የወ/ሮ አዜብ መስፍን ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ መዳከሙ ተሰማ
ESAT ዜና :-ባለቤታቸውን በድንገተኛ ሞት ከማጣታቸው በፊት የፓርላማ አባል የነበሩት ወ/ሮ አዜብ መስፍን በራሳቸው ፍቃድ ፓርላማውን ከመልቀቃቸውም በተጨማሪ በድርጅታዊ ስራዎች ላይ የሚያደርጉት ተሳትፎ እየተዳከመ መምጣቱን ምንጮች ገልጸዋል፡፡
ወ/ሮ አዜብ ባለፈው አንድ ዓመት በፓርላማው መቀመጫቸው ላይ ታይተው የማያውቁ ሲሆን ለፓርላማው ቅርበት ያላቸው ምንጮች ወይዘሮዋ በራሳቸው ፈቃድ ከፓርላማ አባልነታቸው መሰናበታቸውን ገልጸዋል፡፡
አቶ መለስ ዜናዊ በሕይወት በነበሩበት ወቅት የትግራይ ክልል ካለው 38 የፓርላማ መቀመጫ ሁለቱ በእርሳቸውና ባለቤታቸው መያዙ ይታወቃል:: እንዲሁም በ2003 ዓ.ም በስምንተኛው የኢህአዴግ ድርጅታዊ ጉባዔ ወቅት መለስከህወሃት 9 የሥራ አስፈጻሚ አባላት መካከል ወ/ሮ አዜብን በማስመረጥ የኢህአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ውስጥ እንዲቀላቀሉ አድርገዋል፡፡
በዚህም አድራጎታቸውም በትግል ጎዋዶቻቸው ሳይቀር የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴውን የቤተሰብ ጉባዔ አደረገው በሚል ውስጥ ውስጡን በከፍተኛ ደረጃ ሲተቹና ሲወገዙ ቆይተዋል።
አቶ መለስ፤ ወ/ሮ አዜብን ሲያስመርጡ በመተካካት ስም ነባር የትግል አጋሮቻቸውን ማለትም እነስዩም መስፍንን፣ አባይ ጸሐዬ፣ አርከበ ዕቁባይን የመሳሰሉ የስራ አስፈጻሚና የማዕከላዊ ኮምቴ አባላትን በማባረር መሆኑ ደግሞ በህወሃት ውስጥ ያለመተማመን እንዲፈጠር ምክንያት ከመሆኑም በላይ ጉምጉምታና ኩርፊያ ሰፍኖ ቆይቷል።
ወ/ሮ አዜብ መስፍን አቶ መለስ ከሞቱም በሃላ በመጋቢት ወር 2005 ዓ.ም በተካሄደው የህወሃት ጉባዔ በስራ አስፈጻሚነት በመመረጥ በኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚነት እስካሁን የቀጠሉ ቢሆንም ከዚህ ቀደም በሁሉም ቦታ ጣልቃ እየገቡ የሚያዙበትና ሰዎችን የሚዘልፉበትን ያልተገባ ባህርይ ትተዋል ብሏል ምንጫችን ::እንዲሁም ስብሰባዎችን አልፎ አልፎ ከመካፈል ያለፈ እምብዛም ተሳትፎ ሲያደርጉ አለመታየታቸውን የጠቀሰው ምንጫችን ፣ ባለቤታቸውን ተማምነው ከዚህ ቀደም ብዙ የጎዱዋቸው ከፍተኛ አመራሮች ጉዳት ሊያደርሱብኝ ይችላሉ በሚል እየሸሹ ሳይሆን ዕንዳልቀረ መወራቱን ጠቅሷል::
ከያዝነው ዓመት አጋማሽ በሁሃላ ይካሄዳል ተብሎ በሚጠበቀው የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ጉባዔ ላይ ወ/ሮ አዜብ መስፍን በህወሃት የስራ አስፈጻሚነት ዳግም የመመረጣቸው ዕድል አነስተኛ መሆኑን ምንጫችን አክሎ ጠቁሟል፡፡
No comments:
Post a Comment