Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Sunday, January 17, 2016

የቅዱስ ፓትርያርኩና የማኅበረ ቅዱሳን ልዩነት ወደ ሃይማኖት አደገ

ከናቡቴ የተዋህዶ ድምጽ
በፓትርያርክነት ከተሾሙበት ጊዜ ጀምሮ ስለ ማኅበረ ቅዱሳን መልካም የማይመኙት አቡነ ማትያስ ከማኅበሩ ጋር ያላቸው ልዩነት የዓላማ እና የሃይማኖት መሆኑን አረጋገጡ፡፡ ጥር ፫ ቀን ፳፻ወ፰ ዓ.ም በእንግዳ መቀበያ ቢሯቸው ውስጥ ከተሐድሶ መናፍቃን አንቀሳቃሽ “የኮሌጅ ተወካይ ነን” ባዮች ጋር ባደረጉት ስብሰባ የተሐድሶ አቀንቃኞችን ደግፈውና ማኅበሩን ነቅፈው እስከ ሞት ድረስ ለመታገል እንደ ቆረጡ ተናግረዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያን በሕይወት እያለ ቅዱስ ብላ የምትጠራው ብቸኛ ሰው ፓትርያርክ ነው፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ አቡነ ማትያስ ግን ለስሙ የሚመጥን ግብር መሥራት ሲሳናቸው ብዙ ጊዜ ተስተውለዋል፡፡ እስከ አሁን በብዙ ምእመናን ዘንድ ስሕተታቸው ጉዳዮችን ካለመረዳትና በዙሪያቸው ያሉት አካላት ከሚያቀርቡላቸው የተሳሳተ መረጃ የተነሣ እንደሆነ ተቆጥሮ በበጎ ታልፈው ነበር፡፡
አሁን ግን ቤተ ክርስቲያንን ለተሐድሶ መናፍቃን አሳልፈው ለመስጠት መዘጋጀታቸውን አረጋግጠውልናል፡፡ ይህ ደግሞ ቅድስናቸውን ብቻ ሳይሆን አማኝነታቸውንም ጥርጣሬ ውስጥ የሚያስገባ ነው፡፡ አይችሉም እንጂ ማኅበረ ቅዱሳንን ማፍረስ መብታቸው ሊሆን ይችላል፡፡ ማኅበረ ቅዱሳንን አይደለም አንድ ግለሰብ የማኅበሩ አባላትም ማፍረስ አይችሉም፡፡ ማኅበሩን የመሠረተው እግዚአብሔር እንጂ ግለሰቦች አይደሉም፡፡ ችግሩ የማኅበሩ ከሣሾች እንደ ጸሓፍት ፈሪሳውያን በሚያዩት ብቻ ስለሚያምኑ ማኅበሩን ማፍረስ ቀላል ይመስላቸዋል፡፡
ጸሓፍት ፈሪሳውያን ሰው ሆኖ የተገለጠውን አምላክ ሥጋ ለብሶ ስላዩት ብቻ የእግዚአብሔር ልጅ ነኝ ይላል ብለው እንደ ከሰሱት ዛሬም የግብር ልጆቻቸው የማኅበሩን አባላት ሥጋዊ ተክለ ሰብእና ብቻ ተመልክተው በጉልበት፣ በሥልጣንና በገንዘብ እንበልጣቸዋልንና ማኅበሩን ማፍረስ ቀላል ነው ብለው እንዲያስቡ ሆኑ፡፡ ይህ አለመማር ወይም የተማሩትን አለማስተዋል እንጂ እውነት አይደለም፡፡
abune mathias
የሰበሰቧቸው የተሐድሶ መናፍቃን አቀንቃኝ ደቀ መዛሙርት ወደ ግቢያቸው ተመልሰው ኦርቶዶክሳውያኑን ደቀ መዛሙርት “እናንተ ባለ ማርያሞች መጣንላችሁ፣ ከኮሌጁ ብቻ ሳይሆን ከቤተ ክረስቲያንም ጠራርገን ነው የምናስወጣችሁ” በማለት የቅዱስ ፓትርያርኩን ቃል መዶሻ አድርገው ሊቀጠቅጧቸው እንደተነሡ አረጋግጠውላቸዋል፡፡ ቅዱስ ፓትርያርኩ ማኅበረ ቅዱሳንን ማፍረስ ማለት በብዙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ምእመናንን ከቤተ ክርስቲያን ማባረር መሆኑን ባያውቁት እንኳን ይህ ለተሐድሶ መናፍቃን ሰርግና ምላሽ እንደሆነ ያጡታል ብዬ ግን አላስብም፡፡ ቅዱስ አባታችን ለዓላማዎ እስከ ሞት ድረስ መታመንዎ መልካም ነውi መረዳት ያለበዎት ግን እርስዎ ለሰይጣናዊ ተልእኮዎ እስከ ሞት ድረስ የሚታመኑ እንደሆነው ሁሉ እኛ ኦርቶዶክሳውያንም መንግሥተ ሰማያት ለምንገባበት ቤተ ክርስቲያንን የመጠበቅ ዓላማችን እስከ ሞት ለመታመን የቆረጥነው የተጠመቅን ዕለት መሆኑን ነው፡፡

No comments:

Post a Comment

wanted officials