ከኢትዮጵያዊነት የአንድነትና የፍቅር መንፈስ ጋር የሚጣሉ ሁሉ ይደቃሉ!
በዲ/ን ኒቆዲሞስ (ምንጭ ፋክት) መጽሔት
“… ኢትዮጵያን አምላኬ ምትለው እግዚአብሔር ከኃያሉና ከብርቱ መዳፌ የሚያድናት፣ የሚታደጋት ከሆነ የእኔንም እግዚአብሔር ልጨምርላት እችላለሁ …፡፡” ቤኒቶ ሞሶሎኒ
ይህን ንግግር በሮማ አደባባይ የተናገረው ኢጣሊያዊ የፋሽስት መሪ ቤኒቶ ሞሶሎኒ ነው፡፡ ሞሶሎኒ ሮማውያኑ አያቶቹና አባቶቹ በዓድዋ የጦር ግንባር የተከናነቡትን ሽንፈትና ውርደት ከታሪክ መዛግብት እየቀፈፈውና እየዘገነነውም ቢሆን አንብቦ ነበር፡፡ ከዚህ ለማሰብ ቀርቶ ለማለም እንኳን ከሚከብድ የታሪክ ሐቅ ጋር የተፋጠጠው ሞሶሎኒ አምኖ ሊቀበለው የከበደውን ግን ደግሞ ሊፍቀው ያልቻለውን ይህን የታሪክ ውርደት፣ ይህን የታሪክ ስብራትና ክፉ ጠባሳ በሮማና በመላው አውሮጳ ምድር ይሻር ዘንድ ራሱን ታሪክን አዳሽ፣ ኃያልና ብርቱ የዘመኑ ጦረኛ ጎልያድ መሆኑን ለራሱም ለሕዝቡም አሳመነ፡፡
ሞሶሎኒ ሮማውያንን ብቻ ሳይሆን የመላውን አውሮጳውያን ቅኝ ገዢ ኃይሎችን ያዋረደ፣ ልክና ወደር ያጣውን ትዕቢታቸውንና ንቀታቸውን እንደ እንቧይ ካብ የናደውን ይህን የዓድዋውን ሽንፈት በመበቀል በአውሮጳ አዲስ አንጸባራቂ የድል ታሪክ ሊያስመዘግብ ቆርጦ ተነሣ፡፡ ሞሶሎኒ ሮማና መላው የአውሮጳ ቅኝ ገዢ ኃይሎች በኢትዮጵያና በኢትዮጵያውያን የደረሰባቸውን የውርድትና የሽንፈት አሳፋሪ ታሪክ ለማደስ በሮማ አደባባይ ለተሰበሰቡ የኢጣሊያ ሕዝብ እንዲህ ሲል በእብሪት ተሞልቶ ሮማ ዛሬም ኃያልና ታላቅ መሆኗን ለራሱና ለሕዝቡ ዳግም አበሰረ፡፡
ሞሶሎኒ ለ700 ዓመታት የዘለቀውን ታላቁን የሮማን ሥልጣኔና ታላቅነት እያስታወሰ ይህን አይደፈሬ የሆነውን የሮማን ታላቅነትና ክብር የተደፋፈሩትን ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን ለመቅጣት ጊዜው አሁን መሆኑን በአደባባይ አወጀ፡፡ ይህ በኢትዮጵያውያን የደረሰውን የሮማን የታሪክ ስብራት ለመጠገን ሞሶሎኒ የኢጣሊያ ሕዝብ ሁሉ ከጎኑ ይቆም ዘንድ ቀጭን ትዕዛዝ አስተላለፈ፡፡
እናም ይህ አረመኔና ያልተገራ የኢትዮጵያን/ጥቁር ሕዝብን እንደ ሰም አቅልጬ፣ እንደ ገል ቀጥቅጬ በባርነት እገዛው ዘንድ የሚያግደኝ ማን ነው፣ የትኛው ጎበዝ፣ የትኛውስ ኃይል ነው ሲል ሮማዊው ጎልያድ፣ ሞሶሎኒ እንዲህ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነት ላይ ተሳለቀ፡፡ በኢትዮጵያ አምላክም ላይ በድፍረት አፉን አላቀቀ፡፡ እናም እንዲህ ሲል በሮማ አደባባይ ላይ ከፍ ባለ ድምፅ አወጀ፡፡
‹‹… ኢትዮጵያን አምላኬ ምትለው እግዚአብሔር ከኃያሉ መዳፌ የሚያድናት ከሆነ የእኔንም አምላክ ልጨምርላት እችላለሁ …፡፡›› ሲል በኢትዮጵያ አምላክ ላይ ተሳለቀ፣ በልዑል እግዚአብሔር ላይ የትእቢትንና የድፍረትን ነገርን ተናገረ፡፡ በሮማ ምድርም በእምዬ ኢትዮጵያ ላይ የጥፋት ቀን ተቀጠረላት፡፡ ማን ኃያል፣ ማን ብርቱ ነው ሊያቆመን የሚቻለው ያሉ የሮማ የጥፋት አበጋዝ፣ ታላቅ ሠራዊት በኢትዮጵያ ምድር ላይ ያለ ምንም ከልካይና ሃይ ባይ ተመመ፣ ዘመተ፤ ምድሪቷንም ክፉኛ አስጨነቋት፡፡
ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን የአንድነትና የፍቅር መንፈስ እንደ ከንቱነት የቆጠሩ፣ የኢትዮጵያን አምላክም ያቃለሉ እብሪተኞች በበቀል መንፈስ የጥፋት ሰይፋቸውን በሕዝባችን ላይ መዘዙት፡፡ ይህ የጥፋት ሰይፋቸውም ሕፃን፣ ሽማግሌ፣ ሴት ወንድ ሳይል ሁሉንም ያጭደው ያዘ፡፡ የመርዝ ጋዝን፣ የሞት አረርን የጫኑ አውሮፕላኖችም በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ እየተገለባበጡና እያጓሩ ሰውና እንሰሳ ሳይሉ ይሄ ነው የማይባል ዘግናኝና አሰቃቂ የሆነ መአትንና መቅሰፍትን በሕዝባችን ላይ አወረዱበት፡፡
ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን የአንድነትና የፍቅር መንፈስ እንደ ከንቱነት የቆጠሩ፣ የኢትዮጵያን አምላክም ያቃለሉ እብሪተኞች በበቀል መንፈስ የጥፋት ሰይፋቸውን በሕዝባችን ላይ መዘዙት፡፡ ይህ የጥፋት ሰይፋቸውም ሕፃን፣ ሽማግሌ፣ ሴት ወንድ ሳይል ሁሉንም ያጭደው ያዘ፡፡ የመርዝ ጋዝን፣ የሞት አረርን የጫኑ አውሮፕላኖችም በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ እየተገለባበጡና እያጓሩ ሰውና እንሰሳ ሳይሉ ይሄ ነው የማይባል ዘግናኝና አሰቃቂ የሆነ መአትንና መቅሰፍትን በሕዝባችን ላይ አወረዱበት፡፡
እነዚህን የኢትዮጵያን ሰማይ እያረሱ፣ እየሰነጠቁና እያጓሩ የሞት መርዝን የሚረጩ አካላትን አይቶም ሰምቶም የማያውቀው የአገሬ ሕዝብና ባለ ቅኔም፡-
የለህም እንዳልል ይመሻል ይነጋል፣
አለህም እንዳልል እንዲህ ይደረጋል፡፡
አምላክ ለአንተው ፍራ፣
በቤትህ አግድመት ጎዳና ተሠራ፡፡
አለህም እንዳልል እንዲህ ይደረጋል፡፡
አምላክ ለአንተው ፍራ፣
በቤትህ አግድመት ጎዳና ተሠራ፡፡
ሲል ጭንቅ ጥበብ ብሎት ይህን አቤቱታ ለአምላኩ በቅኔው አሰማ፡፡
እማማ ኢትዮጵያ በሰይፍ ለወደቁ፣ በመርዝ ጋዝ ጭስ ላላቁ ልጆቿ፣ ወገቧን በገመድ ታጥቃ ብርቱ ጩኸትን ጮኸች፣ እንደ አይሁዳዊቷ ራሄል ያለ ብርቱ እንባዋንም ወደ አርያም፣ ወደ ፀባዖት ረጨችው፡፡ የሕፃናት፣ የጎበዛዝቱ፣ የእናቶችና የሽማግሌዎች ደም ምድሪቱን አጨቀየው፡፡ ዕንባ በሥፍር ተቀዳ፣ ደም እዚህም እዛም እንደ ጎርፍ ጎረፈ፡፡ ቅዱሳት መካናትና ገዳማት ሳይቀሩ በሮማውያኑ ሠራዊቶች ተደፈሩ፣ መነኮሳት፣ ካህናትና ዲያቆናት ያለ ምንም ርኅራኄ በጭካኔ ታረዱ፣ ተጨፈጨፉ፡፡
በወቅቱ ግራዝያኒ በኢትዮጵያውያን ላይ መጠቀም ስለሚገባው የመሣርያ ዓይነት በሚስጥር ያስተላለፈውን መልእክት የአሜሪካው ‘ላይብረሪ ኦፍ ኮንግረስ’ የሚገኝ አንድ ዶሴ እንደሚከተለው በሚስጢር ጽፎ እንደነበር ያጋልጣል፡፡ “ተልእኳችን እንዲሳካ ከተፈለገ በኢትዮጵያውያን/በጠላት ላይ እጅግ ከፍተኛ ውድመት ከዚህም በላይ የሞራል ስብራት የሚያስከትለውን ልዩ የሆነ ፈሳሽ ቦምብና መርዝ ሼል እንደፈለጉ በስፋት መጠቀም ያስፈልጋል፡፡”
የአገሬን ክብርና ነፃነት ለባዕድ አሳልፌ አልሰጥም፣ በኢትዮጵያዊነት ልዑላዊነትና የአንድነት መንፈስ ላይ በጭራሽ አልደራደርም ያሉት አቡነ ጴጥሮስም በሮማውያኑ መትረየስ በአደባባይ በጭካኔ ተደብደበው ሰማዕት ሆነው አለፉ፡፡ ኢትዮጵያ ፈጽማ በኀዘን ድባብ ተዋጠች፣ ክፉኛም አነባች፡፡
የኢትዮጵያ ታላቅ ባለውለታ የነበሩትና የኢጣሊያን ፋሽስት ግፍ ለዓለም ሁሉ በመግለጽ ከኢትዮጵያውያን ጎን የቆሙት ሲሊቪያ ፓንክረስት፣ የፋሽስቱ መሪ ቤኒቶ ሞሶሎኒ በኢትዮጵያውያን የሃይማኖት አባቶች ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ ሌሎች ኢትዮጵያውያንን ሊያሸማቅቅ እንደሚችልና ጭፍጨፋውም ውጤታማ እንደሆነ በወቅቱ ለቅኝ ግዛት ሚ/ሩ ለግራዚያኒ ያስተላለፈውን ምስጢራዊ የቴሌግራም መልእክት Ethiopia and Eritrea በሚለው መጽሐፋቸው እንዲህ ገልጸውታል፡-
…The execution of Abune Petros, one of the four Ethiopian bishops, has terrified the leaders and the public. The work of repression against armed groups dispersed in the forest continues.
አቡነ ጴጥሮስም በመጨረሻ ቃላቸው፡- እምዬ ኢትዮጵያ … እናት አገሬ … ደሜ ለነፃነትሽ፣ ለክብርሽ፣ ለአንድነትሽ ንጹሕ የፍቅር መሥዋዕት ሆኖ የፈሰሰ ነውና ጽኑና ኃያል በሆነው አምላክሽ ፊት ልክ እንደ አቤል ደም ፍርድን የሚሻ፣ ፍትሕን የሚጠይቅ ይሁን፡፡ ሲሉ ዓይናቸውን ወደ ሰማየ ሰማይ አቅንተው አምላካቸውን እግዚአብሔርን በዕንባ ተለማመኑት፣ ተማጠኑት፡፡
እመብርሃን፣ ድንግል ሆይ … ይኸው ለቃል ኪዳን ምድርሽ እንባዬን ከደሜ ጋር ቀላቅያለሁና… ይህን በሕዝብሽ፣ በአገልጋዮችሽ ላይ እየወረደ ያለውን ግፍና መከራ በልጅሽ ፊት አዘክሪ፣ አሳስቢ፡፡ እናቴ ሆይ አዛኝቱ ያለ አንቺ ማን አለኝ፤ ድንግል ሆይ ‹‹ስምዒ ሐዘና ወብካያ ለሀገሪትነ ኢትዮጵያ!›› ሲሉ የኢትዮጵያን ሰቆቃዋን፣ ጣሯንና ጭንቀቷን አሳስቢ ሲሉ ተማፀኑ፡፡
ያ ለነጻነት ክቡር መንፈስ የፈሰሰ ዕንባቸውና ደማቸው በኢትዮጵያ ተራሮች፣ ሸንተረሮች፣ ዱርና ጫካ ታላቅ የሆነ የነጻነት ደወልን አሰማ፣ አስተጋባ፡፡ እምቢ ለነጻነቴ ያሉ የኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጆች ዘር፣ ጎሳ፣ ቋንቋና ሃይማኖት ሳይለያቸውና ሳይከፋፍላቸው ነፃነታቸውን በደማቸው ለማስመለስ ዱር ቤቴ ብለው ከተሙ፡፡ የእናት ኢትዮጵያን ህመሟን፣ ስቃይዋንና መከራዋን በዕንባቸውና በላባቸው፣ በደማቸውና በአጥንታቸው ታላቅ መሥዋዕትነት ይካፈሉ ዘንድ ዱር ቤቴ አሉ፡፡
የኢትዮጵያዊነትን የአንድነትንና የፍቅር ቅዱስ መቅደስ በደማቸው ዳግም ሊቀድሱና ሊያከብሩ በነፍሳቸው የተወራረዱ ኢትዮጵያውያን ጀግኖች በሮም አደባባይ በደማቸው ሕያው ታሪክን ጻፉ፡፡ የኦሮሞ ምድር ፍሬ የሆኑት ጀግናው ኮ/ል አብዲሳ አጋና ኤርትራዊው ዘርአይ ደረስ፡- በባዕድ ምድር፣ በግዞት እንኳን ሆነው፡- ‹‹ኢትዮጵያ ሆይ ብረሳሽ ቀኜ ትርሳኝ፣ ባላስብሽ ምላሴ በጉሮዬ ይጣበቅ፡፡›› በማለት የእናት ምድራቸውን አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀዩ ሰንደቀ ዓላማቸውን በሮም አደባባይ ከፍ አድርገው በማውለብለብ ኢትዮጵያዊነት የአንድነት እና የፍቅር ቅዱስ መቅደስ መሆኑን በደማቸው መሰከሩ፡፡
በርካታ ኢትዮጵያውያን በአርበኝነት በአገራቸው ዱርና ተራራ ተሰደዱ፣ ሌሎች ደግሞ በዕንባና በለቅሶ እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይታደጋት ዘንድ ሱባኤ ገቡ፡፡ በኢየሩሳሌምም በሚገኘው የዴር ሱልጣን ገዳምም የተሰደዱ በርካታ ኢትዮጵያውያን መነኮሳት፣ ካህናትና ሹማምንቶች የኢትዮጵያ አምላክ ለአገራቸው ነጻነትን ይመልስላት ዘንድ በጸሎት መጋደል ያዙ፡፡
ኢየሩሳሌምን በሚገኘው ገዳማችንን ተሳልመው የጥቂት ቀናት ቆይታ አድርገው መንገዳቸውን ወደ ጄኔቭ ያደረጉት ዓፄ ኃይለ ሥላሴም በሊግ ኦፍ ኔሽን አቤቱታቸውን አቀረቡ፡፡ ንጉሡ በንግግራቸውም የኢጣሊያ የፋሽስት መንግሥት በአገራቸው ሕዝብ ላይ እያደረሱ ያሉትን ግፍና በዓለም መንግሥታት የተከለከለ መርዛማ ጭስ በአገራቸው ሕዝብ ላይ እያወረደ መሆኑን በመጥቀስ ይሄን ዘግናኝና አሰቃቂ መዓት ኃያላኑ ጣልቃ ገብተው እንዲያስቆሙ በብርቱ ተማፀኑ፡፡ የሕዝባቸውም አቤቱታ አሰሙ፡፡
የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ አቤቱታና የሕዝባቸው ለቅሶና መከራ ግን ለአውሮጳውያኑ እምብዛም የሚያስጨንቃቸው ጉዳይ አልነበረም፡፡ እንደውም ለአንዳንዶቹ አውሮጳውያን ራሷን ከነጭ እኩል አድርጋ ለምታስበው ኢትዮጵያ ይህ ቅጣት የሚገባ፣ ልኳን እንድታውቅ የሚያደርግ መሆኑን በማመን ለሞሶሎኒ በግልጽና በስውር በርታ ሲሉ ቀኝ እጃቸውን አዋሱት፡፡
በሊግ ኦፍ ኔሽን መድረክ ተግባራዊ ምላሽ ያላገኙት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴም፣ ‹‹… ይህን የአገሬንና የሕዝቤን ግፍና መከራ ችላ ብላችሁ ብታልፉት ታሪክና እግዚአብሔር ፍርዳችሁን ይሰጣችኋል … ፡፡ ሲሉ ትንቢታዊ የሚመስል ታሪካዊ ንግግርን አደረጉ፡፡ የኢትዮጵያን በአምባገነኑ የፋሽስት ሠራዊት መወረርና የሕዝባችንም ግፍ በዝምታ ያለፉ አውሮጳውያኑ አገራት ብዙም ሳይቆይ ከጀርመን በተነሳው በናዚ ሂትለርና በፋሽስቱ መሪ ሞሶሎኒ የጦር ክተት ታወጀባቸው፡፡
አምባገነኖችን በጊዜው ተው፣ እረፉ ለማለት የሞራል ብቃት፣ ጉልበት ያነሰውና ‹‹ጥርስ የሌለው አንበሳ›› የሚል ፖለቲካዊ ስላቅን ያተረፈው ‹‹ሊግ ኦፍ ኔሽንም›› በዓይኑ ፊት በአምባገነኖቹ ሂትለርና ሞሶሎኒ አገራት በግፍ ሲወረሩ የኃይለ ሥላሴ ትንቢታዊ ንግግር እየተፈጸመ እንደሆነ በወቅቱ ቀውሱን የታዘቡ ፖለቲከኞችና የታሪክ ምሁራን በሰፊው ጻፉ፣ መሰከሩ፡፡ በኢትዮጵያ ላይ የደረሰውን ኢፍትሐዊ ወረራና ግፍ በዝምታ ያለፉ አውሮጳውያን በራሳቸው ሲመጣ ግን ለመታገሥ አልቻሉም ነበር፡፡ ሳይወዱ ተገደው ወደ ጦርነት ገቡ፣ እናም የሁለተኛው የዓለም ጦርነት በአውሮጳ ሊፈነዳ ግድ ሆነ፡፡
የታሪክ ምሁራንና የፖለቲካ ተንታኞች እንደጻፉት ለሁለተኛው የዓለም ጦርነት መፈንዳት ሊግ ኦፍ ኔሽን ኢትዮጵያ በፋሽስት ኃይል ስትወረር ያሳየው መለሳለስና ደካማ አቋም እንደ አንድ ትልቅ ምክንያት ከሚጠቀሱት መካከል መሆኑን ያስመሩበታል፡፡ ‹‹አክሲስ ፓወር›› በሚል በጀርመኑ ሂትለር፣ በፋሽስቱ ሞሶሎኒና በቶኪዮ/ጃፓን የተባባረ ኃይል ዓለምን በራሳቸው ቁጥጥር ስር ለማድረግ የተነሡ ሮምንና ጀርመንን ለመመከት እንግሊዝና ፈረንሳይ ሌሎችን አገሮችን በማስተባበር ወደ ጦርነት ከተቱ፡፡
የኢትዮጵያና የሕዝቦቿም ለቅሶ በእግዚአብሔር ፊት ታሰበ፡፡ የግፍ ጽዋም ሞልቶ ፈሰሰ፡፡ እናም፣ ‹‹ስለ ድሆች፣ ስለ ምድሪቱ ግፉአን፣ ፍትሕንና ፍርድን ስለተነፈጉ ምንዱባን እግዚአብሔር አሁን ይነሳል፡፡››፣ ‹‹እግዚአብሔር ተዋጊ ነው ስሙም እግዚአብሔር ነው፡፡›› ተብሎ በአባቶቻችን ቅዱሳን ነቢያት የተነገረለት የሠራዊት አምላክ እግዚአብሔር የመዓቱን ጽዋ በአውሮጳ ምድር ላይ አፈሰሰው፡፡ አውሮጳ እስከዛሬ አይታው በማታውቀው መከራና ሰቆቃ ውስጥም ተዘፈቀች፡፡
በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ያለቁበትና የአካል ጉዳተኛ የሆኑበት የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከፍተኛ የሆነ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ሥነ ልቦናዊ ቀውስ አስከትሎ የናዚውን ሂትለርና የፋሽስቱን ሞሶሎኒ ታሪክ በውርደት ደመደመው፡፡ የትኛው አምላክ ነው ኢትዮጵያን ከኃያሉ ክንዴ የሚያስጥላት ያለው ሞሶሎኒም በሮም አደባባይ አይወርዱ ውርደትን ተዋርዶ የሞት ስቅላት ተፈረደበት፡፡
‹‹ኢትዮጵያን ከሕዝቦቿ ጋር ካልሆነም ኢትዮጵያን ገጸ-በረከት አድርጌ አቀርብልሃለሁ፡፡›› ብሎ ለአለቃው ለሞሶሎኒ ቃል የገባው ማርሻል ግራዚያኒም በአርበኞቻችንና በእንግሊዛውያን የጦር ሠራዊት ዕርዳታ ከነሠራዊቱ አፍሮና ተዋርዶ አገራችንን ለቆ ወጣ፡፡ በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ በልጆቿ ደም የተቀደሰው አረንጓዴ፣ ቢጫና ቀዩ ሰንደቀ ዓላማዋ ዳግመኛ ከፍ ብሎ ተውለበለበ፡፡ እነ ዘርአይ ደረስ፣ እነ አብዲሳ አጋ፣ እልፍ ኢትዮጵያውያን አርበኞች በሮም አደባባይ ሳይቀር በደማቸው ከፍ ያደረጓት ሰንደቀ ዓላማችን ሚያዚያ 27 ቀን 1933 ዓ.ም. በክብር ዳግመኛ ከፍ ብላ ተውለበለበች፡፡
ዳግመኛ ኢትዮጵያዊነት ለጊዜው የሚያንቀላፋ እንጂ የማይሞት ጽኑና ሕያው ቃል ኪዳን መሆኑ ተበሰረ፡፡ ከኢትዮጵያና ከኢትዮጵያዊነት ጽኑ ቃል ኪዳን ጋር የተገዳዳሩ ሁሉ ዕድል ፈንታቸው፣ ጽዋ ተርታቸው ድቀት፣ ውርደትና ጥፋት ሆነ፡፡ የኢትዮጵያዊነትን የአንድነትና የፍቅር ቅዱስ መቅደስን ሊያረክሱና ሊያራክሱ የተነሡ ሁሉ ለድቀት፣ ለውርደትና ለአሳፋሪ ሽንፈት መዳረጋቸው የታወቀ ሐቅ መሆኑ ተመሰከረም፡፡ በምንም የማይረታና የማይሸነፍ በዓድዋ የተበሰረው ጽኑ የኢትዮጵያዊነት ታላቅ መንፈስም ዳግመኛ በሮማ ውርደት የተነሣ ከዓለም ጫፍ እስከ ጫፍ ተሰማ፡፡
ይህ የኢትዮጵያዊነት ክቡር የአንድነትና የፍቅር መንፈስ የቋራው ካሣ/ቴዎድሮስ በመቅደላ አፋፍ የተሰውለት፣ አፄ ዮሐንስ፣ ‹‹ኢትዮጵያ አገርህ ልጅህ፣ ሚስትህ፣ እናትህ፣ ዘውድህ፣ ክብርህና መቃብር ናት፡፡› በሚል በመተማ አንገታቸውን ለሰይፍ፣ ደረታቸውን ለጦር የሰጡለት፣ እምዬ ምኒልክ፣ እቴጌ ጣይቱ፣ እልፍ የኢትዮጵያ ጀግኖች በዓድዋ ጦር ግንባር በደማቸው የቀደሱት፣ ያከበሩትና ያወደሱት ነው … ይህ ዘመን የማይሽረው የኢትዮጵያዊነት ቃል ኪዳን፣ ክቡርና ታላቅ መንፈስ!!
በየዓመቱ የምናከብረው፣ የምንዘክረው ሚያዚያ 27 ቀንም ክቡር አባቶቻችንና እናቶቻችን ለኢትዮጵያ ነጻነት፣ ልዑላዊነት፣ ለሰንደቀ ዓላማዋ ክብርም ያለ ምንም መሳሳት ውድ ሕይወታቸውን የከፈሉበት ነጻነታችንን ምናስታውስበት ታላቅ ቀን ነው፡፡
ደግሞም የኢትዮጵያዊነትን የአንድነትንና የፍቅርን ሸማ የተላበስን ሁሉ በኢትዮጵያዊነት የአንድነትና የፍቅር መንፈስ ላይ ለመገዳዳር ለሚነሡ ሁሉ ሌሎች የደረሰባቸውን ውርደትና ድቀት ከታሪክ ይማሩ ዘንድ የምናሳስብበት ቀንም ነው፡፡ የኢትዮጵያዊነት ክቡር መንፈስ የዘር፣ የነገድ፣ የቋንቋ፣ የሃይማኖት ድንበር የማያግደው ሕያውና ጽኑ ቃል ኪዳን፣ ቅዱስ የፍቅር መቅደስ መሆኑን ያስታውሱና ራሳቸውንም ከውርደት፣ ከጥፋትና ከድቀት ያድኑ ዘንድም እንነግራቸዋለን፣ ግድ እንላቸዋለንም!!
No comments:
Post a Comment