ሰበር ዜና :የአንድነት ፓርቲ ፕሬዚዳንት ኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው በገዛ ፍቃዳቸው ሥልጣናቸውን ለቀቁ
አቶ በላይ ፍቃዱ ቀጣዩ ፕሬዚዳንት በመሆን ተመረጡ
የአንድነት ፓርቲ ብሔራዊ ም/ቤት በዛሬው ዕለት ከጠዋቱ 3፡00 ሰዓት ጀምሮ የተሰበሰበ ሲሆን በስብሰባውም ላይ በፕሬዚዳንቱ ኢ/ር ግዛቸው ሽፈራው ሪፖርት የቀረበ ሲሆን ከውስጥና ከውጭ በተፈጠሩ አንዳንድ የማያሰሩ ችግሮች፣ ካለባቸው የሥራ ጫና እና ፓርቲው ወደፊት አንድነቱን ጠብቆ ለ2007 ምርጫ አሸናፊ ሆኖ እንዲወጣ በማሰብ በራሳቸው ሙሉ ፍቃድ ከፕሬዚዳንትነታቸው በመልቀቅ ለብሔራዊ ም/ቤቱ ባቀረቡት ሪፖርት አሳውቀዋል፡፡
ብሔራዊ ም/ቤቱ የኢ/ር ግዛቸው የሰለጠነ ዲሞክራሲያዊ አካሄድ እጅግ ከፍተኛ በሆነ አክብሮት በመመልከትና በአገር ውስጥ በተቃውሞው ጎራ ለሚንቀሳቀሱና ለራሱ ለገዢው ፓርቲም ጭምር አስተማሪ የሆነ እርምጃ በመውሰዳቸው አክብሮትን ቸሯቸዋል፡፡
በቀጣይም የፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ በሚፈቅደው መሰረት በፕሬዚዳንትነት የሚመሩ እጩዎችን በማቅረብ ለማስመረጥ አምስት አባላት በአስመራጭ ኮሚቴነት ተሰይመዋል፡፡
ራሳቸውን ለፕሬዚደንትነት በእጩነት ያቀረቡት
1ኛ. አቶ በላይ ፈቃዱ
2ኛ. አቶ ደረጀ ኃይሉ
3ኛ. አቶ ትዕግስቱ አወሉ ሲሆኑ እነዚህ እጩዎች ራሳቸውን ተራ በተራ ካስተዋወቁ በኋላ የብሔራዊ ም/ቤቱ አባላት
በምስጢር ድምፅ አሰጣጥ ለሚፈልጉት ዕጩ ድምፅ ሰጥተዋል፡፡
በመጨረሻም በተደረገው የድምፅ ቆጠራ አቶ በላይ ፍቃዱ ከፍተኛ ድምፅ በማማምጣት አንድነት ፓርቲን በፕሬዚዳንትነት እንዲመሩ ተመርጠው ቃለ መሃላ ፈፅሟል፡፡
ስብሰባው እጅግ ዲሞክራሲያዊ በሆነ መግባባት ተጠናቋል ሲሉ የአንድነት ፓርቲ ሴክሬታሪያት ለፍኖተ ነፃነት ገልጸዋል፡፡
No comments:
Post a Comment