አርቲስት ሚኪያስ መሐመድ የተለያዩ ሰዎችን ‹‹ጎማ እናስመጣ›› እንዲሁም በአንድ ወቅት ንሮ የነበረውን የሲሚንቶ ገበያ ሰበብ በማድረግ ‹‹የማውቃቸው ሰዎች አሉና ሲሚንቶ አብረን እንነግድ›› በማለት ነበር እንቅስቃሴውን የጀመረው፡፡
ሚኪ ወደዚህ ስራ ሲገባ በቀላሉ የሚያውቃቸውንና ገንዘብ አላቸው ብሎ የሚተማመንባቸውን ሰዎች ማጥመድ ጀመረ፡፡ በዚህ ወጥመድ ውስጥ የተወሰኑ ባለሀብቶች ገብተውለት 8 ሚሊዮን ብር ገደማ ሲያገኝ የተጠቀሰውን ያህል መጠን ያለው ቼክም ፅፎ ሰጣቸው፡፡ ቼኩ በቂ ስንቅ(ገንዘብ) የሌለው መሆኑን ባለሀብቶቹ ሲረዱ እንደተጭበረበሩ የገባቸው ሲሆን፤ ከእነዚህ ሰዎች አንዱ(2 ሚሊዮን ብር የሰጡት) ጉዳያቸውን ይዘው ወደቦሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ አቀኑ፡፡ የቦሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስም አቶ ሚኪያስ መሐመድን በጷግሜ ወር በቁጥጥር ስር አዋለው፡፡
በፖሊስ ጣቢያው ከሳሽና ተከሳሽ ፊት ለፊት ሲገናኙ ተከሳሽ ሚኪ ስቅስቅ ብሎ እያለቀሰ የከሳሽ እግር ስር ወድቆ ተማፀነ፡፡ ‹‹እንደራደር›› ሲልም ጥያቄ አቀረበ፡፡ በዚህ መሰረት ግማሽ ክፍያ ወዲያውኑ ለመስጠትና ቀሪውን ደግሞ በ15 ቀናት ውስጥ ለመክፈል ጊዜ እንዲሰጠው መደራደሪያ አመጣ፡፡ በዚህ መሐል ነው እንግዲህ ምስኪኑ ራስታ ዘፋኝ ህይወቱን ሙሉ ያጠራቀመውን ገንዘብ አንስቶ ለሚኪ የሰጠው፡፡ ሚኪም ከታደለ ሮባ የወሰደውን ገንዘብ ከተከሰሰበት 1.7 የሚሊዮን ብር ዕዳ ግማሹን ሊከፍል ቻለ፡፡
ይህ ሁሉ ሁኔታ ሲሆን ማለትም ሚኪ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ሲውል ዛሬ እያስተባበለ ያለው ሰይፉ ፋንታሁን ሊያገባ ጥቂት ቀናት ቀርተውት ነበር፡፡ ሚዜውም ነበር፡፡ ሙሽራውና ሚዜዎች ስቲም ሊገቡ ቀጠሮ በነበራቸው ቀን ሚኪ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ስለነበር ሳይገኝ ቀርቷል፡፡ ከእስር ከተፈታ በኋላ ሰርጉ ሲከናወን ይህንን ሚስጥር የሚያውቁት ሚኪና ታደለ ብቻ ነበሩ፡፡ እናም ውሾን ያነሳ… ተባባለው ተማማሉ፡፡
ከሰርጉ ስነስርዓት በኋላ የሚኪ ስልክ ድንገት ዝግ መሆኑ ግን ግራ የሚያጋባ ሆነ፡፡ በዚያ ላይ አሜሪካ የመግባቱ ጉዳይም መወራት ጀመረ፡፡ እሱ ግን በቫይበር ከሚደወሉለት ስልኮች ውስጥ የአንድ ሰውን ጥሪ ብቻ ያነሳ ነበር፡፡ የሰራዊት ፍቅሬን!!
በዚህ ወቅት ከሚኪያስ መሐመድ ቼክ የተሰጣቸው ሰዎች በሙሉ ወደባንክ መጉረፍ ጀመሩ፡፡ ቼኩን አስመትተውም አርቲስቱ የሚመጣበትን ቀን መጠባበቅና መፀለይ ሆነ ስራቸው፡፡ ይሁንና በመሀል ሽምግልና ተብሎ እነዚህ ቼኮች በሙሉ ተሰበሰቡ፡፡
(በዚህ ወቅት አማን(ጀርመኑ) ለተባለ ወጣት ከሚኪ የተፃፈለትን የ350ሺህ ብር ቼክ ልብ ያለው ሰው አልነበረም፡፡ ይህ ወጣትም ቼኩን አስመትቶ ጉዳዩን አቃቤ ህግ ጋር አድርሶታል፡፡)
ከሽምግልናው ጎን ለጎን ድምፃዊ ታደለ ሮባ ‹‹ይህን ያህል አመት የሰራሁበትን ገንዘብ ዘረፈኝ፤ ጉድ አደረገኝ›› እያለ የሚኪ እናት ቤት ይመላለስ ነበር፡፡ እናትየውም ‹‹አይዞህ ቤቴን ሸጬም ቢሆን እከፍላችኋለሁ እንጂ ልጄን ከሳችሁ አታሳስሩብኝ›› ይሉ ጀመር፡፡
የእናትየው ሀዘንና ቼክ የተጭበረበሩ ሰዎች ለቅሶ ያሳዘነው ዮናስ ቬጋስ ‹ጉዳዩን ለኔ ተውት›› ብሎ እንቅስቃሴ ጀመረ፡፡ እንቅስቃሴው ሚኪን ከአሜሪካ አስመጥቶ የእናቱን ቤት ሸጦም ቢሆን ቼክ ለተሰጣቸው ሰዎች ገንዘባቸው እንዲመለስላቸው የማድረግ ነው፡፡
በመሆኑም ዮናስ ቬጋስ ወደአሜሪካ አቀናና ከሚኪ ጋር ተገናኘ፡፡ ከቀናት በኋላም ታደለ ሮባ ተከተለው፡፡
የሚገርመው ‹‹በህይወት ዘመኑ የሰራበትን ገንዘብ የበላው›› እና ስልኩን ዘግቶ የጠፋበት ሚኪያስ መሐመድ በአሜሪካ ታደለ ሮባን አየር ማረፊያ ድረስ ሄዶ በመቀበል ሰርፕራይዝ አድርጎታል፡፡
በቀጣይነት ድርድሮችና ውይይቶች መደረግ ጀመሩ፡፡ በአደራና በሽምግልና ቼኮቹ የተቀመጡት ሰራዊት ፍቅሬ ጋር በመሆኑ ሚኪ በቀጥታ ለሰራዊት በመደወል ሁኔታውን አረጋገጠ፡፡ ከዚህ በኋላ ወደኢትዮጵያ ተመልሶ አጭበርብሮበታል የተባለባቸውን ቼኮች ለመክፈል ተስማማ፡፡ የሚመለስበት ቀንም ተቆረጠ፡፡ ነገር ግን በዚህ መሀል አንድ ችግር ተፈጠረ፡፡ 350 ሺህ ብር የተበላው ወጣቱ አማን(ጀርመኑ) ‹‹ክሴን አላነሳም፤ በክሱ እቀጥልበታለሁ›› ሲል በአቋሙ ጸና፡፡ ሚኪያስም ‹‹እንደዚህ ከሆነማ አልመለስም በቃ!!›› ሲል ሀሳቡን የመቀየር ነገር አመጣ፡፡ አማንን(ጀርመኑን) የሚያውቁት ሰዎች በሙሉ ክሱን እንዲያቋርጥ ቢወተውቱትም አማን ግን በእንቢታው ፀና፡፡ (ይህኛውን ታሪክ በቀጣይ እንመለስበታለን)
የአማን ነገር እንደማይሆን ሲታወቅ ‹‹ያበጠው ይፈንዳ›› በሚል ይመስላል ሚኪያስ መሀመድና ታደለ ሮባ ከሎስ አንጀለስ በአንድ አውሮፕላን ተሳፍረው ቅዳሜ ጠዋት አዲስ አበባ ገቡ፡፡
አዲስ አበባ ከገቡ በኋላ ሚኪያስ መሀመድ ለሽማግሌዎቹ አንድ ተማፅኖ አቅርቧል፡፡ ይህም ገንዘብ እንዳላጭበረበረና አሜሪካ የሄደው ለመዝናናት እንደሆነ በሚዲያዎች የሀሰት ዘገባ እንዲሰራለት ነው፡፡ ይህን የሀሰት ዘገባ ሰይፉ ፋንታሁን ብቻ ‹‹እሺ›› ብሎ ሲቀበል ሌሎች ለሙያቸው ያደሩ ጋዜጠኞች አንሰራም ብለዋል፡፡
እናም ዘሃበሻ ቀደም ብላ እንደጠቀሰችውም ሚኪያስ መሀመድ ቅዳሜ ምሽት ሰይፉ ሬዲዮ ላይ ቀርቦ የውሸት መአቱን የደረደረው ለዚህ ነው፡፡ እውነታው ይህ ሆኖ ሳለ ጉዳዩን እያወቅን ዝም ብለን የቆየነውን እኛን ሰራተኞቹን መወንጀል ለምን አስፈለገው? እንላለን፡፡