Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Tuesday, April 12, 2016

ከታቦት ጋር በተያያዘ ቀሲስ ዘማሪ እንግዳወርቅ በቀለ ለ 13 ቀናት ታሰረ


engida

“ታቦቱ በህጋዊ መንገድ የተቀረጸ ነው” 
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በዘማሪነት የሚታወቁት ቀሲስ እንግዳወርቅ በቀለ ለ13 ቀናት ከሌሎች አራት ሰዎች ጋር ታስረው በዋስ  መፈታታቸውን ከቅርብ ሰዎቻቸው በደረሰን መረጃ መሰረት ለማወቅ ከቻልንበት ደቂቃ ጀምሮ ቀሲስን በማግኘት ከራሳቸው አንደበት የእስራቸው ምክንያት ምን እንደነበር ለማወቅ ይገኙበታል የተባለን የስልክ ቁጥር ስንቀጠቅጥ አምሽተን በስተመጨረሻ ተሳክቶልን አግኝተናቸዋል::
ትናንት ገና ወደመኖሪያ ቤታቸው መግባታቸውን የገለጹልን ቀሲስ የእስራታቸው መንስኤ በህጋዊ መንገድ ተቀርጾ ኮሎራዶ ውስጥ ለምትገኝ ቤተክርስቲያን ሊላክ የነበረ ታቦት መሆኑን አጫውተውናል፡፡
ወደ አሜሪካ ለአገልግሎት ለማቅናት ተዘጋጅተው የነበሩት አባ ገ/ወልድ ቀሲስን በማግኘት ወደ አሜሪካ ለመሄድ መዘጋጀታቸውን በዚያ የሚገኙ የእምነቱ ተከታዮችም ማግኘት ከቻሉ ሁለት ታቦቶችን ይዘው እንዲመጡላቸው እንደጠየቋቸው በመንገር ታቦት ስለሚዘጋጅበት መንገድ ቀሲስ የሚያውቁት ነገር ስለመኖሩ እንደጠየቋቸው ያስታወሱት ዘማሪው ‹‹ጸጋዘዓብ የተባለ ሰውን እንዲያገኙና ታቦቱን ካዘጋጀላቸው በኋላ ለአባቶች በመንገር እንዲያስባርኩ በመምከር ሁለቱን ሰዎች አገናኘኋቸው››ይላሉ፡፡
ታቦት እንዴት በግለሰብ ይሰራል ይህንን የሚያክል ነገርስ ከቤተክህነቱ ውጪ እንዴት ይዘጋጃል በማለት ለቀሲስ ባቀረብንላቸው ጥያቄ ‹‹ታቦቱን ግለሰቡ የሚያዘጋጀው በቤተክህነቱ ፈቃድ ነው፡፡የተባለው ታቦት እንዲዘጋጅም በመጀመሪያ የአቡነ ሳሙኤል ፈቃድ ተገኝቷል፡፡አቡነ ሳሙኤል ታቦቱ እንዲቀረጽ የፈቀዱበት ወረቀትም እጃችን ላይ ይገኛል››ብለዋል፡፡
ሁለቱን ሰዎች ካገናኙ በኋላ ምን ደረጃ እንደደረሱ ጠይቀዋቸው ጭምር እንደማያውቁ የሚናገሩት ቀሲስ ‹‹ታቦቱን ለማሰራት ተነጋግረው የርክክቡ ሰዓት ሲደርስ አራዳ ጊዮርጊስ በተቃጠሩበት ወቅት ግርግር ተነስቶ ይከታተሏቸው በነበሩ ሰዎች አማካኝነት ፖሊስ ተጠርቶ ሲያዙ አባ ገ/ወልድ ደውለው አስጠርተውኝ ስለሁኔታው ለማስረዳት በሄድኩበት ፖሊስ አንተንም ለጥያቄ እንፈልግሃለን በማለት ለ13 ቀናት አስሮ ፈትቶኛል››ብለዋል፡፡
ታቦት ማስቀረጹ ህጋዊ ከሆነ ለምን ወዲያውኑ ንጹህነታችሁ ተረጋግጦ አልወጣችሁም በማለት ላቀረብንላቸው ጥያቄ ቀሲስ ‹‹ፖሊስ ፍርድ ቤት አቅርቦ የማጣራው ነገር አለ በማለቱ የምርመራ ጊዜ ጠይቆብን እንድንቆይ ተደርገናል፡፡በመጨረሻ ግን ምንም ነገር ስላልተገኘብን ሁላችንም እንድንወጣ ተደርገናል››፡፡
መዝገቡ ተዘግቶ በነጻ ተሰናበታችሁ ወይስ ዋስ እንድትጠሩ ተደረጋችሁ ብለናቸው ነበር በምላሻቸውም ‹‹ታቦቱን የቀረጸው 20.000 ፣ሊወስዱ የነበሩት እና እኔ 15.000 ሌሎቹ ደግሞ 10.000 ብር አስይዘን ወጥተናል››ብለዋል፡፡
ታቦቱ በህጋዊ መንገድ የተሰራ ነው የሚሉት ቀሲስ ተሐድሶዎች ስሜን ለማስጠፋት ሲሉ ያልተደረገ ነገር እንደተደረገ በማድረግ ቢያስወሩም ተቀበለ ስለተባልኩት ገንዘብ የማውቀው ምንም ነገር የለም››ማተቤን በገንዘብ እንደማልሸጥም ማንም ሰው ይመሰክርልኛል፡፡የእምነት ሰው በመሆኔ ይህ ለእኔ ፈተና ነው፡፡ነገር ግን እውነት ነጻ አውጥታኛለች››በማለት ማብራሪያቸውን አጠናቅቀዋል፡፡

No comments:

Post a Comment

wanted officials