Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Saturday, September 20, 2014

‹‹ስደት እናንተን አይመለከታችሁም ተብለናል›› መምህራን

• ‹‹ስደት እናንተን አይመለከታችሁም ተብለናል›› መምህራን
negereለመምህራን እየተሰጠ በሚገኘው የሰባት ቀናት ስልጠና መምህራን አሁንም ዝምታን መምረጣቸውን ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ ስልጠናው ላይ የሚገኙ መምህራን ዝምታውን የመረጡት የኢትዮጵያ መምህራን ድምጽ ይሰማ የተባለ አካል ከስልጠናው መልካም ነገር ስለማይገኝ መምህራኑ በስልጠናው ንቁ ተሳትፎ እንዳያደርጉና የገዥው ፓርቲ አባል የሆኑ መምህራንን እንዲያገልሉ መግለጹን ተከትሎ እንደሆነ ታውቋል፡፡
አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ደራርቱ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ስልጠናውን የሚወስዱ መምህራን ዝምታን የመረጡ ሲሆን በተለይ በትናንትናው ዕለት በስልጠናው ህዝብ ሲሰደብ ውሏል በሚል አንገባም ብለው እንደነበር ስልጣኞች ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ ‹‹በትናንትናው ስልጠና ኦሮሚያ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች የተገደሉ ተማሪዎች የተገደሉት በጠባብ አመለካከት መሆኑ እንዲሁም አማርኛ ተናጋሪው ህዝብም ትምክተኛ ነው በመባሉ ህዝብ ወደሚሰደብበት ስልጠና አንገባም›› ብለው እንደነበር አንድ ሰልጣኝ መምህር ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጾአል፡፡
መምህራኑ በስተመጨረሻ ወደ ስልጠናው ቢገቡም ጥያቄ ባለመጠየቅ ዝምታን በመምረጣቸው የኢህአዴግ አባላት እንዲጠይቁ እየተደረገ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ሰልጣኙ ‹‹መምህራን እንደሚያምጹ ስለታወቀ የኢህአዴግ አባላት ለዘጠኝ ቀናት ይህን አሁን የሚሰጠውን ስልጠና ሰልጥነዋል፡፡ በመሆኑም እነሱ ብቻ ናቸው ጥያቄና አስተያየት እያቀረቡ የሚገኙት›› ሲል ገልጾአል፡፡
በሌላ በኩል መምህራን ዝምታን በመምረጣቸው በጥቆማ ‹‹ለምን አትጠይቁም?›› እየተባሉ እንደሚገደዱና ተገደው የሚጠይቁትን ጥያቄም ሰልጣኞች ሊመለስላቸው እንዳልተቻለ ሰልጣኞቹ ገልጸዋል፡፡ የአቃቂ ሰልጣኞች ‹‹በደርግ ዘመን የፖለቲካ ሰደተኛ ብቻ ነበር የነበረው፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን የኢትዮጵያ ህዝብ የኢኮኖሚና የፖለቲከኛ ስደተኛ እየሆነ ነው፡፡ ይህ ለምን ሆነ?›› የሚል ጥያቄ የተነሳ ሲሆን ‹‹ይህ የትምክት ጥያቄ ነው!›› የሚል በኃይለ ቃል የተሞላ መልስ እንደተሰጣቸው ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል የየካ ክፍለ ከተማ ሰልጣኞች የተለያዩ ጥያቄዎችን ቢያነሱም መልስ እንዳልተሰጣቸው ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጸዋል፡፡ መምህራኑ ‹‹ሙስና ተስፋፍቷል፣ ልማት የምትሉት የቆሙ ህንጻዎች ከሆነ ልማት የለም፣ አርሶ አደሩ ጋር መሰረታዊ ለውጥ የለም፣ የመምህራን ችግር ሰሚ አጥቷል›› የሚሉ አስተያየቶችና ጥያቄዎች የተሰነዘሩ ሲሆን አብዛኛዎቹ መልስ እንዳልተሰጣቸው ገልጸዋል፡፡ ሰልጣኞቹ ስለ ስደት በጠየቁበት ወቅትም ‹‹እናንተ መምህራን ናችሁ፡፡ ስደት አይመለከታችሁም፤ እናንተን አያሳስባችሁም፡፡›› የሚል መልስ እንደተሰጣቸው ገልጸዋል፡፡
Source : negere Ethiopia

No comments:

Post a Comment

wanted officials