ድምፃዊ ንዋይ ደበበ መልካም ግንኙነትና ወዳጅነት እንደነበራቸው ከሚናገሩት አቶ ኤፍሬም ኤርሚያስ ከሚባሉ ግለሰብ 20,000 ዶላር ተበድሮ ‹‹አልከፍልም›› ብሏል ተብሎ ፍትሐ ብሔር ክስ ተመሠረተበት፡፡
ድምፃዊውና አበዳሪ መሆናቸውን የሚናገሩት ግለሰብ በነበራቸው መልካም ግንኙንት አማካይነት ከስድስት ዓመታት በፊት ገንዘቡን እንዳበደሩት በክሱ ላይ ሰፍሯል፡፡ ‹‹በአሜሪካ ያሉብኝን አንዳንድ ዕዳዎች ለመክፈል ገንዘብ ስለሌለኝ አበድረኝ፤›› ብሎ ድምፃዊ ንዋይ 20,000 ዶላር የተበደራቸው ቢሆንም፣ በተለያዩ ጊዜያት ሲጠይቁት ሊከፍላቸው ባለመቻሉ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት እንደወሰዱት ሰነዶች ያስረዳሉ፡፡
በሦስት እማኞች ፊት በአንዲት ግለሰብ አማካይነት ብድሩን የሰጡት መሆኑን አመልካቹ ለፍርድ ቤት ገልጸው፣ ሚያዝያ 6 ቀን 2000 ዓ.ም. ያበደሩትን ገንዘብ ላለፉት ስድስት ዓመታት በራሳቸውና በሽማግሌዎች ቢያስለምኑም ሊሰጣቸው አለመቻሉን ለፍርድ ቤቱ ገልጸዋል፡፡
ከአሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ መፈለጉን፣ ነገር ግን የተለያዩ ዕዳዎች ስላሉበት የሚከፍለው ገንዘብ እንደሌለው ሲያስረዳቸው ብድሩን እንደሰጡት በክስ ማመልከቻቸው የገለጹት ከሳሽ አቶ ኤፍሬም ኤርሚያስ፣ ክሱ እልባት እስከሚያገኝ ድረስ የድምፃዊው ቤት እንዲታገድላቸው ያቀረቡትን አቤቱታ፣ የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ፍትሐ ብሔር ችሎት ተቀብሎና መርምሮ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
ፍርድ ቤቱ በሰጠው ትዕዛዝ፣ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 3 የሚገኘው የድምፃዊው ንዋይ መኖሪያ ቤት እንዳይሸጥ፣ እንዳይለወጥና በማንኛውም ዓይነት መንገድ ለሌላ ወገን እንዳይተላለፍ ዕግድ ጥሎበታል፡፡ በመዝገቡ ላይ እልባት ለመስጠት ለኅዳር 2 ቀን 2007 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
No comments:
Post a Comment