Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Tuesday, September 9, 2014

የአርምሞ ዘመን ውጣ፣ የመናገር ዘመን ግባ!

የአርምሞ ዘመን ውጣ፣ የመናገር ዘመን ግባ! (በላይ ማናዬ)

  • 2
    Share
በላይ ማናዬ
2006 ዓ.ም የአርምሞ፣ የዝምታ አመት ሆኖ አልፏል፡፡ ህዝብ እየተበደለ ዝምታን የመረጠበት አመት ማለት 2006 ነበር፡፡ ግድያ ነበር፤ ግን በዝምታ ታልፏል፡፡ መፈናቀል ነበር፤ ግን በዝምታ ታልፏል፡፡ እስራቱም፣ ግርፋቱም፣ ስደቱም፣ እንግልቱም ህዝብ በአርምሞ ያሳለፋቸው በደሎች ነበሩ፤ ናቸውም፡፡ የሚያነበው መጽሔትና ጋዜጣ ሲከረቸም መልሱ ዝምታ ነበር፤ ነው! የአርምሞ ዘመን፣ የዝምታ አመት!
አሁን ይህ አመት ተሸኘ፡፡ እንኳንም ተሸኘ፤ (ምናልባት የዘመን ኩርፊያ ይዞን ከነበረ ቢለቀን)፡፡ ግን የዝምታችን ምንጭ ምንድን ነው? ምን ሆነን ነው ግን?

ከስድስት ኪሎ ወደ ካዛንቺስ የሚያደርሰኝን ታክሲ በረዥሙ ሰልፍ ውስጥ ራሴን ጨምሬ ለረጅም ጊዜያት ከጠበኩ በኋላ ታክሲ ውስጥ ገብቼ ከኋላ ወንበር ላይ ከሌሎች ሶስት ሰዎች ጋር ወንበሮችን ተጋርቼ ተቀምጫለሁ፡፡ ከኋላ ወንበር ላይ ከተቀመጥነው አራት ሰዎች መካከል አንዱ በእድሜ የገፉ የደስ ደስ ያላቸው ሽማግሌ ነበሩ፡፡ ሽማግሌው አሁንም አሁንም ግራ ቀኝ ዞር ዞር እያሉ ያያሉ፡፡ በአንድ ሁሉም ወንበሮች በሰው በተሞሉ ታክሲ ውስጥ አንድም ሰው ትንፍሽ ሲል አይደመጥም፡፡ ሁሉም በአርምሞ በየራሱ ሀሳብ የተዋጠ ይመስላል፡፡
የታክሲ ሹፌሩ ረዳት እንኳ ሂሳብ ለመሰብሰብ ድምጹን አያሰማም፡፡ በፊቱ እንቅስቃሴ ብቻ ሂሳብ ይለቅማል፡፡ ሽማግሌው አሁንም አሁንም ዞር ዞር ይላሉ፡፡ ግን ማንም ልብ ያላቸው አይመስልም፡፡ ዝምታ ብቻ! ሽማግሌው ድንገት ወደ እኔ ዞር ብለው፣ ‹‹ምን አይነት ዘመን ላይ ደረስን!›› አሉኝ፡፡ እኔም ግንባሬን ፈታ ለማድረግ ከመሞከር በቀር ምንም ሳልመልስላቸው ዝም አልኳቸው፡፡
‹‹ሰው አንደበቱን ምን ነካው!?›› አሉ አሁንም ወደ እኔ ዞረው፡፡
‹‹እንዴት?›› አልኳቸው፡፡
‹‹ተመልከት እስኪ…እዚህ ታክሲ ውስጥ ስንት ሰዎች አለን?…ብዙ ነን…አይደለም?››
‹‹አዎ››
‹‹ታዲያ የአንድ ሀገር ልጆችም አይደለን እንዴ! የሚነጋገርም ሰው የለም…አንደበታችንን ማን ዘጋው? የእናንተ የወጣቶቹ ደግሞ ይግረም!››
እውነት ግን አንደበታችንን ማን ዘጋው? አብረን እያለን እንኳ አብረን የማንሆነው ምን ብንሆን ነው? ስንደሰትም ሆነ ስንከፋ አብሮነት አልነበረንም እንዴ? ታክሲ ውስጥ እንዳናወራ፣ አንደበታችን እንዳይከፈት ያደረገን ምንድን ነው?
ተሰለፉ ስንባል መሰለፍ ብቻ! ተንቀሳቀሱ ስንባል እሺ! ተጠጋ ስንባል እሺ! ቤታችንን ሲያፈርሱ ዝምታ፣ ገንዘብ አምጡ ስንባል እሺ፣…ያለንን ሲወስዱብን ለምን የማንል ምን ሆነን ነው? ዝምታ ብቻ ለምን? የአርምሞ ዘመን!
እስኪ የአርምሞ ዘመን ውጣ፣ የመናገር ዘመን ግባ እንበል! 2007 ዓ.ም ሲገባ ከዚህ የአርምሞ ድብታችን መላቀቅ ግድ ይለናል፡፡ ዘመኑን አዲስ እንዲሆን የምናደርገው ከአሮጌው አስተሳሰባችን ስንላቀቅና ለለውጥ ዝግጁ ስንሆን ነው፡፡ ዘመን እንደሆነ ያው ዘመን ነው፤ ጉዳዩ ያለው ከሰዎች የአስተሳሰብ ለውጥ ላይ ነው፡፡ በመጪው አመት ግፍ በቃ የምንልበት አመት ሊሆን ይገባል፡፡ 2007 የለውጥ አመት ይሁንልን!

- See more at: http://satenaw.com/amharic/?p=1591#sthash.AXDuhdoV.dpuf

No comments:

Post a Comment

wanted officials