የአፍሪካ ህብረት እንዲሁም የኢትዮጵያና የደቡብ አፍሪካ መንግስታት ምላሽ አልሰጡም
የአሜሪካ መንግስት ዘገባው አስቂኝ አልቧልታ ነው ሲል አጣጥሎታል
ተጠርጣሪ ሆኖ የተጠቀሰው የሱዳን መንግስትም ዘገባው የውሸት ፈጠራ ነው ብሏል
ከረዥም ጊዜ ውዝግብ በኋላ እ.ኤ.አ በ2012 የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሆነው የተሾሙት ደቡብ አፍሪካዊቷ ዱላሚኒ ዙማ ላይ፣ በዚያው ሰሞን እዚሁ አዲስ አበባ ውስጥ ግድያ ሊፈፀምባቸው ነበር በሚል አልጀዚራ ሰሞን ዘገበ፡፡
የግድያ ሴራው ጠንሳሾች ማንነትንና መነሻ ሰበቡን በግልጽ ያልዘገበው አልጀዚራ፣ ሱዳን ተጠርጣሪ እንደነበረች ጠቅሶ ሴራው ለደቡብ አፍሪካም ሆነ ለኢትዮጵያ የደህንነት ሰዎች ድንገተኛ ነበር ብሏል፡፡
ከደቡብ አፍሪካም ሆነ ከኢትዮጵያ በኩል ዘገባውን በተመለከተ የተሰነዘረ ምላሽ የለም፡፡ የአፍሪካ ህብረትም፤ በአልጀዚራ የተላለፈውን ዘገባ አይተነዋል ከማለት ውጭ፣ ማረጋገጫም ሆነ ማስተባበያ ምላሽ አልሰጠም፡፡
ኮሚሽነሯ የስራ ሃላፊነታቸውን ደህንነቱ በተጠበቀ መንገድ እያከናወኑ ናቸው በሚል መግለጫ ያወጣው የአፍሪካ ህብረት፤
የኢትዮጵያ የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት ተቋም፤ የህብረቱ መሪዎችና ተወካዮችን ደህንነት ለመጠበቅ የሚያካሂደውን ስራ እናደንቃለን፤ እንደአስፈላጊነቱም ከደቡብ አፍሪካ መንግስትና ከሌሎች የህብረቱ አባል አገራት ጋርም በትብብር ይሰራል ብሏል፡፡
በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ሃላፊ ሊንዳ ግሪንፊልድ ግን፣ ዘገባውን የሚያጣጥል ቀጥተኛ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡ የግድያ ሴራ ተጠንስሶ ነበር የሚለው መረጃ ከየት እንደመጣ አይታወቅም፤ ቁም ነገር የሌለው ቧልት ነው ብለዋል – ሃላፊዋ፡፡
በአልጀዚራ ዘገባ ውስጥ የግድያ ሴራ ተጠርጣሪ ሆኖ የተጠቀሰው የሱዳን መንግስትም፤ ዘገባው የውሸት ፈጠራ ነው በማለት እንዳስተባበለ ሱዳን ትሪቢዩን ገልጿል፡፡ የግድያ ሴራን የሚያክል ወንጀል ያለ ጠንካራ መነሻ ሰበብ እንደማይጠነስስ የገለፁ የሱዳን መንግስት ባለስልጣናት፤ “ኮሚሽነሯን ለመግደል ሱዳን ምን መነሻ ሰበብ ይኖራታል?” በሚል ዘገባው ጤናማ አእምሮ ላለው ሰው ትርጉም የሚሰጥ አይደለም ብለዋል፡፡ የደቡብ አፍሪካ መንግስት እና ኮሚሽነሯ በጉዳዩ ላይ ምንም አለማለታቸው አስገራሚ ነው ሲሉ፣ የሱዳን ባለስልጣናት መናገራቸውንም የሱዳን ትሪቡን ገልጿል፡፡
addisadmas.com
No comments:
Post a Comment