“ሕወሀት ኢሕአዴግ” በቅርብ ጊዜ የብሔራዊ እርቅ ተማጻኝ!
ብሔራዊ እርቅ (National Reconciliation) በተለይ በእርስ በእርስ ግጭት ደም የተቃባንና የከፋ አደጋ የተጋረጠበትን ኅብረተሰብ ወይም የመበታተን አደጋ የተጋረጠባትን ሀገር በይቅር ለእግዚአብሔር ይቅር አባብሎ ሰላም ለማውረድና የቂም በቀልን ዶሴ ዘግቶ በአዲስ መንፈስ ብሔራዊ መግባባትን (National Consensus) ፈጥሮ የአንዲት ሀገርን ሕዝብ በአንድነት አስተባብሮ ለማንቀሳቀስና ህልውናውን ከመረጋጋቱ ጋራ ለማስቀጠል ዓይነተኛ መንገድ ነው፡፡
በሕወሀት ኢሕአዴግ የአገዛዝ ዘመን የዚህ የብሔራዊ እርቅ (National Reconciliation) ጥያቄ በተለያዩ አካላት በተደጋጋሚ ሲቀርብ ቆይቷል፡፡ ነገር ግን የአገዛዝ ሥርዓቱ ይህ እርቅ ቢፈጸም የመጀመሪያውና ዋነኛው ተጠቃሚ እሱ መሆኑን እስከአሁንም ቢሆን መረዳት ባለመቻሉ ምክንያት የተለያዩ የእብሪት ኃይለ ቃሎችን በመሰንዘር ከተለያዩ ወገኖች ለሚቀርብለት ጥያቄ ቀና ምላሽ መስጠት ሳይችል ቀርቷል፡፡ የዚህም ምክንያቱ አንደኛ የሥርዓቱ ባለሥልጣናት የሌላው ጉድፍ እንጅ የራሳቸው ግንድ ስላልታያቸው ሲሆን ሌላኛው ደግሞ ቀኑ ለእነሱ “ሁልጊዜም ፋሲካ” እንደሆነላቸው የሚኖርና አይቀሬው ነገር ማለትም ቀን ተለውጦ ትላንት በሌላው እጅ የነበረው ዛሬ በእነሱ እጅ ያለው ነገ ደግሞ በሌላው እጅ እንደሚገባ ያለመረዳትና ዘለዓለም በእነሱ እጅ የሚኖር ስለመሰላቸው የፈጠረባቸው መዘናጋት ናቸው፡፡
በእኔ እምነት ይህ ትንሽዬ አገዛዝ የቀረበለትን ወርቃማ እድል ሊጠቀምበት ሳይችል ቀርቶ በማባከኑ ከጉዳዩ ተጠቃሚ ሊሆን የሚችልበትን እድል ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዳመለጠው አስባለሁ፡፡ አርቀው ማሰብ ቢችሉ ወይም የያዙትን የኃላፊነት ቦታ የሚመጥን ጭንቅላት ቢኖራቸውና ነገ ሌላ ቀን ነው ብለው ጥያቄውን በቀናነት ተቀብለው አስተናግደውት ቢሆን ኖሮ ለሁሉም መልካም ተአማኒ ሰላም ለሀገርም የጸና መሠረት ያለውና ትክክለኛ የዲሞክራሲ (የበይነ-ሕዝብ) ሥርዓት ለመመሥረት በተቻለ ነበር፡፡
ይህ እድል በወያኔም ባይሆን በሌላ ለሀገሪቱና ለሕዝቧ እንደሚኖር አትጠራጠሩ፡፡ ለወያኔ ግን ኃጢአቱን ሊያሥተሰርይለትና በኢትዮጵያ ታሪክ መልካም ስም ሊያሰጠው የሚችለውን መልካም ታሪክ ሠርቶ ማለፍ የሚችልበት ቀን አለፈ፡፡ እስከዛሬ ይህ ትንሽዬ አገዛዝ ተለማኝ ሌሎች ወገኖች ማለትም የሲቢክ (ሕዝባዊ) ማኅበራትና ፖለቲካዊ (እምነተ-አሥተዳደራዊ) ማኅበራት ደግሞ ለማኝ ነበሩ፡፡ እመኑኝ አትጠራጠሩ ከዚህ በኋላ ግን ለማኙ ወያኔ ተለማኙ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይሆናል፡፡ አዲሱን ዓመት 2007ዓ.ምን ጨምሮ ቀጣዩ ዓመት ለወያኔ ጭንቅና ጥብ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ደግሞ ተስፋን ይዘው መጥተዋል፡፡
ከዚህም የተነሣ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ወያኔ ይሄንን ብሔራዊ እርቅ እሱ በሚመቸው መንገድ አጠናቆ ከጉድ ከውርደትና ሞት ለመዳን የሚችልበትን ስልት በመንደፍና ጭንቅ በገጠመው ቁጥር እየሰበሰበ የሚያሠማራቸውን ከጭንቁ የሚታደጉትን “የሀገር ሽማግሌ” ተብየዎችን ቀሳጢ ጉዳይ አስፈጻሚዎች በማሠማራት ውትወታውን እንደሚያጧጡፈው “ምናለ አምሳሉ በሉኝ” ጠብቁ፡፡ በእኔ እምነት ሕወሀት ኢሕአዴግ ይሄንን ታላቅ ብሔራዊ ቁምነገር መከወን የሚችልበት አቅም ትከሻ ቅድስናና ሰብእና ቅንጣቱ እንኳን የለውም፡፡ በሕወሀት ኢሕአዴግ ከዋኝነት አስተናጋጅነት ኃላፊነት ኢትዮጵያ ውስጥ ሊመጣ ሊገኝ የሚችል መሠረት ያለው እውነተኛና ትክክለኛ ሰላምና እርቅ አይኖርም፡፡ ምክንያቱም አንዴ ሁለቴ ሦስቴ ብቻም አይደል ለቁጥር ለሚያዳግት ጊዜ መንግሥት ነኝ ከሚል አካል ፈጽሞ በማይጠበቅ ነውረኛነት ብልግና እብለትና ክህደት ማጭበርበር ማወናበድም የኢትዮጵያ ሕዝብ በተደጋጋሚ ጊዜያት ስለተካደና ስለተሞኘ ስለተወናበደና ስለተጭበረበረ ወያኔ መታመንን መልሶ ላያገኘው አጥቶታልና ብቻ ሳይሆን ወያኔ ይሄንን ማድረግ የሚችልበት ተፈጥሮ ወይም ሰብእና እንደሌለው ሕዝቡ በሚገባ ያውቃልና ነው፡፡
አሁንም እርግጠኛ ነኝ ወያኔ ይሄንን አስመሳይ እንቅስቃሴ በሚጀምርበት ጊዜ በተቃውሞና በፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥ ያሉ የሥልጣን ጥማት ያስቸገራቸው ዜጎች በአገዛዙ በመደለል የእንቅስቃሴው አባሪ ተባባሪ ሆነው በመራኮት በሀገርና በሕዝብ ዘላቂ ጥቅም ላይ ከባድ ስሕተትና በደል የሚፈጽሙ ግለሰቦችና ቡድኖች እንደሚኖሩ አትጠራጠሩ፡፡ ምን አለፋቹህ የምታዩት ታላቅ ድራማ ይኖራል፡፡ ከዚህ በኋላ ከምሁራንም በሉ ከፖለቲከኞች እንዲሁም ከሀገር ሽማግሌዎች ባጠቃላይ ከሀገሪቱ ልኂቃን የብሔራዊ እርቅን ጥያቄ ለወያኔ አቀረቡ የሚባሉ ዜጎች ቢኖሩ ያለውንና የነበረውን የተፈጠረውንና የሚፈጠረውን ሁሉ ጨርሰው የማያውቁ ያልተረዱና የማይረዱ የዋሀን እንደሆኑ ልነግራቸው እወዳለሁ፡፡
ይሄንን ሐሳብ ያለ ምንም ግላዊና ከሀገር ጥቅም ጋር ከማይቃረን ምክንያት ከቀናነት ብቻ የሚያስቡ ዜጎች ካሉ እንደምኞታቸው ቢሆን ምንኛ መልካም በሆነ ነበር፡፡ ያለው ሀቅ ግን ከሚያስቡት እጅግ የራቀና የተለየ ነው፡፡ የሥርዓቱ ባለሥልጣናት በብዙ ቢሊዮን (ብልፍ) የሚቆጠረውን ከሀገሪቱ የመዘበሩትን ገንዘብ ቢመልሱም እንኳ፣ ለሀገር ለወገን በተቆጩ የዜግነት ግዴታቸውን ለመወጣት በታተሩ እየታፈኑ ተወስደውባቸው ልጆቻቸው ወላጆቻቸው በግፍ ተገለውባቸው ለመቅበር እንዲችሉ አይደለም ሞታቸውን እንኳን እንዳያውቁ ተደርገው እርማቸውን እንዲበሉ የተደረጉ ወገኖችን “ግድ የላቹህም ከሁሉም ነገር ሀገር ትበልጣለችና ስለ ሀገር ብላቹህ ይቅር በሉ” ብለን ማሰመን ብንችልም እንኳ፣ “በገደሉኝ በተሻለኝ” የሚያሰኙ ግፍና በደል የተፈጸመባቸውን ወገኖችንም እንደዚያው ማሳመን ብንችልም እንኳ፤ ሀገር ይቅር የማትለው ለይቅርታ የማይመች በርካታ የሀገር ክህደት ወንጀሎች አሉና ይህ የብሔራዊ እርቅ ሐሳብ ከወያኔ ጋራ ምንም የሚሆን አይደለም፡፡ በወያኔ የተደለሉ የተወሰኑ ወገኖች ተወናብደውና አወናብደው እንዲሆን ቢያደርጉ ግን ሀገሪቱ በኢፍትሐዊ መንገድ በወያኔ ያጣቻቸውን ብሔራዊ ጥቅሞቿን የኢትዮጵያ ሕዝብ ቀን በወጣለት ጊዜ ሥልጣንን በእጁ ባደረገ ጊዜ እንዲመለሱለት ጥያቄ የማቅረብና ማስመለስ የሚችልበትን መብት እንዲያጣ ያደርገዋልና ከወያኔ ጋራ በዚህ መልኩ መሸኛኘት የማይታሰብ ነው፡፡
በየዋህነት እንደሚያስቡት ወገኖች በወያኔ እጅ ይሄ ቢፈጸም በኋላ ላይ ለማይወጣላቸው ጸጸት እንደሚዳረጉ ነገሩ እርግጥ ነውና ከወዲሁ መጠቀሚያ ከመሆን እንዲቆጠቡ ማስገንዘብ እወዳለሁ፡፡ ለነገሩ የፈለገውን ያህል ቢባል በተለያዩ መሥሪያ ቤቶች በወያኔ ተሹመው እያገለገሉ እንደምናያቸው የትምህርታቸውንና የእድሜያቸውን ያህል የማያስቡ እንደ እንስሳ ያለ ሆዳቸው ምንም ነገር የማይታያቸው፤ ካለባቸው የአድር ባይነት ርካሽና ወራዳ ሰብእናቸው የተነሣ የዐፄ ኃይለሥላሴን የደርግን አሁንም ደግሞ የወያኔን ሥርዓት ወይም ደግሞ ደርግን ሲያገለግሉ ቆይተው አሁን ደግሞ የወያኔ ሹመኛ ሆነው ያለ አንዳች የአቋም ችግር እንደሚያገለግሉት ሆዳቸው አምላካቸው ክብራቸው በነውራቸው የሆኑ ግልሰቦችን እንደባዶ ብርጭቆ የሞሉባቸውን ሁሉ የሚሞሉ፣ በዚህ ርካሽና ወራዳ ማንነታቸውም ከሰው ፊት ሲቀርቡ ቅንጣትም እንኳን ሐፍረትና መሸማቀቅ የማይታይባቸውን ግለሰቦች አግኝቶ መንቀሳቀሱ አይቀርም፡፡ ምን ቢሠራ ምን ቢያደርግ ግን የሕዝብ አመኔታን አያገኝም እንጅ፡፡
ነገር ግን አገዛዙ የኢትዮጵያ ሕዝብ አንቅሮ እንደተፋው አውቆ ምንም ቢያደርግ ተአማኒነት አግኝቶ ተጠቃሚ በሚሆንበት መንገድ የሚያደርገውን አስመሳይ ብሔራዊ እርቅ (National Reconciliation) መከወን እንደማይችል ከተረዳ ግን ጡንቻው ሊያቆየው እስከቻለለት ጊዜ ድረስ እየተንገታገተ ይቆይና የፍጻሜው ሰዓቱ ሲደርስ በየመቀመጫችን የቀበረብንን የዘርና የሃይማኖት የሰዓት ፈንጅዎች (Time Bombs) በማፈንዳትና ሀገሪቱን በማፈራረስ ለፍርድ የሚያቀርብ ጠያቂና ከሳሽ አካል እንዳይኖርበት ለማድረግ እንደሚሞክር ካላቸውና ከምናውቀው “ከእኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” ተፈጥሯቸውና ከእስከዛሬው ፀረ ኢትዮጵያ ሸራቸው በመነሣት መረዳት ይቻላል፡፡ ወያኔ ሁለቴና ሦስቴ አይደለም ሽህ ጊዜ እንኳን በምርጫ ቢሸነፍም ተሸንፌያለሁ ብሎ ሥልጣን የማያስረክብበትም ዋነኛው ምክንያት ይሄ ነው፡፡ ሥልጣን በለቀቀ ማግሥት በፈጸመው ግፍ፣ ሙስና፣ ወንጀልና የሀገር ክህደት ሁሉ እየታነቀ ለፍርድ እንደሚቀርም አሳምሮ ስለሚያውቅ፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዚህ ወያኔ ከደገሰበት የጥፋት ድግስ አንጻር ሊጠነቀቃቸው የሚገቡ በርካታ ጉዳዮች ቢኖሩም ይህ የወያኔ ሀገሪቱን አፈራርሶ የመጥፋት ሰይጣናዊ ተግባር እውን ይሆናል ብሎ ግን ቅንጣት ታክል እንኳን እንዳይጠራጠርና ሥጋት እንዳያድርበት ማስገንዘብ እወዳለሁ፡፡ ይህች ሀገር መቸም ጊዜ ቢሆን ባላት የሠራዊት ብዛትና ኃይል ብቻ በመመካት ከጥፋት የዳነችበት ወይም የተረፈችበት ዘመን ኖሮ አያውቅም፡፡ ይልቁንም በየበረሀው በየገዳሙ በየዋሻው በየፍርኩታው በየበዓታቸው ጤዛ ልሰው ቅጠል ቀምሰው ዳዋ ጥሰው ድንጋይ ተንተርሰው ግርምዓ ሌሊቱን ፀብአ አጋንንቱን ታግሰው በአስጨናቂ ጾም ጸሎት ሥግደትና የተለያዩ የመከራ ትሩፋት ስለ ተወዳጅ ሀገራቸውና ሕዝባቸው መከራ በመቀበል በሚያለቅሱት በቅዱሳኖቿ ጸሎትና ምልጃ እንጅ፡፡ ይሄንን ያህልም የተፈተነውና መከራ እያየን ያለነውም የእነሱን ጸሎት ፈጣሪ ስላልሰማ ወይም ስለማይሰማ አይደለም፡፡
የዚህ ምክንያት መጽሐፍ ቅዱስ ላይ በዕብ. 12፤5-11 ላይ ይገኛል “ልጀ ሆይ የጌታን ቅጣት አታቃልል በሚገሥጽህም ጊዜ አትድከም ጌታ የሚወደውን ይቀጣዋልና የሚቀበለውንም ልጅ ሁሉ ይገርፈዋል፡፡ ብሎ የሚነጋገረውን ምክር ረስታቹሀል፡፡ ለመቀጣት ታገሡ እግዚአብሔር እንደ ልጆች ያደርጋቹሀልና፡፡ አባቱ የማይቀጣው ልጅ ማን ነው? ነገር ግን ሁሉ የቅጣት ተካፋይ ሆኗልና ያለ ቅጣት ብትኖሩ ዲቃሎች እንጅ ልጆች አይደላቹህም፡፡ ከዚህም በላይ የቀጡን የሥጋ አባቶች ነበሩን እናፍራቸውም ነበር እንዴትስ ይልቅ ለመናፍስት አባት አብልጠን ልንገዛና በሕይዎት ልንኖር በተገባን? እነሱ መልካም ሆኖ እንደታያቸው ለጥቂት ቀን ይቀጡን ነበርና እርሱ ግን ከቅድስናው እንድንካፈል ለጥቅማችን ይቀጣናል፡፡ ቅጣት ሁሉ ለጊዜው የሚያሳዝን እንጅ ደስ የሚያሰኝ አይመስልም ዳሩ ግን በኋላ ለለመዱት የሰላምን ፍሬ እርሱም ጽድቅን ያፈራላቸዋል” ይላል ቃሉ፡፡ “የእስራኤል ልጆች ሆይ! እናንተ ለእኔ እንደ ኢትዮጵያ ልጆች አይደላቹህምን? ይላል እግዚአብሔር” ትን. አሞ. 9፤7 በመሆኑም እኛ ኢትዮጵያዊያን ልጆች እንጅ ዲቃሎች አይደለንምና ምንም ቢበድሉ የቱንም ያህል ቢረክሱ ቢያምፁበትም ምንም እንደማይላቸው እንደ ሌሎች ሀገራትና ሕዝቦች ዝም አይለንም እሽ እስክንልና እስክንመለስ ድረስ ይቀጣናል፡፡
ትናንትና በቅዱሳኖቿ ጸሎትና ልመና እንደሚመጣባትና እንደሚደርስባት የፈተናና የመከራ ክብደትና ብዛት ሳያደርግባት እንደአመጣጡ እየመለሰ ከብዙ መከራና ጥፋት የታደጋት አምላክ ዛሬም አለ፡፡ በእርግጥ ቃሉ “እሽ ብትሉ ለኔም ብትታዘዙ የምድርን በረከት ትበላላቹህ እንቢ ብትሉ ግን ብታምፁም ሰይፍ ይበላቹሀል” ትን.ኢሳ. 1፤19-20 እንዳለው ይህ ሁሉ ጉድ የመጣብንና የተሰበርነው እንቢ በማለታችን መሆኑን ሁሉም እያንዳንዱ ወደሌላው ሳይሆን ወደ ራሱ ወደ ውስጡ በመመልከት ምን ያህል እንዳመፅን እንደረከስን እንደበደልን ከውስጡ ከሚያገኘው መልስ የሚረዳው ነገር ቢሆንም ምን ብንበድለው ምን ብናሳዝነው እንዲህ ወያኔ ላሰበብን ለደገሰብን ዓይነት ጥፋት አሳልፎ ይሰጠናል ብላቹህ ቅንጣት ታክል እንኳን እንዳትሠጉ፡፡ “እመኑ እንጂ አትፍሩ”
ከዚህ በኋላ የኢትዮጵያ ሕዝብ በእግዚአብሔር ቸርነትና በራሱ በልጆቹ ጥረት ቀድሞ በመንቃት ከጫፍ እስከ ጫፍ ወያኔ የተከለብንን የዘርና የሃይማኖት ፈንጅዎቹን በማምከን ሌሎች እሾሆቻችንም በመንቀል በአዲስ መንፈስ እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ እንደ አንድ ልብ መካሪ ሆኖ በመነሣት ከጥፋት ይድናል የሚል የጸና እምነት አለኝ፡፡ ለወያኔ የምንሰጠው ወይም የማንነፍገው ነገር ቢኖር ፍትሕና ሕትህ ብቻ ነው፡፡ ሁሉም የዘራውን ማጨዱ ግድ ነው፡፡ ቃሉም እንደሚል “ሰው የሚዘራውን ሁሉ ያንኑ ደግሞ ያጭዳልና” ገላ 6፤7 ፡፡ እናም በብዙ ነገር የቆሰለውን የደማውን ያመረቀዘውን የሀገር አንጀት የሚያጠግገው ቂም በቀልን የሚሽረው ፍትሕ ብቻ ነው፡፡ ለዚህች ከቅርብ እርቀት ላለች ትንሣኤያችንን ለምታረጋግጠው ብሩህ ቀናችንም ታጋዩ አርበኛው ወታደሩም በጽናት ይታገል፣ ሁሉም ዓይነት ሠራተኛ በትጋት ይሥራ፣ ገበሬውም በብርታት ይረስ፣ ካህኑም በንጽሕና ይጸልይ ይቀድስ፣ እናቶችም ያለ እረፍት ይማለሉ፣ ሁሉም ዜጋ እጁ ላይ ባለው ነገር ሁሉ የመጨረሻ ይበርታ፡፡
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
source: goolgule
No comments:
Post a Comment