን ውጊያ ያካሄዱትም በዚሁ በክሬሚያ ነበር።
  • በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከፍተኛ ደም የፈሰሰበት ጦርነት ከተካሄደባቸው ቦታዎች ውስጥ ክራሚያ አንዷና በዋናነት የምትጠቀስ ነች።
  • የጀርመን ናዚዎች ክራሚያን ለመያዝ ባደረጉት ወረራ ከ 170 ሽህ በላይ የሶቭየት ጦር የተሰዋ ሲሆን በወቅቱ ፋሽስቶችን እስከመጨረሻ የመከተችው ኣና የጀግኖች ከተማ በመባል ልዩ ሽልማት የተሰጣት የክራሚያ ዋና መናገሻ የሆነችው ሴቫስቶፖል ነበረች። በወቅቱ ምዕራብ ዩክሬን የፋሽስቱ ሂትለር ተባባሪ በመሆን በሽዎች የሚቆጠሩትን ጸረ-ፋሽስት ሃይሎች እንደገደሉና እንዲሰደዱ እንዳደረጉ ታሪክ መዝግቦታል።
  • በሁለተኛው ያለም ጦርነት ማጠቃለያ በሦስቱ ተባባሪ ሐያላን ሀገሮች (Allied Forces) መሪዎች ያሜሪካው ፍራንክሊን ሩዝቬልት፣ የሩሲያው ጆሴፍ ስታሊን እና የኢንግሊዙ ዊንስተን ቸርችል መካከል የተደረገው ስብሰባ የተካሄደው በያልታ ፣ ክራሚያ ውስጥ ነበር።

ይህ ሁሉ በራሽያውያንና ክራሚያ መካከል ያለውን ከፍተኛ የታሪክና  የሰነልቦና ትሰሰር  አንዱ ሌላውን ለምን እንደሚፈልግ ያሳያል::

ይህ ብቻ ሳይሆን ክራሚያ ለሩሲያ የምታስገኘው  ጂኦ-ፖለቲካዊና ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታም እጅግ ትልቅ ነው። ክራሚያ ቀደም ሲል የሶቭየት ህብረት በሁዋላም የሩሲያ ፌዴሬሽን ባህር ሀይል የሆነው ብላክ ሲ ፍሊት የጦር ሠፈር ነች። በዩክሬን ውስጥ የራሽያ ፍቅር የሌለው መንግስት ሥልጣን ቢይዝ የሩሲያን ደህንነት ዛሬም ባይሆን ነገና ከነገ ወዲያ አደጋ ላይ ሊጥለው እንደሚችል ራሸያ ጠንቅቃ ታውቃለች። ይህ አደጋም አፍንጫዋ ስር ሲከሰት እጅ አጣጥፎና ምንም እንዳልተፈጠረ በማስመሰል ማለፍን የራሸያ መሪወችም አልፈለጉም። ስለዚህም ቀልጠፍና ፈርጠም  ያለ እርምጃ መውስድን አስፈላጊ ሆኖ አግኝተውታል። የራሽያው ፕሬዚደንት ፑትን በቅርቡ ለሀገሪቱ ፓርላማ ባደረጉት ንግግር ክራሚያ ለሩሲያ ምን ያህል ስትራተጂያዊ አስፈላጊነት እንዳላት ሲገልጹ “ ወደ ሜዴትራንያንና ወደ ጥቁር ባህር መሽጋገሪያችን የሆነችው ሶቫስቶፖል በባዕዳን ቁጥጥር ስር ሆና ማየት ከቶውንመ ተቀባይነት የለውም “ ነበር ያሉት።

ከላይ ስንደረደርበት የቆየሁት አመለካከት ወዳገራችን ሁኔታ ሲመለስ፤ ኢትዮጵያሰ ስለ ኤርትራ ምን ያስጨንቃታል የሚለውን ጥያቄ ማጫሩ አይቀሬ ነው። ከዚህ አኳያ እያንዳንዱ ሰው የየራሱን ምርምር አድርጎ መደምደሚያ ላይ እንዲደርስ ያስፈልጋል ብዬ አስባለሁ። ሆኖም ግን ኢትዮጵያ በታሪክ፣ በኢኮኖሚ፣ በሀገር ደህንነት ወዘተ አንጻር እጅግ ብዙ ጉዳት እንደደረሰባት  እና ወደፊትም መገመት የሚከብድ አደጋ እንደተጋረጠባት ብዙወች በመረጃ አስደግፈው ጽፈውበታል። በኢኮኖሚ አንፃር ብቻ ሲታይ እንኴ የራሷን ወደብ እንድታጣ የሆነችው ኢትዮጵያ ለጂቡቲ መንግስት ለወደብ ኪራይ የምትክፍለው ገንዘብ በየቀኑ በሚሊዮኖች የሚቆጠር እንደሆነ ይታወቃል:: ይሀ ገንዘብ ለሀገር ልማት ቢውል ኖሮ የምን ያክል ህጻናትን ህይወት ማዳን እንደሚቻል ምን ያህል ተጨማሪ ትምርት ቤት ጤና ጣቢያ ማቌቌም እና ህይወት ማዳን እንደሚቻል ስናስብ የሁኔታውን አንገብጋቢነት ለመገንዘብ ይረዳል::

አሁን ካለው አሀዝ ስንነሳ ኢትዮጵያ የራሷን ወደብ አጥታ ለጅቢቲ የምትከፍለው ወጪ  በያመቱ ለአንዳንዱ ወረዳ በሚሊዮኞች የሚቆጠር ተጨማሪ በጀት ለመመደብ የሚያሰችል ነው። ይህ ታዲያ ድህነትን ለመቀነስ፣ ለልማት ወዘተ ምን ያህል አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ማንናውም ጤነኛ አእምሮ የሚገነዘበው ነው።

በዚህ አንጻር ሰፋ ያለ ግንዛቤ ለማግኘት ለሚፈልግ ሁሉ የዶ/ር ያዕቆብ ሐይለማርያም “አሰብ የማን ናት”፤ የአምባሳደር ዘውዴ ረታን “የኤርትራ ጉዳይ”፤ ባዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲ የታተመውን “የአክሊሉ ማስታወሻ” ጥሩ ግንዛቤና መረጃ ሊሰጡ የሚችሉ መጻህፍት መሆናቸውን መጥቀስ እወዳለሁ።

የሶቭየት ህብረት መፈራረስ ክራሚያና ኤርትራ
የሲቭየት ህብረት መፈራረስን ተከትሎ በነበረው ያልተረጋጋ ወቅት ክራሚያም በግርግር ከዩክሬን ጋር ተደባልቃ ከራሸያ ተገንጥላ እንድትሄድ አድርገዋል የሚባሉት እንኳንስ ለሀገር ለራሳቸውም ማሰብ ይሳናቸው ነበር እየተባለ የሚነገርላቸው ፕሬዚደንት ቦሪስ ዬልሰን ናቸው:: ግለሰቡ የዚሀ አይነት ውሳኔ ሲወስኑ የክሬሚያን ታሪክ፣ ስትራተጂክ ጠቀሜታ ወዘተ ከቁብ አላስገቡትም፣ የህዝቡንም ስሜት ቦታ አልሰጡትም ነበር። የሳቸው ሩጫ ከምን እንደመነጨ በግልጽ በማይታወቅ መልኩ ጎርባቾቭ የቀደዱትን የለውጥ መንገድ በመለጠጥ ሶቭየት ህብረትን በማፈራረስ ላይ ያተኮረ ነበር፡፡ ክራሚያን በተመለከተም የሶቭየት ህብረት ታላቅ የባህር ሀይል የሆነው ብላክ ሲ ፍሊት ንብረት ሽያጭና ገንዘብ መሰብሰብ ላይ ነበር ትኩረታቸው። ያም ሆኖ  በንግድ አንጻር እንኳ እዚህ ግባ የሚባል ገንዘብ አላገኙበትም።

የክራምያን ጉዳይ መደምደሚያ ለመስጠት የተሞከረው በሶቭይት ሕብረት ባጠቃላይ እንዲሁም በራሽያና በተቀሩት  ሶሻሊስት ሀገሮች ታይቶ የማይታወቅ ቀውስ እና አለመረጋጋት በሰፈነበት ወቅት ነበር። በዚያ የቀውስ ወቅት በቂ የሆነ አማራጭና ረጋ ብሎ ለማሰብ ጊዜ ሳይኖር ሬፈረንደም ተካሄደና 58% የሚሆን ህዝብ ደገፈው በማለት ክራሚያ ከሩሲያ ተለይታ የዩክሬን ግዛት ሆና እንድትሄድ ተወሰነ።

ይህ ጉዳይ ግን በብዙ ዜጎች ልብ ውስጥ ቁርሾ አስከተለ፤ ጠባሳም ጣለ። የጊዜው ሁኔታ ባይመችና በወቅቱ ማድረግ ስለሚገባቸው ነገር ግራ ቢጋቡም፤ እጅግ ብዙ የክራሚያ ኑዋሪዎች ልባቸው መሸፈቱ አልቀረም፡፡ በዘሩም በታሪኩም ራሽያዊ ነኝ ብሎ የሚያምነው የክሬምያ ሀዝብ የለም ዩክሬናዊ ነህ ሲባል ጥርሱን ነከሰ። ሆኖም ግን በወቅቱ የሚያዳምጠው አላገኝም። ያ ታምቆ የቆየ  ቅሬታ  አሁን በቅርቡ አመጽ ወልዶ እነሆ እየሆነ ያለውንና የሆነውን ዓለም እየመሠከረ ነው።

የኤርትራ ከኢትዮጵያ የመገንጠል ዕውነታ ከሶቭየት ህብረት መፈራረስ እና ከቀዝቃዛው ጦርነት “መገባደድ” ጋር በቅርብ የተቆራኘ ነበር፡ “ህዝበ ውሳኔ” (ሬፈራንደም ) የተባለው ሂደትም በሀሪቱ በከፍተኛ ቀውስ ውስጥ በነበረችበት፣ ገና ቋሚ መንግስት እንኳን ሳይኖራት ነበር። በ“ህዝበ ውሳኔ” ሂደት ውስጥም የኢዮጵያዊነት አማራጭ በታፈነበት ኢትዮጵያዊ ነኝ ብሎ የሚያምነውና የሆነውን የአፋርና ኩናማ፣ የሳሆ፤ ወ.ዘ.ተ ህዝብንም ፍላጎት ለማክበር ምንም ጥረት ሳይደረግና ውጤቱም ሳይታይ በግድ ያልሆነውንና ያላመነበትን ማንነት  ተቀበል ተብሎ የተጠናቀቀ የግርግር ሁኔታ ነው። ይህ ስለሆነም እነሆ እስካሁን የቀጠለው ቅሬታ የመሳሪያ ግጭትን ወልዶ ካንድ ቀውስ ወደሌላ በመሽጋገር ላይ ይገኛል።

የሚገርመው ከስልሳ አመት በሓላ ሩሲያ በክሩስቼቭ ጊዜ የተጀመረውን ያስተዳደር ክልል ማሸጋሸግ እና በቦረስ ዬልሲን ዘመን የተወሰደውን የረጅም ጊዜ ዕይታ የጎደለውን የፖለቲካ ርምጃ ለማረም የተዘጋጀ ድርጅትና መሪ አግኝታለች። ኢትዮጵያችን ግን በሁሉም መልኩ ሀላፊነት የጎደለውን የመለስ ዜናዊ ለሀገር ደንታ ቢስ የሆነ ውሳኔ ለማረም እና ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ጥቅም በድፍረት የቆመ የመንግስት መሪ ገና አልታደለችም። ያም በመሆኑ መከራውም ቀጥሏል መፍትሄውም እየተወሳሰበ መሄዱ አይቀሬ ሆኗል።

የተባበሩት መንግሥታት “የዩክሬንን ሀገራዊ አንድነት ስለማሰከበር” ያካሄደው የድምጽ አሰጣጥ
የክሬሚያ ነዋሪወች በዩክሬን ስር መተዳደርን አንፈልግም ብለው ማጉረምረም ሲጀምሩ ነው ታላላቆቹ የምእራብ መንግስታት ሁኔታውን ለማዳፈን መሯሯጥ የጀመሩት። የክሬምያን ህዝብ ታሪክ፣ ፍላጎትና ማንነት ጠንቅቀው የሚያውቁት ምዕራባውያን ጭንቀታቸው ያነጣጠረው በክሬምያ ላይ ሳይሆን ሩሲያ እንደገና ተጠናክራ በመውጣት ጉዳይ ላይ ስለሆነ ይህንን ለማከሽፍ፣ ባለፈው የካቲት መጨረሻ ገደማ ዩክሬን ውስጥ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጠው መንግስት ባመጽ ሲፈነቀል ቃል ያልተነፈሱት ምዕራባውያን፤ በክራሚያ የተደረገውን ሬፈረንደም ተከትሎ ዩክሬን ተወረረ፣ ወዘተ፤ የሚለውን ከበሮ መደለቅ ጀመሩ። ከሁካታው በስተጀርባ ግን አሁን ባለው ሁኔታ ምዕራባውያኑም ሆኑ ራሱ የዩክሬይን መንግስት የክራሚያ ጉዳይ ያለቀለት እንደሆነ የተቀበሉት ይመስላል። ሩጫው ሊፈጠር የሚችለውን ሌላም ምስቅልቅል ሁኔታ ለመቀነስ ምናልባትም ራሱ የዩክሬን እንደሀገር የመቀጠል ጉዳይ አደጋ ላይ እንዳይወድቅ የመጨነቅ፣ ሰፋ ያለ የርስ በርስ ጦርነት ባውሮፓ ውስጥ እንዳይቀሰቀስ የመፍራት ጉዳይ እንጂ ክራሚያን የማስመለስ ፍላጎት አይመስልም።

የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታ ጥበቃው ምከር ቤት (ድምጽን በድምጽ ሽሮ ጥርስ-አልባ የሆነው) እና ጠቅላላ ጉባኤውም በዚህ ጉዳይ ያስተላለፈውና ከፍተኛ ክፍፍል የነበረበት ውሳኔ “ይህን ብለን ነበር “ ከማለት የማያልፍ ነው። ጠንከር ያለ የማዕቀብ እርምጃ ወሰዱ የተባሉት አሜሪካና የአውሮፓ ማህበረሰብም ቢሆኑ ርምጃቸው ጥቂት ባለስልጣኖችን የሚነካ ከመሆን አላለፈም።

ቀረብ ብሎ ሲታይ ደግሞ ያፍሪካ መንግስታት በተለይም የኢትዮጵያ እና የኤርትራ መንግስታት የወሰዱት አቋም ትኩረትን የሚስብ ነው፡፡ የሁለቱም ወኪሎች  በተባበሩት መንግስታት ውሳኔ አሰጣጥ ላይ የክሬምያን ከዩክሬን መገንጠል ሳያወግዙም ሳይደግፉም ድምጽ ተአቅቦ (አብስቴን) በማድረግ ማለፉቸውን እንገነዘባላን።

ይህ የድምጽ አሰጣጥ ከብዙሀኑ ያፍሪካ ሀገሮች የተለየ አይደለም፤ በተባበሩት መንግሰታት ምክር ቤት ”የዩክሬንን ሀገራዊ አንድነት ማሰከበር “ በሚል ርእስ የክራሚያን መገንጠል ለመቃወም የቀረበውን ረቂቅ የውሳኔ ሀሳብ የደገፉ ያፍሪካ ሀገሮች 19 ብቻ ሲሆኑ የተቃውሞ ድምጽ ያሰሙ ሁለት (ሱዳንና ዚምባብዌ ) ድምጸ ተአቅቦ ያደረጉ ደግሞ ወደ 22 ያፍሪካ ሀገሮች ነበሩ። ከነዚህም ውስጥ ኢትዮጰያና ኤርትራ ይገኙበታል። ይህ በሶሰት ቦታ የተከፈለ የድምጵ አሰጣጥ  የሚያሳየው የተባበሩት መንግሥታትም ሆነ ያፍሪካ አንድነት ማህበር በተመሳሳይ ሁኔታዎች ላይ የሚወስዷቸው አቋሞች ከሀገራቸው ፖለቲካ፣ እና ከሚያስገኝላቸው ጥቅም አንጻር እንጂ ከቋሚ መተክልና ዕምነት በመነሳት እንዳልሆነ ነው፡፡

ከዚህ ሁኔታ መገንዘብ እንደሚቻለው ለተመሳሳይ ሁኔታወች እያንዳንዱ ሀገር ስለሚወስደው እርምጃ ወሳኙ ጉዳይ “የተባበሩት መንግስታት ወይም ያፍሪካ አንድነት ህግ” ሳይሆን እያንዳንዱ ሀገር የሚያገኘው ጥቅማ ጥቅም እንደሆነ ነው። ባጭሩ የሀይል አሰላለፉን  የሚገዛው መተክል (ፐሪንስፕል) ሳይሆን በጊዜው ሀገራት የሚያገኙት ጥቅም እና የሀይል ሚዛን ይመስላል።

No comments:

Post a Comment

wanted officials