መስከረም ፪(ሁለት)ቀን ፳፻፯ዓ/ም ኢሳት ዜና :-
የመዠንገር ብሄረሰብ ተወላጆች ጎደሬና ሜጫ በሚባሉት አካባቢዎች እንደ አዲስ በጀመሩት ጥቃት በርካታ ሰዎች መገደላቸውንና እስካሁን አስከሬኖች እንዳልተነሱ የአካባቢው ምንጮች ገልጸዋል። ከጋምቤላ ብሄረሰብ ውጭ ያሉ የሌሎች አካባቢ ተወላጆች በሙሉ ይወጡ
በሚል የተጀመረው ግጭት ፣ ደም አፋሳሽ ሆኖ ከመቀጠሉ ባሻጋር፣ በትናንትናው እላት ብቻ ከ1 ሺ ያላነሱ
ሰዎች ተፈናቅለው ቴፒ ከተማ መግባታቸው ታውቋል።
ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ሰዎች እንደሚሉት ዋነኛው የግጭት መንስኤ በጡረታ የተገለሉ የህወሃት የጦር መኮንኖች የአካባቢውን መሬት በርካሽ ዋጋ በመግዛት ነዋሪዎችን ማፈናቀላቸውና አካባቢውን እየተቆጣጠሩ መምጣታቸው መሆኑን አስተያየት ሰጪዎች ይገልጻሉ።
የመዠንገር ጎሳ አባላት ብሄር ሳይለዩ በማንኛውም ሰው ላይ ጥቃት እየፈጸሙ ሲሆን፣ ካለፉት ሁለት ወራት
ጀምሮ በርካቶች ተገድለው በሺ የሚቆጠሩት ዜጎች ደግሞ ተፈናቅለዋል።
የክልሉ የጸጥታ ሹም መያዛቸውና የቀድሞው የክልሉ ፕሬዚዳንት ኦኬሎ አኳይ ደቡብ ሱዳን ውስጥ ተይዘው ለኢህአዴግ መንግስት ተላልፈው መሰጠታቸው ለአሁኑ ግጭት ማገርሸት ምክንያት መሆኑን ምንጮች ይናገራሉ።
ግጭቱን ለመቆጣጠር ወደ ስፍራው ያመራው የፌደራል ፖሊስ ሰራዊትም ከአካባቢው ታጣቂዎች በደረሰባቸው ጥቃት ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው ምንጮች ገልጸዋል።
ግጭቱ ይህን ዜና እስካጠናከርንበት ጊዜ ድረስ ቀጥሎአል።በጉዳዩ ዙሪያ የክልሉን ባለስልጣናት ለማነጋገር ሙከራ ብናደርግም አልተሳካልንም።
ኢሳት በትናንትና የዜና እወጃው ከ9 ያላነሱ ሰዎች መገደላቸውን ጠቅሶ ነበር። ይሁን እንጅ የአካባቢው ምንጮች እንደሚሉት የሟቾች ቁጥር ከተጠቀሰው አሃዝ በላይ ነው።
No comments:
Post a Comment