የአቶ ተፈራ ዋልዋ ባለቤት በጥፊ ተመተዋል
የአቶ ተፈራ ዋልዋ ባለቤትና የአንዳርጋቸው ፅጌ እህት የሆኑት ወ/ሮ አይኔ ፅጌ ወላጅ አባታቸው ለመጠየቅ ወደ ማዕከላዊ ሄደው በግርማይ ማንጁስ በጥፊ መመታታቸውን በስፍራው የነበረ ከፍተኛ የህወሀት ደህንነት አባልአጋለጠ። ከአራት አመት በፊት ከግንቦት ሰባት ጋር በተያያዘ በማዕከላዊ ታስረው የነበሩት ወላጅ አባት አቶ ፅጌን ለመጠየቅ የሄዱት ወ/ሮ አይኔ የያዙትን ስንቅ ለማቀበልና ህጉ በሚፈቅደው መሰረት ወላጅ አባታቸውን ለማናገር ሲጠይቁ በስፍራው የነበረው የፌዴራል ፖሊስ ሲከለክላቸው የህገ መንግስቱን ድንጋጌ በመጥቀስ መብት እንዳለቸው መግለፃቸው ሲታወቅ ፖሊሱ ስልክ በመደወል የፌዴራል ፖሊስ የወንጀል መከላከልና ምርመራ ሃላፊ የሆነው የህወሀት አባል ግርማይ ማንጁስን እንደጠራና ግርማይ እንደመጡ « ማን ሆነሽ ነው አንቺ?» በማለት ከዘለፉ በኋላ በጥፊ መማታታቸውን ይኸው የአይን እማኝ ደህንነት አስረድቷል።
ስለ ጉዳዩ በወቅቱ “ሪፖርተር” ጋዜጣ የአቶ ተፈራ ዋልዋ ባለቤት ወ/ሮ አይኔ ከማዕከላዊ ፖሊሶች ጋር በፈጠሩት አለመግባባት ለሰዓታት ታስረው ተፈቱ በማለት በደፈናው መዘገቡን ያስታወሰው የድህንነት አባል በጥፊ መመታታቸውን ደፍሮ ሊዘግብ እንዳልቻለ ገልፆዋል። በአጋጣሚ ከአቶ መለስ ዜናዊ ጋር ስብሰባ ላይ የነበሩት አቶ ተፈራ ዋልዋ ስልክ ተደውሎ በባለቤታቸው ላይ የተፈጠረው ሲነገራቸው በቁጣ ስብሰባውን አቋርጠው እንደወጡ አያይዞ አስታውቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከየመን ተይዘው ኢትዮጵያ የተወሰዱት አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ በማዕከላዊ እስር ቤት ውስጥ እንደሌሉ ታማኝ ምንጮች አረጋግጠዋል። አቶ አንዳርጋቸው ሜክሲኮ በሚገኘው የፌዴራል ፖሊስ ህንጻ ቢሮ ለአንድ ቀን በእህታቸው አይኔ ፅጌ መጐብኘታቸውን የጠቆሙት ምንጮቹ ስለመገናኘታቸውም ሆነ ስለአንዳርጋቸው ከማንም ጋር ምንም አይነት ንግግር እንዳያካሂዱ በነግርማይ ማንጁስ ለወ/ሮ አይኔ ጥብቅ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው አጋልጠዋል። ወ/ሮ አይኔ ከሌላው ጊዜ በተለይ ዝምታና ገለልተኛነትን እንደመረጡ ምንጮቹ አያይዘው ገለፀዋል።
No comments:
Post a Comment