Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Wednesday, January 13, 2016

ይድረስ ለ ኢህአዴግዬ! ጉዳዩ፤ እየመሸ መሆኑን ስለማሳወቅ! – አቤ ቶኪቻው

(ይህ ጽሁፍ ለአዲስ ገጽ መጽሄት ተብሎ የተጻፈ ነው! ባለፈው ቅዳሜ ከታተመ በኋላ መጽሄቷን በቅርብ የማያገኙ ወዳጆች አጋራን ባሉኝ መሰረት እነሆ… ብያለሁ!)
Abe-Tokchaw-Satenawይሄንን ደብዳቤ ልጽፍልሽ ከመጀመሬ በፊት አንድ የቴሌቪዥን ፕሮግራም እየተመለከትኩ ነበር። ያዲሳባ ሴቶች መደዳውን ተደርድረው አንድ ጎረምሳ በፍቅር ያጫቸው ዘንድ በዜማ እና በሌሎችም ጥቅማጥቅሞች ሲለማመጡት እና እኔ እሻል እኔ ሲፎካከሩበት አየሁ… አጀብ ያገሬ ቴሊቪዥን ጣቢያዎች ስንት ርዕሰ ጉዳዮች ባሉባት ሃገር ለቆነጃጅት ጎረምሳ በመምረጥ መጠመዳቸው ስልጣኔው እንዴት ዘልቆ ቢገባቸው ነው… ስል አደነኳቸው።
ይህ አይነቱ የቴሌቪዥን መሰናዶ እዚህ እኛ የምንኖርበት ሃገርም አለ… እነ አሜሪካም ያደርጉታል፤ ልክ ባለፈው ጊዜ አቶ ሃይለማሪያም ‘’ድርቅ ብርቅ አይደለም ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ካሊፎርኒያም በአሁኑ ሰዓት በድርቅ እየተሰቃየ ነው’’ እንዳሉት በይው! ታድያ ግዜው የግሎባላይዜሽን ነውና፤ እዚህ እኔ ያለሁበት እንግሊዝ እና አማሪካ ያለው ነገር ሁሉ ኢትዮጵያ መኖሩም ብዙም ባይደንቅም፤ ነገር ግን ‘እነርሱጋ ለምን ኖረ እኛጋስ ለምን ያስፈልጋል ብሎ መገምገም የቴሌቪዥን ዝግጅት አቅራቢዎቹ ስራ ነበር። እነ ድርቁንስ እግዜሩ ከላይ አከፋፍሎን ነው… ድርቅናውን ግን ራሳችን እንዳመጣልን ከነርሱ የኮረጅነው ነው። ልብ አድርጊልኝ ኢህአዴግዬ፤ ቆነጃጅት መድረክ ላይ ተኮልኩለው ‘’ቁርስህን እንቁላል ፍርፍር ራትህን ቋንጣ ፍርፍር እንዳበላህ፣ በዘፈን እያሞካሸው እንዳባብልህ እኔን ውሰደኝ እኔን ውሰደኝ’’ ሲሉ ማየት ከባድ ድርቅና አይደለም ትያለሽ…? እነ አማሪካ እና እንግሊዝ እንዲህ ያለውን ዝግጅት በየቴሌቪዥናቸው የሚያቀርቡት ማህበረሰቡ ርስ በርሱ በቅጡ የማይቀራረብ ሁሉም የየራሱን ክበብ ከቦ አትደረስብኝ አልደርስብህም ያሰመረ አይነት ስለሆነ የመገናኛ መድረክ ለመፍጠር አስበው ነው… እኛ ሃገር አውቶብስ ፌርማታው… ታክሲ ግፊያው ወፍጮ ቤቱ ሳይቀር የፍቅር መድረክ በሆነበት ቆነጃጅት በቴሌቪዥን መስኮት አደባባይ ወጥተው አንዱን ወንድ እኔን ውሰደኝ እኔን… ሲሻሙበት ማየት በእውኑ እንግዳ ነገር ነው!
አንዳንድ ወዳጆች እማ እንደሚጠረጥሩት ‘’ይሄ አይነቱ ዝግጅት ኢህአዴግዬ ጎረምሳውን ሁሉ አስራ፣ አስራ ሃገሩ ላይ የወንዶች እጥረት እንዲከሰት በማድረጓ የመጣ ነው’’ ቢሉ… የለም… በዚህ እንኳ እኔ አልስማማም፤ ነውር አይደለም እንዴ ኢህአዴግዬ እንዲህ አይነት አድሎ አታውቅም። የጾታ እኩልነት በተረጋገጠበት በዚህ ወቅት ወንድ ወንዱን ለይታ አታስርም ይሄ ስም ማጥፋት ነው ሁሉንም ነው የምታስረው እንጂ ‘ወንድ ወንዱን ለቅማ አስራ የወንድ እጥረት ተከሰተ’ ብሎ ማለት ተራ ስም ማጥፋት ነው ብዬ ተከራከርኩልሽ!
ነገርን ነገር ያነሳዋል አፈር ስሆን በዘጠና ሰባት ዓመተ ምህረት የሆነውን ልንገርሽ…. ምነው እንኳ ያኔ ‘’ከንግዲህ ጣቱን የቀሰረ ጣቱ ይቆረጣል’’ አዋጅ የታወጀ ጊዜ… አንቺኮ ትረሻለሽ! ደግነቱ እኛ አለንልሽ መዝግበን የያዝን ሰዎች እናስታውስሻለን! እናልሽ ያኔ ጎረምሳው ሁሉ በአደገኛ ቦዘኔ አዋጅ ተለቅሞ እስር ቤት ሲገባ አንዱ ‘’አደገኛ ቦዘኔ’’ ወዳጃችን በዛ በቀውጢ ሰዓት አንዷን አፍቅሮልሽ ጠየቃት፤ የፍቅር አጋሬ ሁኚ … ብሎ ቢላት ጊዜ ምን አለችው መሰለሽ… ‘’የኔ ጌታ በዚህ ሰዓት ካንተጋ ፍቅር ጀምሬ ካሁን አሁን ታሰረ አልታሰረ እያልኩ የምጨነቅበት እና የምሳቀቅበት ምክንያት የለም! ግርግሩ ሲያልፍ ካለህ ያኔ ጠይቀኝ’’ አለችው።
የኔ ነገር… ይሄንን ሁሉ ያነሳሁት በምን መሰለሽ… ላንቺ ይሄንን ደብዳቤ ከመጻፌ በፊት አየሁት ባልኩሽ ፕሮግራም ላይ፤ አንዷ ኮረዳ በግድግዳ ተከልሎ ላላየችው ጎረምሳ የዘፈነችለትን ዘፈን፤ እኔ ላየኋት ላጣጣምኳት ኢህአዴግዬ ለምን አልዘፍንላትም ስል ባስብ ጊዜ ዝግጅቱ ትውስ ብሎኝ ይሄንን ሁሉ መዘብዘቤ፤ ‘እስቲ ልቤን አትስቀለው ቶሎ ዝፈንልኝ…’ ብለሽ ችኩል ስትይ ታየኝ። አንቺ እኮ ችኩል ነሽ እንደው ጥድፍ ጥድፍ ማለት ትወጃለሽ ‘ችኩል ብላ ካደረገች በኋላ እንዴት ላድርገው ብላ የምታማክር፤ ከገደለች በኋላ ቁም! ብላ የምታስጠነቅቅ ችኩል’ እያለ ሃገሩ ሲያማሽ መቼም ጆሮ ለባለቤቱ ባዳ ነው እና አልሰማሽም፤ እኔ አለሁልሽ አይደል እንዴ ታድያ ይሄው ነገርኩሽ (ማስታወሻሽን ያዢ ብቻ አንቺ) እና አዚምላት አዚምላት ያለኝ ምን የሚለውን ዘፈን መሰለሽ…
’ገዳይ ነሽ ገዳይ ነሽ በፍቅር ገዳይ ነሽ…
ገዳይ ነሽ ገዳይ ነሽ በመውደድ ገዳይ ነሽ’’
ምነው ሳቅሽ መጣ እወነቴን ነው ገዳይ ነሽኮ… ካላመንሽኝ ያለፉትን ሳምንታት ዜናዎች ዘወር ብለሽ ተመልከቺ… (በቅንፍም፤ ‘’ዞሮ መመልከት ብችል መቼ ገዳይ እሆን ነበር’’ ካልሽኝ አደንቅሻለሁ!) ሰው አንድ ይገድላል ሁለትም እሺ ይሁን ሴጣን ካሳሳተው ምን ይደረጋል፤ አንቺኮ በአንድ ሳምንት ብቻ አንድም ሳይሆን አስርም ሳይሆን መቶ ገዳይ መሆንሽን አለም የመዘገበልሽ ተዓምረኛ ነሽ! ደፍተር ያለው በደፍተሩ ልብ ያለው በልቡ ሁሉንም ጥፎልሻል….
ሰይጣን ብል ጊዜ ምን ትዝ አለኝ… (ስል መቼም ራስሽው ‘’ሚኒስቴር ጌታቸው ረዳ!’’ ሳትይኝ አትቀሪም።) በትክክል መልሰሻል! እኔ የምልሽ ኢህአዴግዬ እንደው እንዴት እንዴት አይነቱን ታበቅይ ጀመር ባክሽ…? የኛ ሀገር ሰው ለራሱ እንኳንስ እንዲህ በቀጥታ ሰድበሽው እና እንዲሁም ምን ለማለት ፈልጋ ነው… ብሎ ይጠምድሻል ጭራሽ ባለስልጣኖችሽ የገዛ ህዝብሽን ‘’ሰይጣኖች አጋንንቶች ጠንቋዮች…’’ እያሉ ሲሳደቡ ዝም ትያለሽ እንዴ! እንዴ…. ማህበረሰቡ እኮ ‘’ድሮም ሰው የውሎውን ነው የሚያወቀው’’ ብሎ በሌላ በሌላ እየጠረተረሽ ነው…!
ኢህአዴግዬ… ለመሆኑ እንዴት አለሽልኝ… ጤና እንዴት ይዞሻል… ጤና መንሳት እንዴት ይዞሻል አልልሽም… የገዛ ጤናሽን ነው የምጠይቅሽ፤ ስብሰባው ግምገማው እንዴት እያደረገሽ ነው፤ እውነቴን ነው የምልሽ እንዳንቺ ብርቱ የለም እኮ፤ ትዝ ይልሻል ከአስር ይሁን አስራ ምናምን አመት በፊት የመበስበስ አደጋ አጋጠማት ተብለሽ… ምነው እንኳ የገዛ አባትሽ አቶ መለስ ዜናዊ ነበሩ እኮ ‘’ኢህአዴግ የመበስበስ አደጋ ላይ ናት’’ ብለው ባደባባይ የተናገሩት… ከዛ የመበስበስ አደጋ ድነሽ ስንቱን ለአደጋ ዳረግሽው… ልልሽ ነበር እንዲህ አይባለም!
ይሄው ዛሬም ቃል በቃል መበስበስ ባይባልም ትልቅ የሆነ የመልካም አስተዳደር ችግር ውስጥ እንድለሽ ቱባ ቱባ ባለልጣኖችሽ ተሰባስበው ሲናገሩ ሰማን። እኔ የምልሽ አንዳንዴ እኮ አስማተኛ ነው የምትመስይኝ… በዘረፈ ብዙ ችግር ውስጥ ሆነሽ አለቀላት በቃ! ስትባይ አንቺቴ አፈርሽን ረገፍ ረገፍ አድርገሽ ተነስተሽ ነፍስ ዘርተሽ ዳግም አናታችን ላይ ጉብ ስትይ… የምርም አስማት የምትችዪ ነው የሚመስለኝ…
የሆነስ ሆነና ኢህአዴግዬ ዛሬ ዋናው ደብዳቤ ልጽፍለሽ ያነሳሳኝ ጉዳይ እየመሸ መሆኑን ልነግርሽ ፈልጌ ነው…
ጊዜው እንዴት እንደሚሮጥ ልብ ብለሻል። እንደ ዋዛ ሃያ አምስት አመት ሞላሽ እኮ… ትዝ ይለኛል አስራ አስራ ስምንት አመት የሞላሽ ጊዜ ‘’ኢህአዴግ እስካሁን ላጠፋችው ልጅነት ይዟት ነው ብለን እንምራታለን ከንግዲህ ግን አስራ ስምንት አመት ሞልቷታል እና ሃላፊነቱን ትወስዳለች’’ ብለን ከጓደኞቻችን ጋር ስናወራ ነበር… ይሄው ዛሬ ይሄንን ደብዳቤ ስጽፍልሽ ሩብ ምዕተ አመት ሆኖሻል… ይሄ እድሜ ታድያ ምራቅ ዋጥ የምታደርጊበት ብቻ ሳይሆን ያጠፋሽው የበደልሽውንም ተናዘሽ ሂስሽን ዋጥ የምታደርጊበት እድሜ ይመስለኛል!
እውነቴን ነው የምለሽ ኢህአዴግዬ እየመሸብሽ ነው… እንደው ዝም ብሎ ደመና ነው ብለሽ እንዳትታለዪ… ደምመና ሆኖ አይቀርም… (ብዬ ልቀኝብሽ እንዴ….) የምሬን ነው እየመሸ ነው… ልብ ብለሽ ብትመለከቺ ሰማዩ ጠቁሯል። ግዜው እየመሸብሽ ነው…
እና ምን ይጠበስ….? ያልሽኝ እነደሆነ ግን እንደሚከተለው እነግርሻለሁ…
እኔ እንደሌላው መሽቶብሻል እና ወደምትሄጂበት ሂጂ አልልሽም። እኔ እንደማምነው አንቺም ሌላ ሃገር፣ ሌላ ቤት የለሽም። የትም የምትሄጂበት አይኖርሽም… እና ዝም ብለሽ እረፍት አድርጊ…. ጋደም በዬ ኢህአዴግዬ! አረፍ በይ…! ቆመሽ አታቁሚን… ጋደም በይ እና አረፈሽ አሳርፊን እንጂ!
ዘንድሮ ምን ልብ አለኝ እንዳትይኝ እንጂ ልብ ብለሽ እንደሆነ፤ ቀድሞ ሰላማዊ ታጋይ የነበሩ ሁሉ በሰላማዊ ትግሉ ተስፋ ቆርጠው የትጥቅ ትግል አማራጭን መጠቀማቸው የመምሸቱ ምልክት ነው… በየቦታው የህዝቡ ሆድ ብሶት አደባባይ መውጣቱ በኦሮሚያ እና በጎንደር እንደሚታየው የሚሆነው ሁሉ የመምሸቱ ምልክት ነው…. አንቺም ብትሆኚ ለየጥያቄዎቹ ሁሉ ደምሽ ቱግ ቱግ እያለ ተኩሽ ተኩሽ የሚያሰኝሽ የመምሸቱ ምልክት ነው… እና ግዴየለሽም መሽቶ ሳይመሽ በፊት አረፍ በይ!
ታድያ እንዲያም ስልሽ እንደ ንጉስ ሚካኤል ስዑል ተኝተሽ ምሪን አይደለም። ‘’መሪውን ተረከቡኝ ልተኛበት… ልረፍበት’’ ብለሽ ጥሪ አድርጊ! አንቺስ ብትሆኝ ምን በወጣሽ ሃያ አምስት አመት ሙሉ ስትመሪ እና ስታማርሪ ትኖሪያለሽ! አለበለዛ ምሽቱ እየገፋ አንቺም እርጅናው እየተጫጫነሽ መጥቶ በድቅድቁ ጨለማ የወደቅሽ እንደሆነ ለመጠገን ከባድ ነው…. እና መሽቶ ሳይመሽ ጨለማው ሳይበረታ አረፍ በይ ኢህአዴግዬ!
አሳቢሽ
ከሰላምታ ጋር!

No comments:

Post a Comment

wanted officials