እናስራችኋለን? ለካንስ የነአጅሬ ጋጠወጥነት ከድንበርም ተሻግሯልና!
ነፃነት ዘለቀ (ከአዲስ አበባ)
በሀገራችን ባደመነው አጠቃላይ የሀዘን ድባብ ሳቢያ ፈገግታ እያማረኝ ፈገግ ለማለት ምንም ዕድል ሳላገኝ ብዙ ሰሞኖችን ባጀሁ፡፡ ዕድሜ ለዚህ ነገረኛ ኢሳት የሚባል ቴሌቪዥን ዛሬ ማታ ግና በሣቅ የሚያፈርስ ዜና ሰማሁና ምሽቱን ብቻ ሳይሆን ትዝ ባለኝ ቁጥር ሌቱን ሁሉ በሣቅ ስፈርስ አደርኩ – የግራ ጎን አጥንቶቼ ክፋይ ጉድ እስክትለኝ፡፡ ሣቅ ጥሩ ነው፡፡ አንዳንዴ በሣቅ የሚገድል ነገር ማግኘት የመታደል ያህል ነው፡፡ እውነተኛው ሣቅ ሞቶ ቢቀበርም ወያኔን መሰል ጅላንፎ ጉጅሌ የሚሠራቸው አንዳንድ ነገሮችን በመታዘብ ለጊዜውም ቢሆን ፈገግ መሰኘት ሲያስፈልግም ሆድን ያዝ አድርጎ በሣቅ መንፈርፈር ሰውነትን ያፍታታል፤ ወቅታዊ እፎይታንም ይሰጣል፡፡ እኔ – እውነቴን ነው – ለብዙ ጊዜ ያጣሁትን ሣቅ ዛሬ አገኘሁትና ከልቤ ተዝናናሁ፡፡ ወያኔ እኮ አልታወቀለትም እንጂ ደምበኛ የኮሜዲ መፍለቂያ ውድብ ነው፡፡ ልዩ የኢትዮጵያ ቻርሊ ቻፕሊን ሆነው የለም እንዴ!
ይህን የወያኔን ሞኝነት ጉዳዩ ለሚመለከተው የዓለም ክፍል ያንጸባረቀ ጉዳይ ለፖለቲካችን ቅርብ የሆነ ሰው ባያጣውም ለእንደኔ ዓይነቶች የማይሞላላቸው አንዳንድ ባዘኔዎች ማስታወሱ ደግ ይመስለኛል – ‹ቦዘኔ› እንዳላልኩ ይታወስልኝ፡፡ ብዙ ሰው እኮ የማይሞቀው የማይበርደው ሆኗል፡፡ ደንዘናል፤ በቁም ሞተናል፤ ‹ብታምኑም ባታምኑም› ብዙዎቻችን ከሰውነት ተራ ወጥተን የአምልኮተ ንዋይ ሰለባዎች ሆነናል፡፡ በሀገር ውስጥ ትንሽ ትልቁን ብታዩት ከሞላ ጎደል ሁሉም ሊባል በሚችል ሁኔታ ገንዘብ እንዴት ሊያገኝና በአቋራጭ ሊከብር እንደሚችል ሲጨነቅና ሲጠበብ ይታያል፡፡ ኅሊና ብሎ ነገር ጠፍቷል፡፡ ወንድም ወንድሙን፣ እህት እህቷን እስከመግደል በሚደርስ ሰይጣናዊ ጭካኔ ተሞልተን እየተፋጀን ነው፡፡ ወያኔ በቀደደው የጥፋት ጎዳና እየተመምን ከሰውነት ደረጃ በሚያስወጣ የሀብት ፍቅር ተነድፈን ልንጨራረስ የቀረን ጊዜ ሩብ ሐሙስ ቢሆን ነው፡፡ አልተነሳሁበትም እንጂ በዚህስ ትንሽ ባወራሁ፡፡
ወያኔም ባቅሙ አስታራቂና የሰላም አባት ሆኖ የደቡብ ሱዳን ተፋላሚዎችን በዕርቅ ለማስማማት አዲስ አበባ ይጠራቸዋል፡፡ ሳልቫኪር የሚሉት ባለባበሱና በዐይነ ውኃው ፊውዳላዊ አምባገነን የሚመስለኝ አማቻችን ሰውዬና ዶክተር ማቻር የሚባለው ሞገደኛ ሰውዬ ወደ አዲስ አበባ መጥተው (እንዳሁኑ ሁኔታ ደግሞ በመስፈራርቾ ተጠርተው) ሼራተን ሆቴል ሁለት ክፍሎች ውስጥ ይመሽጋሉ – ‹አማቻችን› ያልኩት የሳልቫኪር ይሁን የማቻር ልጅ የኛን ሀገር ልጅ እንዳገባ/ች በሚዲያ ስለሰማሁ ነው፡፡ ድርድሩም በወያኔ ጉጅሌ አማካይነት ተከናወነ ይባልና የዕርቁ ስምምነት ተፈረመ ተብሎ በወያኔው ቱሪናፋ ሚዲያዎች ይለፈፋል – (ከብቱ ወያኔ በሰሞኑ ጭፍጨፋው የጠለሸ ስሙን ያደሰ መስሎት በገባበት ወጥመድ የኋላ የኋላ ራሱ ገብቶበት ተተበተበበት እንጂ)፡፡ የወያኔ ኢትዮጵያ ለራሷ ብቻ ሣይሆን ለጎረቤት የሚተርፍ ሰላምና ዴሞክራሲ መጋዘኗ ውስጥ ጢም ብሎ እንዳለና ለሱዳንም፣ ለሶማሊያም፣ ለግብጽም፣ ለሦርያም፣ ለአፍጋኒስታንም፣ ለኢራቅም፣ ለቬንዝዌላም፣ ለ“ዴሞክራክ ሪፓብሊክ” ኮንጎም፣ ለሤንትራል አፍሪካ “ሪፓብሊክ”ም፣ ለሃይቲም፣ ለኡክሬንና ራሽያም፣ ለሰሜን ኮሪያም፣ ለ‹ኤርትራ›ም፣ ለሊቢያም፣ ለፓኪስታንም፣ ለበርማም፤ ለፍልስጥኤምም፣ (እንዴ፣ ዓለም ለካንስ በትርምስ ላይ ናትና ጎበዝ – የወያኔ የሰላም በረከት የሚላክላቸው ሁከት የነገሠባቸው ሀገሮች ዝርዝር አላልቅልኝ እኮ አለ!) ኤክስፖርት ለማድረግ ዝግጅቷን እንዳጠናቀቀች በነዚሁ በእውነት ዕርሙ የወያኔ ሚዲያዎች ከጥንፍ እስከ ጥንፍ ተስተጋባ፡፡ እኛም ይሄ የቤት ቀጋ የውጪ አልጋ የሆነ የወሮበሎች ቡድን ምን መተት ቢኖረው ይሆን እንዲህ ዓለምን ጉድ ባሰኘ መልክ የሰላም አባት ሊሆን የበቃው ብለን ተገረምን፡፡ የገዛ “ዜጎቹ”ን ባልተወለደ አንጀት እየጨፈጨፈና የስምንት ዓመት ሕጻን ሣይቀር ደረቱን በጥይት ዝናብ እየበሳሳ ባለበት ወቅት እንዲህ ያለ ሰላም ለሱዳናውያኑ ማስገኘቱ በርግጥም አንዳች ነገር አለው አልንና በጣም ተደነቅን፡፡ ኢትዮጵያችንም ስሟ ታደሰልን ብለን ደስ አለን – ደስታችን አንድ ጀምበር እንኳን ሳይዘልቅ ጠወለገብን እንጂ፡፡
ነገሩ ለካንስ ሌላ ኖሯል፡፡ ሳልቫኪር ሀገሩ እንደገባ ለሀገሩ መገናኛ ብዙኃንና ለባለሥልጣናቱ ሲናገር እንደተደመጠውና በሚዛናውያን ሚዲያዎች ሲዘገብ እንደተከታተልነው የሰላሙ ስምምነት የተፈረመው በወያኔ አስገዳጅነት ነበር፡፡ የአስገዳጅነቱ አካሄድም ነው በአስቂኝነቱ ወደር ያልተገኘለት፡፡
ከፍ ሲል እንደተገለጸው ወያኔ ሁለቱን ሰዎች ሼራተን ውስጥ በሁለት የተለያዩ ክፍሎች ያስቀምጣቸዋል፡፡ ፊት ለፊት ሳይገናኙም በተላላኪ ሃሳብ እንዲለዋወጡ ያደርጋል፡፡ መገናኘት ያልፈለጉት ምናልባት ራሳቸው ሊሆኑ እንደሚችሉ እንገምት፡፡ ወያኔ ግን የሁለቱ ሰዎች ያለመታረቅና ዕርቁን በፊርማ ያለማጽደቅ አዝማሚያ ሲገባው ያቺን የጫካ ህግ በመምዘዝ “ካልፈረማችሁ እዚሁ አስራችኋለሁ፤ ወደ ሀገራችሁ መሄድ ህልም እንደሆነባችሁ እንደነ እስክንድር ነጋና ርዕዮት ዓለሙ ከርቸሌ ትወረወራላችሁ፤ ከዚህ የሚያወጣችሁ አንድም ኃይል የለም” ብሏቸው ያርፋል፡፡ ይህ ያላሳቀ ምን ሊያስቅ ይችላል? እንዴ፣ በዚህማ ድዳችንን ተወቅረንም ሆነ ተነቅሰን መሣቅ አለብን፡፡ ግሩም እኮ ነው እናንተ ሆዬ!
ትርፋ ትርፉን እንተወውና ቃል በቃል ወያኔ ያላቸው “ስምምነቱን በፊርማችሁ ካላጸደቃችሁ ትታሰራላችሁ!” የሚል ነው – ከሌሎች የማስፈራሪያ አንድምታዎች ጋር፡፡ አስገዳጁ ደግሞ ራሱ ተገድዶ ቤት ጠባቂ የሆነው ደሳለኝ ነው አሉ – ማነው – ኃይለማርያም – ከአለቆቹ በተነገረው ጥብቅ ማስጠንቀቂያ መሠረት፡፡
ልብ አድርጉ! እነዚህ ሰዎች – እነሳልቫኪር – አነሰም አደገም የአንዲት ሉዓላዊት ሀገር መሪዎች ናቸው – አሁን ቢጣሉምና ከሁለት አንድኛቸው ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ያለው መንግሥት በመምራት ላይ መገኘቱ እንዳለ ሆኖ፡፡ ወያኔን ታዲያ ምን ገጠመው? ይህችን እጅ እየጠመዘዙ ማስፈረምን ከሀገር ደረጃ አውጥቶ አህጉራዊ ቅርጽ እንዲኖራት የማድረግን ከፍተኛ ጉጉት ማን አሳደረበት? “የገቡበት የፖለቲካ ቀውስ የሚሠሩትን አሳጥቷቸው ለአንዳች የፖለቲካ ትርፍ ብለው ይሆን እንዲህ ያለ ‹ሪስክ› ውስጥ የገቡት?” ብዬም ተጨንቄላቸዋለሁ – ለወያኔዎቹ – እንዲያ ካልሆነ መቼም ጡት ያልጠባ ማለቴ ያልጣለ ሕጻን ሣይቀር መዘዙን ጠንቅቆ ሊገምተው የሚችለውን ይህን የመሰለ ጅልነት ውስጥ ባልገቡ ነበር፡፡ አሁን አስገድዶ ቢያስፈርማቸው ወደሀገራቸው ሲመለሱ ጉዱን ማለትም ምሥጢሩን እንደሚያወጡት እንዴት ወያኔዎች ሊገምቱ አልቻሉም? እንዴትስ ቢንቋቸው ነው? በኛ የለመዱትን ንቀት እኮ ነው በ‹ኮፒ ፔስት› እነሱም ላይ እውን ያደረጉት፡፡ በውነቱ እነዚህን የመርገምት ፍሬዎች ሰው ናቸው ብሎ መቀበል እንዴት ይቻላል? ኢትዮጵያ በታሪኳ እንዲህ ያለ አሣፋሪ ነገር የፈጸመባት በስሟ የተቀመጠ “መንግሥት” የለም፡፡ እዚህ ላይ አንዲት ብጫቂ ማሳሰቢያ አለችኝ፡- በተለይ ኢሳቶች ይህንን የወንበዴ ጥርቃሞ ቡድን “የኢትዮጵያ መንግሥት” እያላችሁ በዜና ዕወጃችሁ የምትናገሩትን ነገር ባፋጣኝ ብታርሙ ይሻላል፡፡ ይህ ‹መንግሥት› መንግሥት ሣይሆን የከተማ ሽፍታ ነው፤ በአንድ ጎሣ የተዋቀረ፣ ለአንድ ጎሣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጥቅም ያደረ፣ ለዓለም አቀፍ የውንብድና ተቋማት የሰገደና አንዲትን ሀገር ከነሕዝቧ መቀመቅ ለማውረድ ታጥቆ የተነሣን ወሮበላ የአማጊዶዎችን ስብስብ መንግሥት ማለት በመንግሥት ተቋማዊ ምንነት ላይ መቀለድ ነው፡፡ ስለዚህ ቢያንስ “የኢትዮጵያ መንግሥት ተብዬው” በሚል ቢነገር የተሻለ ነውና አንዳንድ ወገኖች አታቁስሉን፡፡ የነሱው ይበቃናል፡፡
አንድ ፈረንጅኛ አባባል አሁን ትዝ አለኝ፡፡ A man cat take a horse to a river; but twenty cannot make it drink. ወዳማርኛው ሲመለስ – አንድ ሰው አንድን ፈረስ ወደ ወንዝ ሊወስደው ይችላል፤ ሃያ ሰዎች ግን ውኃ(ውን) እንዲጠጣ ሊያደርጉት አይችሉም፡፡ የወያኔ ቂልነት፣ የወያኔ ባልጩት ራስነትና አባጉልቤነት እዚህ ላይ ነው፡፡ እነሱ የሚያስቡት ነገር ሁሉ ገዢ ይመስላቸዋል፡፡ የድንቁርናቸው መጠን በምንም ምድራዊ መለኪያ የሚሠፈር አይደለም፡፡ በመንግሥትነት ለሃያ ሦስት ዓመታት የቆዬ አንድ ኃይል የዚችን ፊርማ መነሻና መድረሻ ከነመዘዟ ጭምር ካላወቀ ትልቅ የአስተሳሰብም እንበለው የአመለካከት ችግር አለ ማለት ነው፡፡ እንዲያው ግን ኢትዮጵያ ምን ያህል ብትረገም ፣ እኛም ምን ያህል ባንታደል ይሆን ፈጣሪ እነዚህን ሰዎች የሰጠን? አይጨንቅም? ሳስበው በጣም ይጨንቀኛል – ማይግሬይን የተሰኘውን ከፍተኛ ራስ ምታት የሚለቅ ችግር ነው የገጠመን፡፡
የዚህ ችግር መባቀያ ደግሞ ውስብስብ ነው፡፡ ምዕራባውያንም ይጠየቁበታል – አሉበትና፡፡ ማፈሪያ የሰውነት አካል እንደወያኔው የላቸውም እንጂ ካላቸው በእጅጉ ሊያፍሩበት ይገባል፡፡ በብዙ ነገር እየደገፉ ከበረሃ ወደ ቤተ መንግሥት ያስገቡ ኃይሎች ቆም ብለው ሊያስብቡበት የሚገባ ወቅት ላይ መድረስ የሚገባቸው ይመስለኛል፡፡ እኛን ማመን ስላልፈለጉ እስካሁን አላመኑንም፡፡ የወያኔን ጉድ ቢያውቁትም እንደዚህ ቁልጭ ብሎ የወጣበት ዘመን ባለመኖሩ ይህን ሃቅ ማመን ባይፈልጉና በቆዬ ወያኔን የመደገፍ አቋማቸው የሚጸኑ ከሆነ ከሌላ ከማንም ጋር ሣይሆን ከገዛ ኅሊናቸው ጋር የሚጣሉበት ጊዜ እየደረሰ መሆኑን እየመረራቸውም ቢሆን መገንዘብ አለባቸው፡፡ ወያኔ የአንድን ሉዓላዊ ሀገር ፕሬዝደንት “አስርሃለሁ!” ካለና ካለውድ በግዱ ካስፈረመ ከዚህ በላይ ዓለም አቀፍ ውንብድናና ማፊያነት የለም፤ ወያኔ በዓለም አቀፍ ደረጃ ፕሬዝደንታዊ ስብዕናንና ሀገራዊ ክብርን የሚነካ እንዲህ ያለ ጠያፍ የማንአለብኝነት ተግባር ከፈጸመ የገዛ ምድሩን ዜጎች ምን ሊያደርግ እንደሚችል ማንም ወገን በዚህ ኹነት አማካነት ሊረዳ ይገባዋልና ይህ የሰሞኑ ወያኔያዊ ቅሌት ውርደታዊ ክስተት ለሀገራችን በጎ ገጽታ አለው (ፈረንጆቹ blessing in disguise እንደሚሉት ማለቴ ነው)፡፡ ይህ ነገር እንደሚመስለኝ ወያኔን ብቻ ሣይሆን ምዕራባውያንንም ከነሤራዊ ተንኮላቸው ለማጋለጥ ፈጣሪ ያመቻቸው ነገር መሆን አለበት፡፡ ከፍ ሲል እንደጠቆምኩት ዓለም እስኪታዘበን ድረስ የወያኔን አምባገነንነትና ገዳይነት ስናጋልጥ ብንቆይም ያመነን አልነበረም፡፡ የማቻርንና የሳልቫኪርን ምስክርነት ግን ሊጠራጠር የሚገባ ሰው አይኖርም ብዬ እገምታለሁ ፤ ምንም እንኳን እነሱ ራሳቸውም የአፍሪካዊ አምባገነንነት ወረርሽኝ ሰለባ ቢሆኑም፡፡
አሁን ፈረሱም ሜዳውም ያለው በወያኔ ደጋፊዎች ደጅ ነው፡፡ እስካሁን ያርመጠምጡት የነበረውን የኢትዮጵያ ፖለቲካ ማቃናት የሚያስችላቸው ወርቃማ ዕድል አሁን እፊታቸው አለ፡፡ አንዳንድ ልፍስፍስ ፖለቲከኞቻችንንና ወያኔ ተከል ተቃዋሚ ተብዬዎችን እንዲሁም በወያኔ ቅኝት የሚዘምሩ የነገ ራስ ምታቶችን ትተው ሁነኛ ዴሞክራሲ በሀገራችን የሚመጣበትን መንገድ ሊደግፉ የሚችሉበት ዕድል አሁንም አለ፡፡ አለበለዚያ በኃይል የሚመጣ ሥልጣን ለነሱም ሆነ ለሀገራት እንደማይበጅ የታወቀ ነውና እነዚህ ምዕራባውያን የእጃቸውን የሚያገኙበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም፡፡ ብዙዎቹ በዓለም የሚታዩ አመፆችና የሽብር ተግባራት ሥረ መሠረታቸው ሲጠና መነሻቸው እነሱው ራሳቸው ምዕራባውያኑ ናቸው፡፡ ለዐይን ይበጃል ብለው የሚኳሉት ኩል ዐይንን እንደሚያጠፋ ሁሉ ለአንዳንድ ሤራዎቻቸው ስኬታማነት ብለው – ለምሳሌ እንደ አዲሱ የዓለም ሥርዓት (NWO) – የሚተልሟቸው ዕቅዶች በጊዜ ሂደት ወደነሱው እየዞሩ በመተኮሳቸው ባላስፈላጊ ጥቃቶች ዜጎቻቸውንና ንብረታቸውን አስፈጅተዋል፤ እያስፈጁም ነው – 9/11ን፣ 5/7ንና የናይሮቢን የሽብር ጥቃት ማስታወስ በቂ ነው፡፡ ቢን ላደንን ማነው እዚያ ላይ አድርሶት የነበረው? አዎ፣ ሁሉም የሥራውን ነው የሚያገኘው፡፡ የተከልካት ተክል ትጸድቃለች፤ ጠቃሚ ከሆነች ትጠቀምባታለህ፤ ጎጂ ከሆነች ግን ትጎዳባታለህ፤ ሰውን አለኃጢኣቱ ልታጠቃ ብለህ የወረወርካት ጦር ዞራ ተመልሳ ወዳንተው እንደምትመጣ ካላወቅህ ተሳስተሃል፤ ጊዜ ይፍጅ እንጂ በቆፈርከው ጉድጓድ የመግባት ዕድልህ እጅግ ሰፊና የማይቀርም የመጨረሻ ዕጣ ፋንታህ መሆኑን ማወቅ አለብህ፡፡ የበግ ግልገል መስላህ መንገድ ላይ ያገኘሃትን የጅብ ግልገል ቤትህ ውስጥ ብታሳድጋት ተፈጥሯዊ ባህርይዋን አትለቅምና የኋላ ኋላ የምትጎዳው አንተው ነህ፡፡ እናም ወያኔም ሆነ የስምሪት ኃላፊዎቹ ሁሉ የዘሩትን ያጭዳሉ፤ የጊዜና የቋት መሙላት/አለመሙላት ካልሆነ በስተቀር ወያኔ በኢትዮጵያ ምድርና ሰማይ እንደፏለለ የሚኖርበት ዘመን ያከትማል፤ ጦስ ጥምቡሱ ግን ለብዙዎች ይተርፋል፡፡ አርቆ ማሰብ የሚያስፈልገው ለዚህ ነው፡፡ ዛሬ ለምሳሌ አማራውና ኦሮሞው እንዲሁም ሌላው በገርጂም ሆነ በሰሚትና በቦሌ ከመሬቱና ከንብረቱ እየተነቀለ ለባለጊዜው የጎሣ አባላት እንደልብ ቢታደል ይህ ዘመን ሲገለበጥ ተከፍሎ የማያልቅ ዕዳ ይመጣል፡፡ ይህን የምለው ውሻ ሆድ ውስጥ ቅቤ አያድርምና ሰሞኑን ወደሰሚት ሄጄ ሰዎች ያሳዩኝ ትልቅ መንደር ውስጥ ካለሀብቶምና ካለአብረኸት በስተቀር አንድም – ለውርርድ ያህል እንኳን – አንድም ዘበርጋና ደቻሳ ወይም ሸዋርካብሽና አሰጋኸኝ የሚባሉ ዜጎች የማይኖሩበት ምድረ ገነት በአዲስ አበባ መኖሩን ስለተረዳሁ ነው፤ አዲስ አበባና መቀሌን መለየት የማንችልበት አስገራሚ የታሪክ አንጓ ላይ መድረሳችንን የምገልጥላችሁ ነገ ሊከሰት የሚችለውን አደጋ ከወዲሁ በማጤን በታላቅ ፍርሀት ተውጬ ጭምር ነው – ወያኔና ይሉኝታ የማይተዋወቁ መሆናቸውን ቀድሜ ባውቅም ተጋሩ(ትግራውያን) ወገኖቼ ይህን ያህል ኅሊናቸውን ስተው የወያኔን የአድልዖ አሠራር በጭፍን ይከተላሉ ብዬ አምኜ አላውቅም – አዝናለሁ – ሀዘነይ ካብ ልበይ ኢዩ፡፡ ይህ ሁሉ ግፍ ጊዜው ሲደርስ የሚያስከትለውን ጠንቅ የማይረዳ ሰው ካለ የመጨረሻው ከንቱ ነው፡፡ “ፍቅር ያዘኝ ብለህ አትበል ደንበር ገተር፤ እኛም አንድ ሰሞን እንዲህ አርጎን ነበር” አለች አሉ ያቺ ምስኪን አቀንቃኝ፡፡ የተራ ጉዳይ ነው፡፡ ተራ ሲባል ደግሞ እንደወያኔ ያለ ዐይን ያወጣ አድልዖና ፍርደ ገምድልነት በእስካሁኑ ታሪካችን በግልጽ ታይቷል ለማለት እንዳልሆነ ይሰመርበት፡፡ በአፄው ዘመን በፊውዳላዊ መድሎ፣ በደርጉም በወታደራዊ መድሎ የተወሰነ ብልሹ አሠራር እንደነበር መናገር በደልን ያጥባል እንጂ ክፋት የለውም፡፡ የአሁኑ ግን በሀገራችን ቀርቶ በየትም ሀገር ያልተመዘገበ የአንድ ጎሣ ሁሉንም ነገር የማግበስበስ ሁኔታ በግልጽና ክፉኛ በሚያሳፍር አኳኋን እየታዬ ነው፡፡ በነዚህ ልጆቿ የነገይቷ ትግራይ እንዴት እንደምትሸማቀቅ ሳስበው የትግራይ መሬት ራሷ ታሳዝነኛለች፡፡ በርግጥም ላም እሳት ወለደች፡፡ አሁንም አዝናለሁ፡፡ እግዚአብሔርና አስተዋይ የአብራኳ ክፋይ የሆኑ ልጆቿ ይሁኗት ከማለት ውጪ ምን እላለሁ፡፡ እየታዬ ካው አሰቃቂ መድሎ አኳያ ለጊዜው ከዚህ የዘለለ ነገር መናገር አይቻለኝም – ችግር አለ!!!!!!!!….
ሕዝብን የሚመለከት፣ የሕዝብን ዕንባ የሚጠርግ፣ የሕዝብን ብሶት የሚያዳምጥ፣ ሕዝብን ማዕከል ያደረገ ዓለማቀፋዊ ዘመቻ ያስፈልገናል፡፡ የየሀገሩ ሕዝብ በአንድ ወይ በሌላ ምክንያት እያለቀሰ ነው፡፡ ጥቂቶች በሚፈጥሩት ችግር ቢሊዮኖች እየተሰቃዩ ነው፡፡ ይህ የጥቂቶች የበላይነትና ችግር ፈጣሪነት እስካልተወገደ ድረስ መዘዙ ለሁሉም ነው፡፡ ያስለቀሰ እያለቀሰ፣ ያለቀሰም እያስለቀሰ የሚሄድበት መጥፎ አዙሪት እስካልተወገደ ድረስ ዘላቂ መፍትሔ የለም፡፡ … የሰው ልጅ አእምሯዊ ይዘቱ የተዛባ ይመስለኛል፡፡ ራስህን በማለፊያ ምግብ አጥግበህ ሌላውን ስታስርብና ስታሰቃይ የምትደሰት ከሆነ ከእንስሳነትም ወርደሃል ማለት ነውና ሰብኣዊ ዕድገትህ ላይ ችግር መከሰቱን ልብ ማለት ሊኖርብህ ነው፡፡ አሳዛኝ ወቅት ላይ እንገኛለን፡፡
ወያኔን ግን በደምብ ዐወቅናት አይደል? እስኪ እዚች ላይም ትንሽ እንሳቅና እንዝናና – “ካልፈረማቸሁ እናስራችኋለን!!!” ጥጃ ገዝተው ወይም ወደማርካቶ ወጣ በማለት አንድ አምስትና ስድስት ሺህ ኢትዮጵያውያን የሰው እንስሳትን እንደለመዱት አያስሩም? ቅብጠታቸው ግን ለከትና ድንበር አጣ፡፡ ለነገሩ በጌታዋ የተማነች በግ ላቷን ቀለበት መንገድ ላይና አባይ ላይ ታስራለች ይባል የለም? ዘይገርም ሻሸመኔ ትብስ ኮፈኔ፡፡ ጉድ ነው፡፡
የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር በሰሞኑ ግርግር በአምቦና በሌሎች የሀገራችን አካባቢዎች ሕይወታቸውን ያጡ ወገኖቻችንን ነፍሳት በአብርሃምና በያዕቆብ ነፍሳት አጠገብ ያኑርልን፣ በጠባቡ ቃሊቲ የታሰሩትንም፣ በሰፊው “ዞን 9” የታሰርነውን እኛንም ፈጣሪ በቸርነቱ ይጎብኘን፡፡ አስቡ – ቀኒቷ ቀርባለች፡፡ ምልክቶች ሁሉ ታይተዋልና “ፕሊዝ” ወደየኅሊናችን በመመለስ ውስጣችንን እናጽዳ፡፡ ተመልሰን ሰው እንሁን፡፡ ሰው መሆን እንችላለን፤ መብትም አለን፤ ሰው ለመሆን ደግሞ በሕይወት እስካለን ድረስ ሁላችንም ልንሞክረው የሚገባን ታላቅ አምላካዊ ፀጋ እንጂ ቀነ ገደብ የተጣለበት ለማንም የተከለከለ ጉዳይ አይደለም፤ እናም ተስፋ ሳንቆርጥ ሰው ለመሆን እንሞክር፡፡ ያኔ ነው ከነዚህ ጉግማንጉጎች ነጻ የምንወጣው፡፡ አለበለዚያ በባርነት እየዳከርን ብዙ ጊዜ እንቆያለን – የባርነቱ ዘመን ይረዝምብናል፡፡ እናም ሰው በመሆን ፈጣሪን እናግዘው – የነጻነታችንን ጊዜም እናቅርብ፡፡
No comments:
Post a Comment