Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Saturday, September 6, 2014

የኢትዮጵያውያን ስደተኞች መበራከት DW

የኢትዮጵያውያን ስደተኞች መበራከት
መንግሥት በአንዳንድ የግል ጋዜጦች ላይ ክስ ከመሠረተ እና ባለፈው ግንቦትም ዘጠኝ ጋዜጠኞች እና የድረ ገፅ አምደኞች ከታሰሩ ወዲህ ቁጥራቸው ትንሽ የማይባል ጋዜጠኞች ኢትዮጵያን ለቀው ወጥተዋል።
ባለፉት ጊዚያት ሀገር እየለቀቁ የወጡት ግን ጋዜጠኞች ብቻ አይደሉም፣ ብዙ ወጣቶችም በተለያዩ መንገዶች መሰደዳቸውን የመገናኛ ብዙኃን ዘገባዎች ያሳያሉ። ለጋዜጠኞች ደህንነት የሚሟገተው ድርጅት፣ የ«ሲ ፒ ጄይ» የምሥራቅ አፍሪቃ ተጠሪ ቶም ሮድስ፣ ኢትዮጵያውያን ሕይወታቸውን ለአደጋ እያጋለጡ የሚወጡበት ጉዳይ ከሰብዓዊ መብት ጋ የተያያዘ ነው ይላሉ።
ብዙ ወጣት ኢትዮጵያውያን በየመን ፣ በኬንያ እና ታንዛንያ፣ እንዲሁም በሱዳን እና በሊቢያ በኩል እያደረጉ አደገኛ በሆነ ጉዞ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ፣ ደቡባዊ አፍሪቃ እና አውሮጳ ለመግባት ይሞክራሉ፣ በዚሁ ሙከራቸው ወቅት በየበረሃው እና በየጫካው ወድቀው የሚቀሩት እና ባህር የሚበላቸው ጥቂቶች እንዳልሆኑ እና የሕገ ወጥ ሰው አሸጋጋሪዎች ሰለባም እንደሚሆኑ በየጊዜው የዜና ምንጮች የሚያወጡዋቸው ዘገባዎች ያሳያሉ፣ ከጥቂት ጊዜ በፊት በዚምባብዌ በኩል አድርገው ደቡብ አፍሪቃ የገቡ 24 ኢትዮጵያውያን የመኖሪያ ፈቃድ ስላልነበራቸው በሀገሪቱ ፖሊስ መያዛቸው የሚታወስ ነው። ኢትዮጵያውያኑ ራሳቸውን ለዚህ ሁሉ መከራ የሚያጋልጡበት የተለያዩ ምክንያቶች መኖራቸውን ለጋዜጠኞች ደህንነት የሚሟገተው ድርጅት፣ «ሲ ፒ ጄይ» የምሥራቅ አፍሪቃ ተጠሪ ቶም ሮድስ ገልጸዋል።
« ሁለት ዋነኛ ምክንያቶች ያሉ ይመስለኛል። የመጀመሪያው፣ መንግሥት ማንኛውንም ትችት ወይም ተቃውሞ በቸልታ የማለፍ ልማዱም ሆነ አሰራር በፍፁም የለውም። እና ከማንኛውም ትችት የሚሰነዝር ቡድን ጋ የሆነ ግንኙነት ካለህ፣ ምንም እንኳን ግንኙነቱ ደካማ ቢሆንም፣ የመንግሥት ክትትል ዒላማ ልትሆን ትችላለህ። ሁለተኛው ደግሞ፣ የፍትሑ አውታር በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ነው ፣ እና አንዴ በመንግሥት ክስ ከቀረበብህ ወደ ወህኒ መውረድህ የማይቀር ነው፣ ስለዚህ ብዙዎቹ የረጅም ዓመታት የእስራት ቅጣት እንዳይደርስባቸው መሸሹን መርጠዋል። »
Tom Rhodes
የ«ሲ ፒ ጄይ» ቶም ሮድስ
ለብዙዎች ሀገር እየለቀቁ መውጣት ከሀገሪቱ የሰብዓዊ መብት ይዞታ ጋር የተያያዘ ጉዳይ መሆኑን የገለጹት ቶም ሮድስ በሚቀጥለው ዓመት በሀገሪቱ የሚካሄደው ምርጫ ማበርከቱንም ቶም ሮድስ ይናገራሉ።
« ምርጫ በሚቀጥለው ዓመት ግንቦት ወር ይደረጋል። ይህም፣ ምንጮች እንደነገሩኝ፣ በመንግሥቱ ውስጥ ያሉት ፣ ሥልጣን እንደያዙ ለመቆየቱ ስለሚፈልጉ፣ ሊነሳ የሚችል ማንኛውንም ትችት ለማፈን እየሞከሩ ነው። ተመሳሳይ ሁኔታ ካሁን ቀደም አይተናል። እአአ በ2005 ዓም ተቃዋሚው ወገን ምርጫውን ሳያሸንፍ አልቀረበትም የተባለው ምርጫ ውጤት ክርክር ባስነሳበት ጊዜ ተመሳሳይ ሁኔታ ተመልክተናል። እና ከዚያን ጊዜ ወዲህ እምነት ያጣው መንግሥት፣ በሥልጣን ለመቆየት ሲል ጋዜጠኞችን ብቻ ሳይሆን የሲቭል መብት ተሟጋችቾችን እና ጠበቆችንም ጭምር ለመምታት ወደኋላ አላለም። »
ቶም ሮድስ፣ ጋዜጠኞች እና ብዙ ወጣቶችን ከስደት እና በሰበቡ ከሚደርስባቸው መከራ እና ስቃይ ለመታደግ የኢትዮጵያ መንግሥት ፖሊሲውን ሊከልሰው ይገባል ባይ ናቸው።
«መንግሥት አንዳንድ ፣ ለምሳሌ፣ እአአ በ2009 ዓም የወጣውን የፀረ ሽብርን የመሳሰሉትን ሕጎች ዳግም ማጤን ይኖርበታል። ፖሊሲውን በጥሞና ስንመለከተው፣ በሀገሪቱ የሕግ ሥርዓት ውስጥ ፍትሓዊ አሰራር የተጓደለበት ሁኔታ ሰዎች በሕጉ ሥርዓት ላይ እምነት እንዳያድርባቸው አድርጓል። ይህ ባይሆን ኖሮ ብዙ ሰው ሀገር እየለቀቀ ሲሸስ ባልታየ ነበር። እርግጥ፣ ጉዳዩ የተወሳሰበ ነው። የሀገሪቱ መንግሥት ልማትን በተመለከት ጉልህ መሻሻል አድርጓል። በዚህም የተነሳ በኤኮኖሚ ምክንያት መውጣት የሚገደዱት ኢትዮጵያውያን በጣም ትንሽ ነው። ይሁንና፣ የልማቱ እንቅስቃሴ የሚደረገው ለሰብዓዊ መብት መከበር ትኩረት ሳይሰጥ ነው። ይህም ሰዎች ሀገራቸውን እንዲወጡ ያስገድዳል። መንግሥት የሚሰራበት የመሬት መቀራመትን ፖሊሲ ምን ያህል ብዙ ወጣቶችን እንደሚነካ መመልከት ይበቃል። »
Zeitungen Äthiopien
የኢትዮጵያ መንግሥት የሰብዓዊ መብቱን ይዞታ እንዲያሻሽል እና የፕሬስ ነፃነትን እንዲያከብር ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጫና ሊያሳርፍ እንደሚገባ ድርጅታቸው በተደጋጋሚ ቢያሳስብም፣ እስካሁን ይህ ነው የሚባል የረባ ውጤት ሊያስገኝ የሚችል ግፊት ባለማሰረፉ ቶም ሮድስ አልተደሰቱም።
« በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አሰራር ብዙ ጊዜ ቅር ተሰኝቼአለሁ። ምክንያቱም የሚናገሩት እና የሚያደርጉት የተለያየ ነውና። እና ለምሳሌ ዩኤስ አሜሪካ እና ብሪታንያን የመሳሰሉ ዓበይት ለጋሽ ሀገራት ለኢትዮጵያ ሊያቀርቡት ያቀዱትን ግዙፍ ርዳታ፣ የሰብዓዊ መብት ይዞታን ከግንዛቤ ሳያስገቡ ሊሰጡ አይገባም። »
አርያም ተክሌ
ነጋሽ መሀመድ

No comments:

Post a Comment

wanted officials