Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Saturday, October 18, 2014

ሰማያዊ ፓርቲን ጨምሮ 12 ፓርቲዎች ለምርጫ ቦርድ ደብዳቤ አስገቡ

ሰማያዊ ፓርቲን ጨምሮ 12 ፓርቲዎች ለምርጫ ቦርድ ደብዳቤ አስገቡ
ቀን፡ ጥቅምት 5 ቀን 2007 ዓ.ም.
ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ
አዲስ አበባ
ጉዳዩ፡ የ2007 አገር አቀፍ ምርጫ ይመለከታል፤
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድና የጠቅላይ ሚ/ር ጽ/ቤት እንደምታስታውሱት ጥቅምት 15 ቀን 2005 ዓ.ም. በአዳማ ከተማ በምርጫ 2005 የጊዜ ሰሌዳ ላይ ለመወያየት በቦርዱ በተጠራው ስብሰባ ላይ ተሳታፊ የሆኑ 41 ፓርቲዎች በስብሰባው ላይ ‹‹ከጊዜ ሰሌዳው በፊት በምርጫ ጉዳዮች ላይ እንነጋገር›› በሚል ያቀረቡትን ኃሳብ ቦርዱ ባለመቀበሉ ከነዚህ ውስጥ 33ቱ ፔቲሽን ፈርመው ማቅረባቸው፣ ሃያ አራቱ/24/ ደግሞ ከሰብዐዊና ዲሞክራሲያዊ መብት፣ በምርጫ ሂደትና አፈጻጸም የመከላካያ ኃይሉንና አስተዳደሩን ጨምሮ የመንግሥት መዋቅሮች ጣልቃገብነት፣ የመንግስት ሃብት ለገዢው ፓርቲ ጥቅም መዋል፣ የዲሞክራሲ ተቋማት ላይ የሚደርሰውን ጫና፣ የመንግስት መገናኛ ብዙኃን ለገዢው ፓርቲ በአድልኦ ከማገልገላቸው አልፎ አማራጭ የመረጃ ምንጮች (ነጻው ፕሬስ) ላይ የሚደርሰውን ጫና፣ የምርጫ ቦርድ ነጻነት፣ ሚዛናዊነትና ከአድልኦ ነጻ መሆን …. እንዲሁም ከህገመንግስቱ ጋር የሚቃረኑ አፋኝ ህጎች መውጣታቸውን የሚመለከቱ በአጠቃላይም ከፖለቲካ ምህዳርና ከዲሞክራሲያዊ ነጻ፣ ፍትሃዊ፣ ተኣማኒና አሳታፊ ምርጫ ጋር የተያያዙ 18/አስራ ስምንት/ ጥያቄዎችን በጋራ አቅርበዋል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ መግለጫዎችን አውጥተዋል፡፡ ጥያቄዎቹ ምላሽ ባለማግኘታቸውም ራሳቸውን ከምርጫው አግለዋል፡፡ በመቀጠልም ስለምርጫ 2005 አፈጻጸም ሚያዝያ 22/2005 ዓ.ም መግለጫ አውጥተው ለዋና ዋና ባለድርሻ አካላት ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ይህን እንጂ እስከዛሬ ያቀረብናቸው ጥያቄዎች ተገቢውን መልስ ከማግኘት በተቃራኒ ችግሮቹ በመባባሳቸውና በእጅጉ በከፋ ሁኔታ በመቀጠላቸው ሁኔታዎች ከቁጥጥር ውጪ እንዳይወጡና ሠላማዊ የሥልጣን ሽግግርን ጥያቄ ውስጥ እንዳይከቱ ሥጋት ላይ ከሚጥል ደረጃ ላይ በመድረሳችን ይህን ደብዳቤ ለመጻፍ ተገደናል፡፡
ከላይ የጠቀስነው 18 ጥያቄዎችን ባልተመለሱበት በተካሄደው ምርጫ ሂደትና ውጤት በሚመለከት ከምርጫው በኋላ ሚያዝያ 22/2005 ዓ.ም ያወጣነውን መግለጫ ለማጣቀሻነት አያይዘን አቅርበናል፡፡ በተጨማሪም ከምርጫ 2005 በኋላ በወጣው መግለጫና በተለያዩ ፓርቲዎች በተናጠልና በጋራ በተለያዩ ቦታዎችና ጊዜያት በተደረጉ ሰልፎች የቀረቡ የህዝብ ጥያቄዎች መልስ ያለማግኘታቸው የጥያቄዎቻችንን ትክክለኛነት የሚያረጋግጡና ኢ-ዲሞክራሲያዊ አካሄዱን የሚያጠናክሩ ሆነው አግኝተናቸዋል፡፡ እነዚህ በመንግስት/ገዢ ፓርቲ በማንአለብኝነት የተወሰዱ ህገወጥ እርምጃዎች የአገራችን ቀጣይነት ያለው ዘላቂ ልማትና ሠላም፣ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታ፣ ህገመንግስታዊ ሰብዐዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች አከባበርና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት … በጥያቄ ውስጥ ጥለውታል፡፡ ከነዚህ ዋናዋናዎቹን በማሳያነት ከዚህ በታች አቅርበን ጥያቄዎቻችንን እናስከትላለን፡፡ ጥቅል ተጨባጭ ማሳያዎቹም የሚከተሉት ናቸው፡፡
1ኛ/ በተለያየ የመዋቅር ደረጃ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችን ማስፈራራት፣ የአካላዊና የንብረት ጉዳት ማድረስ፣ በሃሰት ውንጀላና የፈጠራ ክስ ማሰር፣ እየተጠናከረ መምጣትና በዚህም የፓርቲዎችን በዕቅዳቸው መሰረት የመሥራትና የዕለት ተዕለት ነጻ ህጋዊ እንቅስቃሴ መገደብ፤
2ኛ/ በአንድ በኩል የሠላማዊ ትግል ስልቶች ተግባራዊ የሚሆኑበትን መንገድ በመዝጋት፣ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ከህዝብ ጋር እዳይገናኙና ዓላማቸውን፣ ፕሮግራማቸውንና አማራጭ ፖሊሲዎቻቸውን ለህዝብ እንዳያደርሱ በማድረግ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ገዢው ፓርቲ ከምርጫ የጊዜ ሰሌዳ በፊት በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን፣ መንግስታዊ መዋቅርና ሃብት በመጠቀም ለት ተለት በአብዮታዊ ዲሞክራሲ እየጠመቀ የምርጫ ቅስቀሳ ያደረገበትና እያደረገ ያለበት ሁኔታ ግልጽ መሆኑ ፤
3ኛ/ ገዢው ፓርቲ ከመንግስት ካዝና በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ተቀብሎ ያለምንም መስፈርት ለሚፈልጋቸው ፓርቲዎች በማከፋፈል በፓርቲዎች መካከል አላስፈላጊ የአቅም ልዩነት በፈጠረበትና የጥቅም ትስስር/ድጋፍ በገዛበት ሁኔታ የብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ከተግባርና ኃላፊነቱ ውጪ ተሳታፊ መሆኑ፤
4ኛ/ ገዢው ፓርቲ የመንግስት መገናኛ ብዙሃንን በብቸኝነት በሚጠቀምበት እውነታ ለህዝብ አማራጭ መረጃዎችን የሚያቀርቡና በሥርዓቱ ላይ ትችቶች የሚያቀርቡ የነጻው ፕሬስ ጋዜጠኞችን፣ ጦማሪያንና አሳታሚዎችን በመክሰስ አንድም ለወህኒ ያሊያም ለስደት ( በቅርብ ጊዜ ብቻ ከ10 በላይ ጋዜጠኞችና ጦማሪያን መታሰራቸውን፣ ከ20 በላይ ጋዜጠኞችና አሳታሚዎች መሰደዳቸውን ያጤኑኣል) በመዳረግ መራጩን ህዝብ ከአማራጭ መረጃ የማግኘት መብት ሙሉ ለሙሉ በሚያስብል ሁኔታ የተገደበበት፤
5ኛ/ በተለያዩ ቦታዎች በህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ላይ የሚታየው ግጭትና ይህን ተከትሎ የሚታየው የህይወት መጥፋት፣ የንብረት ውድመት፣ መፈናቀልና ማኅበራዊ ምስቅልቅል አሳሳቢ መሆኑ በግልጽ የሚታይና በተደጋጋሚ እየተከሰተ ያለ እውነታ መሆኑ፤ …ወዘተ
እነዚህ ከላይ የተመለከቱት የቅርብ ጊዜ ክስተቶች ማሳያዎች፣ በተያያዘው መግለጫ ላይ የቀረቡ እውነታዎችና ከዚህ በፊት በምርጫ 2005 ዓ.ም ወቅት ያቀረብናቸው ጥያቄዎች ከነጻ፣ ፍትሃዊ፣ ተኣማኒና አሳታፊ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ጋር በቀጥታ የተገናኙ በመሆናቸው ከጊዜ ሰሌዳው በፊት፡- 1. ከ2005 ዓ.ም እስከ ዛሬ ያቀረብናቸው ጥያቄዎቻችን እንዲመለሱ፤ 2. ገዢውን ፓርቲና አጋሮቹን ጨምሮ ሁሉም ህጋዊ ፓርቲዎች በጋራ ተገናኝተው በምርጫና የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ግንባታ ላይ የሚወያዩበት የጋራ መድረክ እንዲዘጋጅ፤እንጠይቃለን፡፡ የእነዚህ ጥያቄዎች መልስ ማግኘት ማለት ለሠላማዊ የሥልጣን ሽግግር / የነጻ፣ ፍትሃዊና ተኣማኒና አሳታፊ የምርጫ ውድድር ሥርዓት/ ሠላማዊ ትግል/ ዕድል ከመስጠትና የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ከማረጋገጥ ጋር በእጅጉ የተቆራኘ ነው፡፡ ማለትም በሌሎች አምባገነን መንግስታትና ሥርዓቶች በጦር መሣሪያ ኃይልና በደህንነት አቅም በመመካት በሥልጣን ላይ ለመቆየት ያሳዩትን እምቢተኝነትና ማንአለብኝነት ተከትሎ የተከሰቱ ህዝባዊ እምቢተኝነትና በውጤታቸውም የተከተሉ ቀውሶችን በጋራ በመከላከል ከአሸናፊ/ተሸናፊ ጠቅላይ የፖለቲካ ሥልጣን አስተሳሰብ በመውጣት ለዲሞክርሲያዊ ሥርዓት ግንባታ መሠረት የመጣልና ለዘላቂ ሠላምና ልማት ዋስትና መስጠት ማለት ነው፡፡ በዚህ ማንም ተጎጂ አይሆንም፡፡
በተቃራኒው እነዚህ ጥያቄዎች ባልተመለሱበት የሚደረግ የምርጫ ተሳትፎ ለኢህገመንግስታዊነትና ኢዲሞክራሲያዊነት ዕውቅና በመስጠት አገሪቷንና ህዝብን ወደባሰ አዘቅት መወርወር በመሆኑ በታሪክና ትውልድ ፊት የሚያስጠይቅ ይሆናል፤በዚህ ማንም ተጠቃሚ አይሆንም፣ በዚህ መተባበርም ከተጠያቂነት አያተርፍም፡፡
ስለዚህ እኛ ስማችን ከዚህ በታች የሰፈረው ፓርቲዎች ምርጫችን ማናችንም ተጎጂና ተጠያቂ የማንሆንበትንና ሁላችንም ተጠቃሚ የሚያደርገንን ዲሞክራሲዊና ነጻ፣ፍትሃዊ፣ተኣማኒና አሳታፊ ምርጫ/ ሠላማዊ ትግል/ በመሆኑ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ከምርጫ የጊዜ ሰሌዳ በፊት ባለበት አገራዊና ህዝባዊ ኃላፊነት መሠረት ለጉዳዩ ትኩረት እንዲሰጠውና ተገቢ ምላሽ በመስጠት ሚዛናዊነቱን. ከወገንተኝነት የጸዳ፣ በምርጫ ህጉ በተሰጠው ሥልጣንና ኃላፊነት መሰረት የሚሰራ መሆኑን እንዲያረጋግጥ በድጋሚ አበክረን እንጠይቃለን፡፡
ጥያቄኣችንን በግልባጭ ያሳወቅናችሁ የመንግስት አካላት ጉዳዩ በመዋቅርና በባለቤትነት በቀጥታ የሚመለከታችሁ በመሆኑ ለአቤቱታችን አጽንኦት ሰጥታችሁ በቅርበት እንዲትከታተሉና አዎንታዊ ተጽዕኖ እንድታደርጉ በመራጩ ህዝብ ሥም እናሳስባለን፡፡
(የፓርቲዎቹ ዝርዝር ከፎቶው ላይ ይመልከቱ)
ግልባጭ፡- ለህዝብ ተወካዮች ም/ቤት፤ ለጠቅላይ ሚ/ር ጽ/ቤት፤ ለኢትዮጵያ ሰብዐዊ መብት ኮሚሽን፤ አዲስ አበባ
Hune Abyssinia's photo.
Hune Abyssinia's photo.
Hune Abyssinia's photo.

No comments:

Post a Comment

wanted officials