Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Saturday, September 20, 2014

ለመምህራን ተማሪዎች በሚሰጠው የፖለቲካ ስልጠና ምክንያት የትምህርት መጀመሪያ ጊዜ ተራዘመ


ለመምህራን ተማሪዎች በሚሰጠው የፖለቲካ ስልጠና ምክንያት የትምህርት መጀመሪያ ጊዜ ተራዘመ

ኢሳት ዜና :-
መንግስት በመላ አገሪቱ የሚገኙ የትምህርት ተቋማት መስከረም 5 ትምህርት እንዲጀምሩ ቀደም ብሎ ይዞት የነበረውን እቅድ በመሰረዝ አዲሱ የትምህርት ዘመን ከመስከረም 30 በሁዋላ እንዲጀመር ትእዛዝ አስተላልፏል።
በትምህርት ሚ/ር ደኤታ ዶ/ር ካባ ኡርጌሳ ዲንሳ ለሁሉም ዩኒቨርስቲዎች መስከረም 5፣ 2007 ዓም የተጻፈው ደብዳቤ   የአንደኛ አመት ወይም አዲስ ገቢ ተማሪዎች ጥሪ ተደርጎ ከመስከረም 18 -20/2007 ዓም ምዝገባ አጠናቀው ኦሬንቴሽን ተሰጥቷቸው ስልጠና እንዲወስዱ፣ የነባር ተማሪዎች ጥሪ መስከረም 30 እና ጥቅምት 1/2007 ዓም ሆኖ ምዝገባ ጨርሰው፣ ትምህርት ሰኞ ጥቅምት 3?2007 ኣም እንዲጀመር፣ የመምህራን ስልጠናን በተመለከተ ሰኞ መስከረም 19/2007 ዓም ኦሬንቴሽን ተሰጥቶ ከማክሰኞ መስከረም 20/2007 ዓም ጀምሮ ለ10 ቀናት ስልጠና እንዲሰጥ ያዛል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በባሕርዳርና ጎንደር ዩኒቨርስቲዎች የሚሰለጥኑ ተማሪዎች ለገዢው ፓርቲ ፈታኝ የሆኑ ጥያቄዎችን ማንሳታቸው ታውቋል፡
በባህርዳር በአማራ ብድርና ቁጠባ የመሰብሰቢያ አዳራሽ የተካሄደውን ስብሰባ የመሩት አቶ ታዘባቸው ጣሴ ” ምርጫ 2007 በመድረሱ ነው ወይ ይህን ዝግጅት ያዘጋጃችሁት ?” ተብለው ሲጠየቁ፣ “አዎ”  የሚል መልስ በመስጠታቸው ተማሪዎች ከፍተኛ ተቃውሞና ጩኸት አሰምተዋል። አቶ ታዘባቸው ግን ኢህአዴግ በምርጫው አሸናፊ ለመሆን ሁሉንም መድረኮች እንደሚጠቀም ለተሰብሳቢው ገልጸዋል፡፡
ተማሪዎችም የመድረክ መሪውን ምላሽ ከሰሙ በኋላ ሌሎች ተቀናቃኝ ፓርቲዎች ያላገኙትን የቅስቀሳ ዕድል ገዢው ፓርቲ ስልጣን ላይ ስላለ ብቻ ሁሉንም የህብረተሰብ አካላት በማስገደድ አዳምጡኝ ማለቱ አግባብነት እንደሌለው ተናግረዋል።  ገዢው ፓርቲ እንደሌሎች ፓርቲዎች በሚዲያ በሚሰጠው የአየር ሰዓት ተጠቅሞ መቀስቀስ እያለበት ዛሬ ይህን ማድረጉ ስልጣንን ያለ አግባብ መጠቀም መሆኑን ተማሪዎች ተናግረዋል። በሰሞኑ ውይይት ከተዳሰሱ ጉዳዮች ውስጥ፤ ያለአግባብ በታሰሩ ጋዜጠኞች ዙሪያ በተነሳው ክርክር ጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙ በገዢው መንግስት ወንጀለኛ ተብላ ብትታሰርም በአለምአቀፍ ደረጃ ያሉ ድርጅቶች ግን ለሃገሯ በሰራችው በጎ ስራ መሸለሙ የእናንተን አካሄድ ስህተትነት ያሳያል፤

ተቀናቃኝ ፓርቲዎች ድምጻቸውን የሚያሰሙበትን ልዩ ልዩ ጋዜጦችና መጽሄቶች እንዲዘጉ ማድረጋችሁ በመምርጫ 2007 ላይ ተጽእኖ በማድረስ እንደ ምርጫ 2002 ብቸኛ ትወዳዳሪ ሆኖ ለመቅረብ አይመስልባችሁም ወይ ?
ከኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ይልቅ በኢሳት ቴሌቪዥን የሚቀርቡ መረጃዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ አሳማኝ እየሆኑ በመምጣትቸው ህብረተሰቡ በጉጉት ይከታተላቸዋል፡፡በእናንተ ሚዲየሞች
የሚቀርቡት ግን ልማታዊ በሚል ሽፋን ተመሳሳይ ይዘት አላቸው፡፡በመንግስት ባለስልጣናት የሚሰሩ የሙስናና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ህዝቡ እያወቀ ይፋ አታደርጉም፡፡ስለዚህ
የኢሳት መረጃ ሃሰት ነው ካላችሁ ለምን ማስተባበያ አታቀርቡም?
በየሶስት ኪሎሜትር ትምህርት ቤት አለ የሚል አሰልች ሪፖርት ሁሌ ቢቀርብም ምን ያህል በሰው ሃይል እና ግብአት የተሟሉ ሆነው ነው?መምህር ጠፍቶ እንዲሁ ውለው የሚመለሱ ተማሪዎች በየአካባቢያችን እየታዩ የትምህርት ቤት ቁጥር ለመናገር  ምን አሯሯጣችሁ?
በኢትዮጵያ ውስጥ አሁን 31 ዩንቨርስቲዎች አሉ ብትሉም የትኛው ዩንቨርስቲ ነው የተሟላ ግብአት ይዞ የሚሰራው?ከቅበላ አቅሙ በላይ ተማሪ ተሰጥቶት በቴሌቪዥን ክፍሎች ሳይቀር ተማሪ የሚያጉር ተቋም የለም ወይ? ምንም ላቦራቶር ሳየኖረው ተማሪን የሚያስተናግደው ሁሉ ለምን እንደ ዩኒቨርስቲ ትቆጥራላችሁ?ፖሊሲው ጥራት ያለው ትምህርት ለሁሉም ቢልም እናንተ ግን ቁጥር ላይ ማተኮራችሁ የትምህርቱን ዘርፍ በእቅድ እንዳልመራችሁት አያሳይም ወይ?
መንግስት የሃይማኖት እኩልነት አለ ቢልም የሙስሊም አስተምህሮት ያላቸውን ሲዲዎችና መጽሃፍት በመከልከል እምነቱን ጠብቆ የሚጓዘውን ህዝበ ሙስሊም አልሸባብ የሚል ቅጥያ በመስጠት የሰብአዊ መብት ረገጣ ለምን ያካሂዳል? የሚሉና የመሳሰሉትን ጥያቄዎች በድፍረት ሲያቀርቡ ተደምጠዋል፡፡ከመድረክ አካባቢ የሚሰጡ ምላሾች ግን አርኪ ባለመሆናቸው ተሰብሳቢዎች በፌዝና በሳቅ የታጀበ ምላሽ ሲሰጡ መዋላቸው ከተሳታፊዎች ተገልጾልናል፡፡
በጎንደር ዩኒቨርስቲ ከተነሱት ጥያቄዎች መካከል ደግሞ የፕሬስ ነጻነት አለ ወይ? ተመርቀን ስራ ለመያዝ የግድ አባል እንድንሆን ለምን ይጠበቃል? ለምን ሁሌ ጥሩ ጎናችሁን ብቻ
ትነግሩናላችሁ? መሬት እየሸጣችሁ አርሶ አደሩ ምን አርሶ ይበላል? ተቃዋሚዎች ለምን ከአገራቸው ይሳደዳሉ? አንድ ለአምስት አደረጃጀት ለምን አስፈለገ? እውን በኢትዮጵያ
ሰብአዊ መብት ይከበራል ወይ?  ተቃዋሚዎችን ለምን አሸባሪ እያላችሁ ትፈርጃላችሁ? ኢህአዴግ በመላ አገሪቱ ከተሞች ተሸንፎ እያለ ለምን ስልጣኑን አላስረከበም? እውን
በኢትዮፕያ ሰላም አለ ማለት ይቻላል? በከፍተኛ የአመራር ቦታዎች ላይ ብቻ ለምን የህወሃት ሰዎች ይገኛሉ? ታሪክን ለፖለቲካ መጠቀሚያ ለምን ታደርጉታላችሁ? አዲሲቱ
ኢትዮጵያ ማለት ለምን አስፈለገ?  የኢትዮጵያ መሬት ለምን ለሱዳን ተሰጠ? በኢትዮጵያ እና በኤርትራ ህዝቦች መካከል ጥላቻ እንዲፈጠር ለምን አደረጋችሁ? በእስር ቤት ውስጥ ያሉ ወገኖች ክትትል እያገኙ ነው ወይ? የሚሉና ሌሎችም ጥያቄዎች ተነስተዋል።
በተመሳሳይ ዜናም ኢህአዴግ ስልጠናውን ለሁሉም የመንግስት ሰራተኞች ለመስጠት እየተዘጋጀ ሲሆን፣ በኦሮምያ የሚገኙ መኮንኖችና መርማሪ ፖሊሶች በሻሸመኔ ስልጠና እየወሰዱ ነው።

No comments:

Post a Comment

wanted officials