''ሰንደቅ አላማውን በማያከብሩት ላይ እርምጃ ይወሰዳል ተባለ'' (አዲስ አድማስ)
የትኛውን ሰንደቅ አላማ፤ የተዘቀዘቀወን፣ የተረገጠውን ወይስ የተቀበረወን...? (እኔ)
እንደ አቶ መለስ እና እንደ ኢሃዴግ ባንዲራውን ጠምዶ የያዘ ማንም አልነበረም። ምክንያቱ ግልጽ ነው፤ ኢህ አዴግ ያኔ ''ወንበዴ'' የነበረች ጊዜ ያኔ መንግስት የነበረው ደርግ አይቀጡ ቅጣትም ይሁን ይቀጡ ቅጥጣት ''ወንበዴውን'' በሚቀጣው ጊዜ በድል ቦታ ላይ የሚያውለበልበው አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ባንዲራን ነበረ። እና በወቅቱ ወንበዴ በአሁኑ ወቅት ደግሞ ነጋዴ የሆኑ መሪዎቻⶭን ባንዲራን ጠምደው ቢይዟት ምንም አይደንቅም። (በቅንፍም፤ መሪዎቻችንን ነጋዴ ያልኩት ከወንበዴ ጋር እንዲገጥም ብዬ እንጂ ለክፋት አለመሆኑን እገልጻለሁ።)
በነገራችን ላይ ኢህ አህአዴግን ኢሃዴግ ያደረጉት አራቱም ድርጅቶች ለየከልላቱ የመረጡት ባንዲራ /አርማ/ ከኢትዮጵያ ባንዲራ መልክ ራቅ ያለ እንዲሆን የተደረገውም የባንዲራውን አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ቀለማት ላይ ቂም ከመቋጠር የተነሳ ሊሆን እንደሚችል እንጠረጥራለን።
መጠርጠራችን ካልቀረም የኦነግን አርማ ራሱ ኢህአዴግ ጠምዳ የያዘችው ከዋናው ሰንደቅ አላማ ቀለማት የተቀዳ በመሆኑ ነው። ከዚህ በፊት እንዳወጋነው ኦነግ ሲመሰረት የነበሩ ታጋዮች የትግሉ ማዕከል ''ጭርቁምፈምቶታ ኡመታ ኢትዮጵያ'' (የተጨቆኑ የኢትዮጵያ ህዝቦች) የሚል መሆን አለበት የሚሉ እና ኦሮሞ ነጻነት ግንባር የሚሉ ሁለት ሃሳቦች ይንሸራሸሩ ነበር። የኦነግን አርማ ልብ ብለን ስናይ ሁለቱም አይነት የግንባሩ ታጋዮች ጸባቸው ከኢትዮጵያ ሰንደቅ እና የሰንደቁ ቀለማት ሳይሆን ጨቋኞች ከሚሏቸው አመራሮች ጋር መሆኑን መረዳት ቀላል ነው።
የኢህአዴግ ቂም ግን ስር ነቀል አቄቂያም ነው። ''ፀቤ ከጨቋኙ ደርግ አምባገነናዊ ስራአት ጋር ነው'' ሲለን የነበረው ኢህ አዴግ ''ባንዲራን ጨርቅ ነው'' ከማለት ጀምሮ በአፋር ግመሎቹ ሁሉ ያውቁታል የሚባለውን፣ በኦሮሞ የተቃዋሚው አርማ ቀለም ሁሉ የተደረገውን፣ በደቡብ ከትንሽ እስከ ትልቅ በዓላት ማድመቂያ የተደረገውን፣ በትግራይ እና በአማራው ዘንድም የማንነት መገለጫ ሆኖ የነበረውን አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ቀለም በሌሎች ክልላዊ ባንዲራ ተካው። ሳስበው ኢህ አዴግ ጠቅላላ የሀሪቱን ሰንደቅ አላማ ራሱ ሌላ አይነት ቀለማት ቢሰጠው ደስታው ይመስለኛል። ነገር ግን ሰንደቁን እንደ ደሙ ለሚያየው መላ ኢትዮጵያዊ ይሄ ከባድ ነበር።
የሆነው ሆኖ ''የብሄር ብሄረስቦች ህዝቦች እና ሀይማኖቶች በእኩልነትና በአንደነት አብረው ለመኖር ያላቸውን ተስፋ'' ያሳያል የተባለው ኮከብ የባንዲራው አውራ ሆኖ ተቀመጠ። (ውይ ትርጉሙ እንዴት ደስ ይላል።... ችግሩ የብሄር ብሄረስቦች እና ሃይማኖቶች እኩለነት እኩለ የገዢው ፓርቲ ግዝገዛ እና ብዝበዛ ሰለባ መሆናቸው ነው) ይሄ ሁሉም ሆኖም የመንግስታችን ዋና ሴራ ሂደት ባለቤቶች (ይቅርታ ሴራ ሂደት ያልኩት ስራ ሂደት ለማለት ፈልጌ ነው) እና የመንግስታችን ዋና ሰዎች ለሰንደቅ አላማው ቁብ ሲሰጡ አልታዩም። ከአምስት ይሁን ከስድስት አመት በፊት በባንዲራ ጉዳይ ልብ ገዝተናል ያለው መንግስታችን አሁን ደግሞ የባንዲራ ቀን ካላከበራችሁ ወዮላችሁ እያለን ነው።
እኛም እንጠይቃለን፤
የቱን ባንዲራ...
አቶ መለስ ጨርቅ ነው ያሉትን ነው፣ ወይስ በአደባባይ ዘቅዝቀው የያዙትን፣ ወይስ በቀብራቸው ጊዜ ሳይሞት አብሯቸው አፈር የገባውን፣ ወይስ መቼለታ ዶክተር ቴውድሮስ ያስረገጡትን ባንዲራ ነው ካላከበራችሁ ወዮላችሁ የምትሉን... !?
No comments:
Post a Comment