ታሪኩ አባዳማ ጥር 2008
ህዝባዊ አመፅ ሲቀጣጠል ገዢ ሀይሎች ብርክ ይይዛቸዋል። እናም ይወራጫሉ ፣ እጃቸው ላይ ባለ በሌለ ነገር ሁሉ ተጠቅመው የህዝቡን ቁጣ ቢቻል ለማዳፈን ካልሆነም ለማብረድ ይራወጣሉ። ከታሰርኩበት ሰንሰለት በቀር የማጣው ነገር የለም ብሎ የተነሳን ህዝብ ግን ምንም አይነት የጭቆና እና አፈና እርምጃ ሊገታው እንደማይችል ከቅርብም ከሩቅም ታሪክ ተምረናል። ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ የፈነዳው ቁጣ በጥይት እሩምታ ፣ በቦምብ ውርወራ ጋጋታ ፣ በጅምላ እስር እና የተዛባ ፕሮፓጋንዳ የሚገታ አይደለም – ዜጎች የግፍ ቀንበሩን ሰብረው ለመጣል እየተዋደቁ ነው።
Grenade attacks in Ethiopian universities
የዲላ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የቦምብ ጥቃት ከተፈጸመባቸው በኋላ ዩኒቨርሲቲውን ለቀው ሲወጡ
ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ውስጥ ወያኔ አደባባይ ተኩስ ከፍቶ ከፈጃቸው ዜጎች ሌላ በትምህርት ተቋማት አካባቢ በንፁሀን ለጋ ወጣት ተማሪዎች ላይ ተሰውረው ቦምብ የሚወረውሩ ካድሬዎቹን አዝምቷል። እነኝህ ቦምብ ወርዋሪ ካድሬዎች ለትምህርት ተቋማቱ እንግዳ አይደሉም። በየትምህርት ተቋማቱ እንደ መደበኛ ተማሪ ቀን ቀን ደብተር ይዘው አንዴ ከዚህኛው ሌላ ጊዜ ከዚያኛው ተቋም እየተመዘገቡ ውሎ አዳራቸውን በዩንቨርሲቲ ውስጥ ያደረጉ ሰላዮች ናቸው – ተማሪው እርሳስ እና ደብተር ተሸክሞ ሲመጣ እነሱ ደግሞ ቦምብ እና ጥይት በቦርሳቸው ሸክፈው ከች ይላሉ።
በቅርቡ አንድ የዲላ ዩንቨረሲቲ ተማሪ በማህበራዊ ድረ-ገፅ ላይ ይፋ እንዳደረገው እነኝህ ቦምብ ታጥቀው ዩንቨርሲቲ የሚኖሩ ካድሬዎች እንደሌላው ተማሪ ዓመታት ቆጥረው ዲግሪ ተቀብለው የሚመረቁ አይደሉም። ከዓመት ዓመት እዚያው ናቸው – ዘንድሮ ማኔጅመንት ፣ አምና ኢኮነሚክስ ፣ ካቻ አምና ሶሲዮለጂ… ተማሪ መሆናቸውን እየጠቀሱ ከተማሪው መንጋ ጋር ተቀላቅለው በግቢው ይወጣሉ ይገባሉ። ዓመቱ ሲጠናቀቅ ተማሪው የትምህርት ውጤቱን ሪፖርት ፣ እነሱ ደግሞ የስለላ አውታራቸው ያከናወነውን የእስር እና ግድያ ሪፖርት በሻንጣቸው ይዘው ተማሪ ወደ ወላጁ እነሱ ወደ ጠቅላይ ጦር ሰፈራቸው ይመለሳሉ።
ወያኔ የቀየሰው የአፈና አውታር በአገራችን ሆነ በውጭ የመንግስታት ታሪክ ውስጥ ከዚህ ቀደም በየትኛውም ምድር ተደርጎ ያልታየ ፍፁም ወሮ በላነት ፣ ፍፁም ህገወጥነት የተመላበት ነው። ይህም በመሆኑ ብዙዎች እውን ይህ አድራጎት መንግስት ፈፀሞት ይሆን? ብለው በጥርጣሬ መንፈስ እንዲያሰላስሉ አድርጓቸዋል። መንግስት እና ወሮበላነት ተዳቅለው ፀያፍ እና ለጆሮ የሚዘገንን ግፍ በዜጎች ላይ የሚፈፅሙበት ታሪካዊ እውነት ግን በአገራችን ሞልቶ ተርፏል።
በአሮማያ ፣ በዲላ ፣ በጂማ… ዩንቨርሲቲዎች በለጋ ወጣቶች ላይ ቦምቡን የወረወሩት እነማን ናቸው?
ወያኔ እያጠራሁ ነው ይለናል – እኛ ግን እንላለን ሙሉ ዘመናቸውን ከጠመንጃ እና ቦምብ በስተቀር ሌላ ሙያ መኖሩን የማያውቁት የወያኔ ምልምሎች የፈፀሙት ለመሆኑ ቅንጣት አንጠራጠርም።
ማን የሚሉት ኢትዮጵያዊ ወላጅ ነው በድሀ አቅሙ ያሳደገውን ለወግ ማዕረግ እንዲበቃ የሚሳሳለትን ለጋ ልጁን ቦምብ አሸክሞ ትምህርት ቤት የሚሰድ? ምንስ ለማትረፍ?
ከጥቂት ዓመታት በፊት የእህቴ ልጅ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን እንዳጠናቀቀ ደብዳቤ ፃፈልኝ። የህክምና ትምህርት ለመከታተል ወደ ተመደበበት ዩንቨርሲቲ ከመንቀሳቀሱ በፊት ላፕ ቶፕ (ኮምፒዩተር) እንደሚያስፈልገው እና ባስቸኳይ እንድልክለት አጥብቆ አሳሰበኝ። የእናቱን አቅም ስለማውቅ እና አንድም ላገኘው መልካም ውጤት ማበረታቻ ፣ ሁለትም ወደ ፊት በርትቶ ቢማር የበለጠ ሽልማት እንደሚጠብቀው ጭምር የትጋት ማጎልበቻ ይሆናል ብዬ አምኜበት ሳላመነታ የጠየቀኝን አደረኩለት። አንድ ወላጅ ወይንም ዘመድ ልጁ ወደ ላቀ የትምህርት ደረጃ ሲሸጋገር ባለው አቅም ሁሉ የትምህርት መሳሪያዎች እንዲሟሉ ብርቱ ድጋፍ ማድረግ ያለ ነው።
ነገ ይጦረኛል ይጠይቀኛል የሚል ወላጅ እርሳስ እና ደብተር ሸማምቶ ‘ይቅናህ ፣ በርታ’ ብሎ እንጂ እንካ ይቺን ቦምብ ተማሪ ጓደኞችህ ላይ አፈንዳ ብሎ ልጁን ወደ ትምህርት ገበታ ሲልክ ታይቶም ተሰምቶም አይታወቅም። በዚህ ረገድ ወያኔ ቦምብ ወርዋሪ ‘ተማሪዎችን’ ዩንቨርሲቲ ውስጥ በመመደብ የፈፀመው ወንጀል በውነት እጅግ የሚያሳዝን ብቻ ሳይሆን የሚዘገንን – ሥርዓቱ ምን ያህል አረመኔአዊ መሆኑን ጭምር ቁልጭ አድርጎ የሚያረጋግጥ ነው። ይህ አድራጎት ወያኔ ዛሬ የደረሰበትን የፖለቲካ ኪሳራ ጭምር አጉልቶ ያሳያል።
በየትምህርት ተቋማቱ በሀላፊነት ወንበር ላይ ተቀምጠው የድሀውን ልጅ በ ቦምብ የሚያስጨርሱ ሹማምንት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የወንጀሉ ተባባሪ ናቸው። የጥበብ ገበያ ተቋማት ለነብሰ ገዳይ የወያኔ ሰላዮች ክፍት ሆነው መለቀቃቸው ትልቁ ተጠያቂነት በነሱ ላይ ይወድቃል። የወያኔ ሰላዮች ከነ ቦምባቸው በየተቋማቱ አገልግሎት እንዲያገኙ – እንደ መኝታ ፣ ምግብ ፣ መታወቂያ ብሎም በትምህርት ክፍሎች እየተዘዋወሩ ስለላ እንዲፈፅሙ ሁኔታው የተመቻቸላቸው በነኝሁ አድር ባይ ሹማምንት ነው።
መደበኛ ተማሪ ለመሆን መሟላት የሚገባውን የትምህርት ደረጃ የማያሟሉ ግለሰቦች በምን አግባብ ዩንቨርሲቲ ማህበረሰብ ውስጥ እንደ ተማሪ መኖር ተፈቀደላቸው። እርግጥ ነው ሹማምንቱ ራሳቸው በምን መመዘኛ ተቀጥረው ወንበር እንደሚያሞቁ ተብሎ ያለቀለት ጉዳይ ነው። በዘር ግንድ እንጂ በብቃት ተመዝነው ሀላፊነት ላይ እንዳልተቀመጡ ዛሬ እኛ ብቻ ሳይሆን ወያኔ ራሱ የሚያፍርበት ውነት ሆኗል። ውነቱ በዘር ከለላ መሾማቸው ብቻ አይደለም – የሙያ ብቃት እና ስነምግባር የሚጎድላቸው በመሆኑ በጭፍን የድርጅት ታማኝነት ተራ የወሮበላ ድርጊት እንዲስፋፋ አድርገዋል።
ባንዳ ሹማምንት በሁሉም የአገልግሎት ዘርፍ ውስጥ ከላይ እስከ ታች መሰማራታቸውን እናውቃለን – እንደ ቆስጠንጢኖስ በርሔ ያሉ ዲግሪ እንደ ሽንኩርት ሸምተው ዶክተር የተባሉ ሰዎች ዩንቨርሲቲዎቹን ማጨናነቃቸውም ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው። እንደነኝህ አይነት መንፈሰ ደካማ ግለሰቦች የሞራል ግዴታ ብሎ ነገር አያውቃቸውም። ለዚህም ነው ዩንቨርሲቲዎች በ ቦምብ ለሚፅፉ ፣ የጥበብን ሀ ሁ በማይረዱ ማይም ነብሰ ገዳዮች ተበክሎ የምናየው።
ዛሬ በመላ አገሪቱ እየተካሄደ ያለው ግብግብ በቅፅበት ለመጨረሻው ድል ይበቃል የሚል ቅዠት የለንም። ትግሉ የደረሰበትን ደረጃ ስንመረምር ግን ካምና ይልቅ ዘንድሮ እናም ከዘንድሮ ይልቅ ለከርሞ ህዝባዊ ሀይላችን እየፈረጠመ ለድል መብቃቱ አይቀሬ መሆኑን በሙሉ ልብ እንናገራለን። ትናንት በጎጥ ከፋፍለው እርስ በርስ በጥርጣሬ እንድንተያይ መደረጉን በፀፀት እያሰብን ዛሬ በጋራ ላንዲት ኢትዮጵያ ህልውና መረጋገጥ ተሰልፈናል። ወያኔ ስልጣን ላይ ሳለ የትኛውም ዜጋ ወይንም ብሔረሰብ በተናጠል ሰብአዊ ክብሩ ሊረጋገጥ እንደማይችል በማያሻማ ሁኔታ የተረዳንበት ወቅት ላይ ነን። የሁሉም ዜጎች ሰብአዊ ፣ ባህላዊ እና ስነልቦናዊ ክብር በህግ የበላይነት ተረጋግጦ ለማየት የግድ ወያኔ መንበረከክ አለበት ብሎ የተነሳን ህዝብ ካለመበት ሳይደርስ የሚገታው ሀይል የለም።
ወያኔ በስልጣን ላይ እስካለ ድረስ ወላጆች ልጆቻቸውን ዩንቨርሲቲ ሲልኩ እርሳስ እና ደብተር ብቻ ሳይሆን የጥይት እና ቦምብ መከላከያ ጭንብል ለመግዛት የሚገደዱበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ይኼ እጅግ ሊያሳስበን ይገባል – ልናስቆመውም የግድ ይለናል። በ ቦምብ የሚፅፉ ታማሪዎች በፈጠሩት አደጋ የብዙ ለጋ ወጣቶች ህይወት ተቀጥፏል – የወጣቶቹ ራዕይ የቤተሰቦቻቸውም ተስፋ ተዳፍኗል። ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ ዩንቨርሲቲዎች የሰላም አየር ተነፍገው በስጋት እና መሸማቀቅ ድባብ ውስጥ እንዲወድቁ ተደርጓል። እየተሸማቀቁ ምርምር ፣ እየተደናበሩ ፈጠራ የለም። ተማሪዎች ግቢያቸውን ጥለው እንዲበረግጉ በለጋ ዕድሜያቸው ካቅማቸው በላይ የሆነ ግፍ እየተፈፀመባቸው ነው።
ዩንቨርሲቲዎች በቁማቸው በድን እንዲሆኑ ወያኔ የወሰነው ዛሬ አይመሰለኝም። ምትክ የማይገኝላቸውን ታላላቅ ልምድ ያካበቱ መምህራንን ጨምሮ ብቃት ያላቸውን አካደሚሽያን መንጥሮ ያባረረው ገና ስልጣን በያዘ ማግስት እንደነበር ሊታወስ ይገባል። ቦምብ ወርዋሪዎች በተማሪነት ስም ግቢውን ተረክበውታል – ይህ ደግሞ ኢትዮጵያን ለማጥፋት ወያኔ ከወጠነው አጠቃላይ ሴራ ተለይቶ የሚታይ አይደለም።
ምርጫችን በእጃችን ነው – አገራችን በፈጠራ ችሎታ የዳበረ ልምድ ባላቸው ዜጎች እንጂ ቦምብ መፍታት እና መግጠም በተካኑ ማይም ነብሰ ገዳዮች እጅ ወድቃ እንዳትቀር በቁርጠኝነት መቆም ይኖርብናል። በቦምብ የሚፅፉ ተማሪዎች ተወግደው ዩንቨርሲቲዎች የጥበብ መቅሰሚያ አምባ እንዲሆኑ ወጣት ተማሪዎች ያቀጣጠሉትን ትግል ከልብ ልናግዝ ይገባል።
No comments:
Post a Comment