Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Sunday, September 21, 2014

አርቲስት ሃይማኖት አለሙ በሞተ ተለየ

(ኢ.ኤም.ኤፍ) በኢትዮጵያ የቴያትር ታሪክ ውስጥ ስማቸው ጎልተው ከሚጠሩት አንጋፋ አርቲስቶች መካከል፤ አርቲስት ሃይማኖት አለሙ በዋናነት ይጠቀሳል። ባጋጠመው ህመም ምክንያት ከዚህ አለም በሞት መየቱ ብዙዎችን አሳዝኗል። እኛ ስለ አርቲስ ሃይማኖት አለሙ ልንለው ካሰብነው በላይ በቅርብ የሚያውቁት ሰዎች ከወዲሁ የተለያዩ የሃዘን መግለጫዎችን መላክ ጀምረዋል። አንዳንዶችም አብረው በነበሩበት ወቅት የነበራቸውን ገጠመኝ በመጥቀስ ስለ አርቲስ ሃይማኖት የጻፉትን ከናንተ ጋር ለማጋራት ወደድን። ከዚህ በታች አቅርበነዋል።
ሃይማኖት አለሙ
ሃይማኖት አለሙ
ደምስ ሰይፉ – “በጋሽ ሐይማኖት ዓለሙ Haimanot Alemu እረፍተ ዜና ልቤ ሃዘን ገብቷቷል… ጋሽ ሐይማኖት በነባሩ የቲአትር መድረካችን ላይ የራሱን ቀለም ያኖረ ትጉህ የጥበብ ሰው ነበር… ለእኔም ሆነ ዘመንተኞቼ ስራዎቹ ሩቅ ቢሆኑም በእርሱ ዙሪያ ያነበብኩዋቸው ድርሳናት በተለይ በነወጋየሁ ንጋቱ ዘመን ፈርጥ የነበረ ሰው መሆኑን ነግረውኛል… ከነፍቄ ጋርም ድንቅ ነበር… በማስተማር ስራውም ብዙ ደቀመዛሙርት አፍርቷል… በተለይ ስሙና ፎቶዎቹን ከፀጋዬ ስራዎች ውስጥ የማናጣው ግሩም ሰው ነበር… በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የ ”ፊትለፊት” ፕሮግራሙም አይዘነጋም… በእውነት ጋሽ ሐይማኖትን ማጣት በአቢሲኒያ የጥበብ መድረክ ላይ አንድ ጣዕም ማጣት ነው… እግዜር ነፍሱን በገነት ያኑራት!!!”
ብርካን ፋንታ በበኩሉ ይህን ብሏል – “ረዳት ፕሮፌሰር ሐይማኖት አለሙ ፣ በአካደሚክስ ዕውቀቱ በዘርፉ ብቸኛ የሚባል ዓይነት ሰው ነበር፡፡ በዩነቨርስቲ መጽሔቶች፣ ባቀረባቸው የምርምር ስራዎች፣ ከዚህ በፊት ከነጋሽ ጸጋዬ ገ/መድህን ጋር በባህልና ጥበብ ዙሪያ ያቀረባቸው essays፣ በአዲስ አበባ ዩነቨርስቲ በመምህርነት ያሳለፋቸው ጊዜያት ለዚህ ሐቅ ምስክሮች ናቸው፡፡ የሐይማኖትን የመድረክ ትወና ለማየት ባልተደለም እፍታውን የማየት አጋጣሚ ነበረኝ፡፡ ለመራሔ ተውኔት አባተ መኩሪያ በተዘጋጀ ስራ ላይ የጋሽ ጸጋዬ ገ/መድህን ስራዎች ሐምሌት፣ ኦቴሎ፣ እናት ዓለም ጠኑ እና ሀሁ ወይም ፐፑ ቁንጹል ስራዎች ቀርበው ነበረ፡፡ ሐይማኖት ያ ግርማ ሞገስ ያለው አቋም ተጽሕኖ ሳይደርስበት የአንድ አዛውንት ገ/ባህሪን ተላብሶ ሲጫወት ለተመለከተው ከዚህ በፊት ሰለእርሱ የትወና ክህሎት እንደ ትንግር ለምን እንደሚወራ መልሱን ያገኝሁበት አጋጣሚ ነበረ፡፡ በጉዲፈቻ ፊልም የዶ/ር ገ/ባህሪ ወክሎ ሲጫወት ለተመለከተውም ለአቡጀዴዎ ትወናም ፍጹም የተለየ ሰው እንደሆነ መረዳት አዳጋች አይደለም፡፡ አጼ ቴዎድሮስን ሆኖ ሲጫወትም የራሱ የሆነ ቀለም ነበረው ይላሉ፣ በቪዲዮ በተቀረጸ “ጴጥሮስ ያቺን ስዓት” በተሰኘው የጸጋዬ ተውኔት ላይ የአንድ ባንዳ ገ/ባህሪን ሲጫወት ተመልክቼዋለሁ፣ ፍጹም እስትንፋስ ለመውሰድ ቅጽበት የሚያሳጣ ብቃት ነበረው፡፡ እንደ አዘጋጅ ሐምሌትን ለመድረክ አቅርቧል፡፡ በፊልም ስራም ቢሆን ምንም እንኳን ያልተሳካለት ቢሆንም የአትዮጵያን መጽሐፍን ወደ ፊልም adopt በማድረግ ፈር ቀዳጅ ሆኗል፡፡ ትወና የሚፈልጋቸው ነገሮች በሙሉ የተቸሩት ሲሆን እነዚህን ጸጋዎች በዕውቀትን በክህሎት ማዳበሩ ካሉትም እንደ አንዱ ላለመሆን ብዙ የተጋ ሰው ነበረ፡፡ ማይክራፎን ኖረ አልኖረ ይህ የሚያስገመግመው ድምጹ ከነሙሉ ግርማ ሞገሱና ደርባባነቱ በየትኛውም አዳራሽ ጥርት ብሎ የሚደመጥ ነበረ፡፡ ትወናን በኢትዮጵያ ተከብሮ ከነበር በሐይማኖት ተክለ ስብዕናና ተክለ ሰውነት ላይ ነው ብንል ማጋነን አይሆንም፡፡”
ጋዜጠኛ አለምነህ ዋሴ እንዳለው፤ “ሃይማኖትን እኔም በእኔ መነገድ አውቀዉ ነበር። የሚያገናኘን የሻሎም ስቱዲዮ ነበር። ሁሌም ራሱን የጠበቀ በአለባበሱ በአነጋገሩ ባህሪው ግርማ የተላበሰ ጨዋ ሰው ነበር።ሁለገብ ታታሪና ፍፁም ዲሲፒሊንድ የሆነ የስራ ሰው ነበር። ከሰዎቸ ጋር የመግባባትና አብሮ ለመሥራት የነበረው ልዩ ብቃት ምሁርነቱን እንዳውቅና እንዳከብረው አድርጉኛል።መከበሩን ሳያጣ መቃለድም ይችል ነበር።ፊትለፊት በተሰኘው የቲቪ ፕርሮግራሙ ያነሳቸው የነበሩ ጉዳዮችና ያቀርባቸዉ የነበሩ እንግዶ ች ስለሱ ሁለገብ ብቃት በጥራት የሚመሰክሩ ነበሩ።ስለእውነት በማውቀው መጠን ትልቅ ሰው ነበር።እንደ ኢትዮጵያውነቴ የተማረ የሰለጠነ ያነበበና እያንዳንዷን የሕይወቱን እለታት በስራና በቁምነገር ያሳለፈ ትልቅ ወገናችንና በስነጥብ የረጅም ጊዜ አገልግሎትና ዝና የነበረው ዕውቅ ሰው በሞት አጥተናል።ለቤተሰቦቹ መፅናናትን እመኝኛለሁ።” ዓለምነህ ዋሴ ከአሥራኤል ቤርሼቫ።
ረ/ፕሮፌሰር አርቲስት ሀይማኖት…
- በትወና /አክቲንግ/ በሜኒሶታ አሜሪካን አገር በሁለተኛ ዲግሪ ተምሯል፡፡
- በአዲስ አበባ ዪኒቨርሲቲና ራክማኖቭ ኮሌጅ ትወናን አስተምሯል፡፡
- የሲሳይ ንጉሱን ልቦለድ /ግርዶሽ/ ወደ ፊልም በመቀየር አዘጋጅቷል፤ ተውኗል፡፡
- የሸክስፒርን ስራዎች በተለይም በጫንያለው ወልደጊዮርጊስና ቴዎድሮስ ተሰማ የተተረጎመውን
ተጫውቷል፡፡
- በተለይም በፀጋዬ ገብረ መድህን ስራዎች በዘመኑ እጅግ ድንቅ ብቃት ያሳየባቸውን የ”እናት ዓለም ጠኑ” እና “ሀሁ በስድስት ወር” ቴአትሮች ገፀባህሪያት በብሔራዊ ቴአትር ተውኗል፡፡
- ሀምሌትን አዘጋጅቷል፡፡
- ከፍቃዱ ተክለማሪያም በፊት ቴዎድሮስን ሆኖ ተውኗል፡፡
- ጊታር በድንቅ ብቃት ይጫወት ነበር፡፡
- በሲዲ ያልተለቀቁ የእንግሊዝኛ ዘፈኖች አሉት፡፡ ከምንም በላይ ግጥም በማራኪ አቀራረብ በማንበብ ይወደድ የነበረው አነጋፋው አርቲስት ሀይማኖት ዓለሙ በመድረክ መምራትም ተወዳጅ ነበር፡፡
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በማስታወቂያው ዘርፍ ተሰማርቶ እየሰራ የነበረው ሀይማኖት ባደረበት ህመም ከዚህ ዓለም ተለይቷል፡፡

No comments:

Post a Comment

wanted officials