በድፍረት ፊልም ላይ ተጥሎ የነበረው ዕግድ ተነሳ
ፊልሙ በሁሉም ሲኒማ ቤቶች ከሐሙስ ጀምሮ ይታያል
የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ የዲፕሎማቲክ ማኅበረሰብ አባላትና የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ቤት ነሐሴ 28 ቀን 2006 ዓ.ም. ተገኝተው ለ15 ደቂቃዎች ከታየ በኋላ፣ በፍርድ ቤት ዕግድ ተጥሎበት የተቋረጠው ‹‹ድፍረት›› ፊልም ችግሩ በሽምግልና በመፈታቱ ዕግዱ ተነሳለት፡፡
በአንጀሊና ጆሊ ኤግዘኪዩቲቭ ፕሮዲዩሰርነት የተሠራውና ሜሮን ጌትነትን ጨምሮ በርካታ ኢትዮጵያውያን የተሳተፉበት ድፍረት ፊልም በውጭ አገር የታየ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ መጀመሪያ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ቤት ተመርቆ በመቀጠል በሁሉም ሲኒማ ቤቶች እንደሚመረቅ ዕቅድና ዝግጅት ከተደረገበት በኋላ፣ ነሐሴ 28 ቀን 2006 ዓ.ም. በመመረቅ ላይ እያለ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ እንዲቋረጥ ተደርጓል፡፡
ለመቋረጡ ምክንያት የሆነው፣ ‹‹ፊልሙ የሚታየው ከእኛ ዕውቅና ውጪ በመሆኑ የማይተካ የሞራልና የኢኮኖሚ ጉዳት ሊያደርስብን ይችላል፤›› በማለት አቶ ፍቅሩ አሸናፊና የፊልሙ ዋና መነሻ የሆነችው ወ/ሪት አበራሽ በቀለ ለፍርድ ቤት ባቀረቡት አቤቱታ ምክንያት መሆኑን መዘገቡ ይታወሳል፡፡
በመሆኑም ሁለቱ ቅሬታ አቅራቢ ከሳሾችና ተከሳሾች ማለትም የፊልሙ ዳይሬክተር አቶ ዘረሰናይ ብርሃኔ፣ ኃይል አዲስ ሥዕሎችና ትሩዝ ኤይድ ሚዲያ በሽምግልና በመስማማታቸው፣ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት መስከረም 8 ቀን 2007 ዓ.ም. በሰጠው ትዕዛዝ ‹‹በድፍረት›› ፊልም ላይ የተጣለው ዕግድ መነሳቱን አስታውቋል፡፡
በሽምግልና የተስማሙት ሁለቱም ወገኖች ግራና ቀኝ ጥያቄ እንደማያነሱ መስማማታቸውን የገለጸው ፍርድ ቤቱ፣ ያቀረቡት ክስ እውነት መሆኑን በቃለ መሐላ አረጋግጠው፣ ለዕግድ ማስከበሪያ የተያዘው 50 ሺሕ ብር ተመላሽ እንዲሆንም ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
የድፍረት ፊልም ዕግድ በመነሳቱ ምክንያት ፊልሙ ከሐሙስ መስከረም 15 ቀን 2007 ዓ.ም. ጀምሮ በሁሉም ሲኒማ ቤቶች እንደሚታይ ለማወቅ ተችሏል፡፡
በፊልሙ ምክንያት ተወዛግበው የነበሩት ሁለቱም ወገኖች ችግራቸውን በሽምግልና ፈተው ዕግዱ ከተነሳ በኋላ፣ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡
No comments:
Post a Comment