ወያኔ የደደቢቱን — እኛ የእለት የእለቱን
በደርግ የሥልጣን ዘመን የመጨረሻ ሰዐት ላይ ወያኔን በደንብ የሚያውቁት ሰዎች ዓላማው ምን እንደሆነ እቅድ ዝግጅቱ እስከምን እንደሚደርስ ኢትዮጵያን ለመያዝ ከበቃም ምን ሊያርግ እንደሚችል ተናግረው ነበር፡፡ ( አቶ አብርሀም ያይህና አቶ ገብረ መድህን አርአያ ይጠቃሳሉ፡፡) ነገር ግን የተነገረው ሁሉ የደርግን እድሜ ለማራዘም እንደሆነ ተደርጎ በመወሰዱና ተናጋሪዎቹንም የደርግ መልእክተኞች አድርጎ በማየት እንኳን ልቡን ጆሮውን የሰጣቸው ሰው ብዙ አልነበረም፡፡ (አቶ ገብረ መድህን ሰሚ አጣሁ ብለው ተስፋ ባለመቁረጥ ወያኔ ዛሬ ቤተ መንግስት ሆኖ የሚፈጽመው ገና ተሀህት እያለ ያቀደ የወጠነውን እንደሆነ ዛሬም እየነገሩን ነው፡፡
ወያኔ የደደቢት ዓላማውን ተግባራዊ ለማድረግ በህዝብና በሀገር ላይ ያደርሰዋል ተብሎ የተነገረንንና ልንከላከለው ቀርቶ ልንሰማው ያልፈቀድነውን ድርጊት ደረጃ በደረጃ በተግባር ሲፈጸም አይተናል፡፡ ስቃይና መከራውንም ተራ በተራ እየደረሰብን አስተናግደናል፡፡ ግን ተቀዋሚዎች በጥቅሉም ተበዳዮች ከዚህ ተምረን በረጅም አስበን፣ ዘላቂ ግብ አቅደን፣ የትግል ስትራቴጂ ነድፈን፣ መክረንና ተባብረን መነሳቱ አልሆን ብሎን እዛና እዚህ ቆመን ዛሬም የእለት የእለቱን እየያዝን እንጮሀለን፡፡ ይህ ደግሞ ለወያኔ ይበልጥ የልብ ልብ እየሰጠው ነገረ ስራው ሁሉ ከአምባገነን ወደ ቅኝ ገዢ ተግባር ተቀይሯል፡፡
ወያኔ ለ17 አመታት ጠመንጃ ነክሶ ሲታገል ሲያሸንፍም ሆነ ሲሸነፍ፣ ነጻ መሬት ሲይዝም ሆነ ሲነጠቅ ከመነሻው ያነገበውን ዓላማና ዘላቂ ግብ አልጣለም ወይንም አለወጠም፡፡ የአንድ አካባቢ መንግሥትነትን አልሞ ተነስቶ ሙሉ ኢትዮጵያን ለመያዝ መብቃቱም ከዓላማው ፈቀቅ፣ ከግቡም ዘነፍ አላደረገውም፡፡ ኢትዮጵያን በሙሉ መያዝ እንደሚችል ሲያረጋግጥ ከወቅቱ ጋር መስሎ ተመሳስሎ በተለይም የአሜሪካንን አረንጓዴ መብራት በማግኘት የአራት ኪሎ መንገዱን ለማሳላጥ የምዕራቡን ርዕዮት የተቀበለ ቢመስልም የሚታለለውን ለማታለል የሚዘናጋውን ለማዘናጋት ተጠቀመበት እንጂ ደደቢት የለበሳትን ማሌ እንኳን ያኔ ዛሬም አልለወጠ፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ተብሎ በቆየበት ሀያ አራት አመታትም ከዓላማውና ከእቅዱ ውጪ የሚመስሉ አንዳንድ ተግባራትን የፈጸመ ቢመስልም ውጥረት ማርገቢያ፣ ወንዝ መሻገሪያ፣ ተቃውሞ ማስተንፈሻ ማስመሰያ እንጂ ከተነሳበት ዓላማ ውጪ የሆኑና የጀመረውን ወደ ግቡ የሚያደርስ የጉዞ መስመር የሚያስለውጡ አይደሉም፡፡ ይህም ዓላማው ምንም ይሁን ምን ከመነሻው ወደ ትግል የገባው በጥልቀት አስቦ በረዥም አቅዶ በጠንካራ መሰረት ላይ ቆሞ መሆኑን ያሳያል፡፡
በአንጻሩ በተለያየ ግዜ ተመስርተው የምናያቸው አብዛኛዎቹ ተቀዋሚ ፓርቲዎች የእንቅስቃሴያቸው ጅማሮ ፓርቲ ለመመስረት የሚያስፈልገውን ሰነድ ከማዘጋጀት የዘለለ አይደለም፡፡ ፓርቲዎቹ መነሻ ዓላማቸው፣ መሄጃ መንገዳቸው፣ ሊያጋጥሙዋቸው የሚችሉ ችግሮችና መፍትሄያቸው፣ እንዲሁም መድረሻ ግባቸው በጥልቀት ታስቦ በረዥም ታቅዶ በጠንካራ መሰረት ላይ የሚቆሙ ባለመሆናቸው ወያኔን እየተከተሉ ከመጮህና በሚሰጣቸው አጀንዳዎች ከመጠመድ ያለፈ ስራ ሲሰሩ ማየት አልተቻለም፡፡
ይህም በመሆኑ ራሳቸው የሚያራምዱት ትግል መኖሩ ቀርቶ በተለያየ ግዜ ህብረተሰቡ ያቀጣጠላቸው ተቃውሞዎች ለውጤት እንዲበቁ ለማድረግ የሚያስችል አመራር መስጠቱ ቢቀር አቅጣጫ የማስያዝና የማስተባበር ስራ እንኳን መስራት አልቻሉም፡፡ በዚህም የትናንቱን የኦሮምያ አካባቢ ህዝብዊ ንቅናቄ ጨምሮ በተለያየ ግዜ የተካሄዱ የህዝብ ተቃውሞዎችና የይስሙላ ምርጫዎች ለበርካታ ዜጎች ሞት እስር መደብደብና ከቤት ንብረት መፈናቀል ምክንያት ከመሆን አልፈው ውጤት ሊያመጡ ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡
በሀያ አራት አመታት ውስጥ በውጪም በውስጥም የብዙ ፓርቲዎችን ስም ሰምተናል፡፡ ነገር ግን መነሻ ዓላማውንና መድረሻ ግቡን በውል ያወቀ ለዛም በበቂ የተዘጋጀና ከቀን ወደ ቀን እየጎለበተ ለመሄድ በሚያስችለው ጽኑ መሰረት ላይ የቆመ ጠንካራ ፓርቲ ግን ለማየት አልተቻለም፡፡ ድክመትን አምኖ ጉድለትን ተረድቶ ብቻየን የትም መድረስ አልችልም በማለት መረዳዳትና መደጋገፍ ሀይል ለመፍጠር ማስቻሉ ቢታወቅም ይህንንም ማየት አልተቻለም፡፡ በመሆኑም በዚህ ሁኔታ ብዙ ፓርቲዎች ብቅ እያሉ ጠፍተዋል፤ ብዙዎች እንደ ቡና ውሀ እያነሱ ሄደው ዛሬ መኖር አለመኖራቸው በውል አይታወቅም፤ ብዙዎች የእንቧይ ካብ ሆነዋል፡፡ ዛሬ ፓርቲ ተብሎ ለመጠራት የሚያበቃውን መስፈርት የሚያሟሉ ስንት ፓርቲዎች ይኖሩ ይሆን!
ያለፈው አልፏል ብንልም አሁንም ከሰሞነኛው የሀገራችን ሁኔታ ትምህርት ተወስዶ የወያኔን እግር እየተከተሉና አጀንዳውን እየተቀበሉ ከመቃወም ለመወጣት የሚያስችል ጅምር ስራ አለመታየቱ ፈቺ ያጣ አንቆቅልሻችን ነው፡፡ ወያኔ ተቃውሞ በተነሳበት ቁጥር የሚንቀሳቀሰው በሀይል ጨፍልቆ ጸጥ ለማድረግ ብቻ ሳይሆን ከዛ በኋላ ወደ ግቡ የሚያደርገውን ጉዞ ሊያሰናክል የሚችል ሌላ ተቃውሞ መቼም በማንምና በየትም አካባቢ ዳግም እንዳይነሳ ለማድረግ ያስችለኛል የሚለውን ርምጃ ለመውሰድ ነው፡፡ ሰሞኑን በኦሮምያ የተነሳውን ተቃውሞ ለመጨፍለቅ ግድያ የፈጸሙትን አረመኔዎች ማመስገኑ ነገም እንዲገሉለት ማደፋፈሩና ዛሬ ያልገደሉትንም ማነሳሳቱና ማዘጋጀቱ ነው፡፡ ዜጎችን እያደነ ማሰሩ ለወደፊት የሚያነሳሱም ሆኑ የሚመሩ እንዳይኖሩ ነው፡፡ተቃውሞ በተቀጣጠለባቸው አካባቢዎች ወታደራዊ አገዛዝ ማስፈኑ ዛሬ ለተቃውሞ የወጡትን ቅስም ለመስበርና ዳግም ተቃውሞ እንዳያስቡ ቅስማቸውን ለመስበርና ሌላውም በእነርሱ የደረሰውን አይቶ ወያኔን መቃወመን እንዳይሞክረው ለማስፈራራት ነው፤ሌላ ሌላውም ኢሰብአዊ ድርጊት አላማና ግቡ ወያኔ የተነሳለትን ዓላማ የሚያስተው ወደ ግቡ ከሚያደርገው ግስጋሴም የሚገታው ብም ለሥልጣኑ የሚያሰጋው ተቃውሞ ወደ ፊት እንዳይገጥመው ለማድረግ ነው፡፡ ለዛሬ ብቻ ሳይሆን ለወደፊቱም ነው የሚሰራው፡፡
ይህን ተከትሎ በተቃውሞው ጎራ የታየው መነሳሳት መልካም ቢሆንም ከተለመደው የእለት ተቃውሞ ያለፈ ነገር አለመታየቱ ለምን የሚል ጥያቄ ያነሳል፡፡ በርካታ ድርጅቶች እስከመኖራቸው የረሳናቸው ሳይቀሩ የወያኔን አረመኔያዊ ድርጊት በማውገዝ የህዝቡን ተነሳሽነት በማድነቅና የመተባበርን አስፈላጊነትና ወቅታዊነት በመግለጽ ከየቤታቸው ሆነው መግለጫ አውጥተዋል፡፡እንደደረሰው እልቂት እንደ ወያኔ አረመኔነት ግን እስካሁን ከዚህ ያለፈ ተግባር ይጠበቅባቸው ነበር፣ ግን የለም፡፡
ወያኔ የደደቢቱን ዓላማውን በተለያየ መንገድና ዘዴ ተግባራዊ ሲያደርግ እኛ አንድ ዓላማ ኖሮን፣ ዓላማችንን ተግባራዊ ለማድረግ ወደሚያስችለን ግባችን ለመጓዝ የሚያስችለንን ስትራቴጂ ነድፈን፣ በቂ ዝግጅት አድርገንና ጥንካሬ ፈጥረን ከመንቀሳቀስ ይልቅ ተራርቀን የወያኔን አግር እየተከተልን ከምናደርገው ተቃውሞ አልወጣንም፡፡ ይህም ሕዝብን ለመስዋዕትነት ወያኔንም ለበለጠ እብሪትና አንባገነንነት ያበቃው በመሆኑ ኢትዮጵያ ዛሬም የግፍና የጅምላ ግድያ እያስተናገደች ነው፡፡ ፖለቲከኞች ይህ አስቆጥቶአቸውና ቁጭት አሳድባቸው ከዚህ በኋላ ሌላ እልቂት ማየት የለብንም በቃ በማለት ተጠራርተው ሸንጎ ተቀምጠው መላ ሊመቱ፣ እቅድ ሊያወጡና ስንዴና እንክርዳዱ ተለይቶ በአጭር ግዜ ከተከታይነት ወደ ቀዳሚነት መሸጋገር የሚያስችል ስትራቴጂ መንደፍ በጀመሩ ነበር፡፡
የብዙዎቹ መነሻ ዓላማቸው ወያኔን መጣል፣ መድረሻ ግባቸው ራሳቸውን ለሥልጣን ማብቃት የሚል ይመስላል፡፡ የመሌየታውና መራራቃቸውም ምክንያት ይሄው ነው፡፡ ግና ይህም ሆኖወያኔን እንዴትና በምን ሁኔታ እንደሚጥሉት ያላቀዱና ለሚያጋጥማቸው ጥሩም ሆነ መጥፎ ነገር ዝግጅትም አማራጭም የሌላቸው መሆኑ ነው ወያኔን እየተከተሉ ከመቃወም ለማለፍ ያላስቻላቸው፡፡ ወያኔ ግን ደደቢት የቀረጸውን ዓላማውን እንዴት መቼና በምን ሁኔታ ተግባራዊ አንደሚያደርግ ብቻ ሳይሆን እነማንን መጠቀም እንዳለበት ፣እንዲሁም ወደ ግቡ የሚያደርገውን ጉዞ ሊያደናቅፉ ይችላሉ ያላቸውን የመለየትና እንዴት መቋቋምና ማዳከም እንደሚችል ጭምር ነው ከመነሻው ያሰበው ያቀደውና የተዘጋጀው፡፡
የባከነው ግዜ ያስቆጫል ፣መጪው ግዜ ደግሞ ይበልጥ ያሳስባል፡፡ወያኔ ከደደቢት ዓላማና ግቡ ዝንፍ እንደማይል በተግባር አሳይቷል፡፡ ስለሆነም በወያኔ አገዛዝ ውስጥ ሆኖ ስለ ዴሞክራሲ፣ ስለ ህግ የበላይነት፣ ስለ ሰብአዊ መብት አይደለም ራሱ ስላጸደቀው ህገ መንግስት መከበር መጠየቅ አይቻልም፡፡ ወያኔ ወደ ግቡ የሚያደርገውን ጉዞ ሰርዞ ከዴሞክራሲ ሊወዳጅ፣ ለህግ ራሱን ሊያስገዛ፣ የዜጎችን ሰብአዊ መብት ሊያከብር ፈጽሞ የማይቻለው ብቻ አይደለም የማያስበው ነው፡፡ አንዳንድ ወገኖች የሚማልሉበትና የሚታለሉበት በዛን ሰሞን የሰማነው አይነት የመልካም አስተዳደር እጦት የሙስና መንሰራፋት የፍርድ ቤቶች ችግር ወዘተ በወያኔዎች የሚነገረው መንገዳቸውን ለማጽዳት እንጂ አላማና ግባቸውን በመለወጥ አይደለም፡፡
ነገሩ ይህ ከሆነ መፍትሄው አንድ ነው፤የወያኔን የአገዛዝ ዘመን ማሳጠር፡፡ይህ ደግሞ እስከዛሬ በመጣንበት መንገድም ሆነ እቅድና ስልት የሚሳካ አይሆንም፡፡ ወያኔ ሲያስር ሲገድል ሲደበድብ ብቻ እየጮሁ ከወያኔ አገዛዝ መገላገል አልተቻለም ወደፊትም አይቻልም፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያን ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ማብቃት በሚል የጋራ ዓላማ በመሰባሰብ ይህን ዓላማ ከግብ ለማድረስ የሚኬድባቸው መንገዶችን፣ የሚደረጉ ትግሎችን የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን የሚጠይቁ መስዋእትነቶችን ወዘተ በጥልቀት ተወያይቶ ተስማምቶና አቅዶ በጠንካራ መሰረት ላይ ቆሞ ለመጀመር ግዜው አሁን ነው፡፡ ለነጻነት እየጮሁ በወያኔ ጥይት ያለቁት ሰማእታት መሰዋእትነት የማይቀሰቅሰው ዜጋ ካለ እሱ ማነው?
No comments:
Post a Comment