6,5 ሚሊዮን ሕዝብ የምግብ ርዳታ መሻቱ
የዓለም የምግብ ድርጅት በዘንድሮዉ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2014 ለ6,5 ሚሊዮን ኢትዮጵያዉያን የምግብ ርዳታ ለመስጠት መዘጋጀቱን የጠቀሰ ዘገባ ሰሞኑን ይፋ ሆኗል። በኢትዮጵያ ግብርና ሚኒስቴር የምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር በሀገሪቱ የምግብ ርዳታ የሚያስፈልገዉ ሕዝብ ከ2,7 ሚሊዮን እንደማይበልጥ ያመለክታሉ።
ሮይተር የዓለም የምግብ መርሃ ግብር በእንግሊዝኛ ምህጻሩ WFP ኢትዮጵያ በገጠማት የአንበጣ ወረርሽ፣ የዝናብ እጥረትና በጎረቤት ሀገር በሚካሄድ ጦርነት ምክንያት የምግብ አቅርቦት የሚያስፈልጋቸዉን 6,5 ሚሊዮን ወገኖች በዚህ ዓመት ለመርዳት አቅጃለሁ ሲል ጄኔቫ ላይ መግለፁን ዘግቧል። በኢትዮጵያ ግብርና ሚኒስቴር የምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ ወልደ ሚካኤል ድርጅቱ በጥቅሉ በሚያካሂዳቸዉ ፕሮጀክቶች የታቀፉትን እና የዉጭ ስደተኞችን እንዲሁም ሊፈናቀሉ ይችላሉ ተብለዉ የሚገመቱ ወገኖችን ጨምሮ ጠቅሶ ሊሆን እንደሚችል ነዉ የሚያስረዱት።
ሮይተርስ የጠቀሳቸዉ የWFP ቃል አቀባይ ኤልዛቤት ባየርስ ወቅታዊዉን የደቡብ ሱዳንን ዜጎች ወደኢትዮጵያ መሰደድ ምክንያት በማድረግ ለዘጋቢዎች በሰጡት ማብራሪያ ሀገሪቱ ከተለያዩ አካባቢዎች የሚመጡ ስደተኞችን ጨምራ የምግብ ርዳታ ለማቅረብ ድጋፍ እንደሚያስፈልጋት ለማሳየት መሞከራቸዉን ነዉ ያመለከቱት።
«በ2014 WFP 6,5 ሚሊዮን ገደማ ኢትዮጵያ ዉስጥ ለችግር የተጋለጡ ሰዎችን ለመደገፍ አቅዷል። ይህንንም የምናከናዉነዉ በሶስት ትላልቅ መስመሮች አማካኝነት ነዉ፤ የረዥም ጊዜዉ የምግብ ዋስትናን ማጠናከር በሚያስችለዉ ምግብ ለሥራ በተሰኘዉ ፕሮጀከት፤ በድርቅና በሌላ አደጋ ለተጎዱ ኢትዮጵያዉያን የአስቸኳይ የምግብ ርዳታ፤ እንዲሁም ለስደተኞች የህይወት ማዳኛ ርዳታ የሚሉት ናቸዉ። ምክንያቱም ደቡብ ሱዳን ዉስጥ ያለዉ ግጭት ለኢትዮጵያና ለሌሎች ጎረቤት ሃገራት ስደተኞችን በማስተናገድ ረገድ ከፍተኛ የሰብዓዊ ተግዳሮት ፈጥሯል።»
WFP ከመንግስት ጋ በመተባበር የሚያካሂዳቸዉ የእርዳታ እንቅስቃሴዎች በድርቅ የተጎዱ 2 ሚሊዮን፣ የምግብ ለሥራ ተጠቃሚዎች 1,2 ሚሊዮን፣ ተጨማሪ ምግብ የሚያስፈልጋቸዉ 1,1 ሚሊዮን፤ በትምህርት ቤት ምግብ የሚዳረሳቸዉ 670ሺ፤ መርት በተባለዉ ፕሮጀክት የታቀፉ 649 ሺ እንዲሁም 500ሺ ስደተኞች የምግብ ድጋፍ እንደሚያደርግ ነዉ የዘረዘሩት ቃል አቀባይዋል። እናም አሉ፤
«እናም 6,5 ሚሊዮን ሕዝብ ምግብ አጥቷል ማለት አይደለም፤ የተለያዩ መርሃግብሮች ናቸዉ፤ በጥቅሉ ግን ቁጥሩ ይህ ነዉ። እነዚህም የWFP የርዳታ መርሃግብር ተጠቃሚዎች ናቸዉ። ገሚሶቹ ኢትዮጵያዉያን፣ ገሚሶቹ ደግሞ ስደተኞች ናቸዉ።»
ከዚህም ሌላ WFP ማንኛዉንም ተግባር ከመንግስት ጋ በቅርበት በመተባበር እንደሚያከናዉንና ያም የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደረገዉን ጥረት እንደሚደግፍ አመልክተዋል። እሳቸዉ ለዘጋቢዎች ያደረጉት ገለፃም ከዘገባዉ እንደሚለይ በመጠቆም በስደተኞች ብዛት ጫና የደረሰባት ኢትዮጵያ ሁኔታ በዓለም ዓቀፍ ለጋሾች ትኩረት እንዲያገኝ ለማድረግ መሞከራቸዉን ገልጸዋል።
No comments:
Post a Comment