Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Thursday, April 14, 2016

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያቤት በኢትዮጵያ የሚታየው የሰብአዊ መብት ጥሰት አለመሻሻሉን ገለጸ


ሚያዚያ ፮(ስድስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- 
የ2015ትን የአለም የሰብአዊ መብት አያያዝን የሚተነትነው ሪፖርት በኢትዮጵያ የሚታየው አፈናና ዜጎችን በእስር ቤት ማሰቃየት መቀጠሉን ይተነትናል፡፡
የአሜሪካ መንግስት በያመቱ በሚያወጣው የሰብአዊ መብት አያያዝ ሪፖርት የኢትዮጵያ የደህንነት ሰራተኞች ተቃዋዎችን ፣ ደጋፊዎቻውንና ጋዜጠኞችን እንደሚያሳድዱ፣ እንደሚያስሩ፣ በእስር ቤት ውስጥ አሰቃቂ ድደባ እንደሚፈጽሙ፣ እንዲሁም በህግ ስም ፖለቲካዊ ክስ እንደሚመሰር ዘርዝሮአል፡፡
ያለ ህግ እንደፈለጉ መግደል፣ ማሰር፣ ለፍርድ ቤት ሳያቀርቡ ዜጎችን ለረጅም ጊዜ በእስር ማቆየት፣ ለህይወት አደገኛ በሆነ እስር ቤት ውስጥ ማሰቃየት፣ በተራዘመ የፍርድ ሄደት ማሰቃየት፣ በዳኞች ላይ የፖለቲካ ተጽእኖ ማሳረፍ፣ የግለሰቦችን መብት መዳፈር፣ ህወገጥ ብርበራ ማካሄድ እንዲሁም በመንግስት የሰፈራ ፕሮግራም ከፍተኛ የሰብአዊ መብት ጥሰት መፈ‹ም የሚሉት ተጠቅሰዋል፡፡
ሀሳብን በመግለጽ በኩል የሚታየውን አፈና ሲዘረዝር ደግሞ በህትመትና በኢንትረኔት አገልግሎት ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እንደሚደረግ ፣ መሰብሰብ፣ መደራጀትና በነጻ መንቀሳቀስ የተገደበ መሆኑን፣የትምህርት ነጻነት መጥፋቱን፣ በሃይማት ጉዳይ ጣልቃ መግባት መቀጠሉ እንዲሁም በመንግስታዊና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ላይ የሚደረገው ቁጥጥር መጠናከሩን ያትታል፡፡
ዜጎች መንግስታቸውን፣ አስተዳደራቸውን፣ ፖሊሲንና በሙስና የተዘፈቁ ዳኞችን በሰላማዊ መንገድ የሚለውጡበት እድል አነስተኛ መሆኑን የሚጠቅሰው ሪፖርቱ፣ በሴቶችና ህጻናት ላይ የሚፈጸመው የመብት ጥሰትና መገለልም ቀጥሎአል ብሎአል፡፡
በኢትዮጵያ ዋናው ችግር ተጠያቂነት የሚባል ነገር አለመኖሩ ነው የሚለው የስቴት ዲፓርትመንት ሪፖርት፣ መንግስት በአብዛኛው ከሙስና በስተቀር ሌሎች ወንጀሎችን የሚፈጽሙ ባለስልጣናትን ለፍርድ እንደማያቀርብ ገልጾአል፡፡
ሪፖርቱ ካለፈው ምርጫ ጋር በተያያዘ 6 ሰዎች መገደላቸውን፣ እንዲሁም ከምርጫው በሁዋላ በሃመር ወረዳ በመንግስት እና በጸጥታ ሃይሎች መካከል በተነሳ ግጭት 48 ሰዎች መገደላቸውን ጠቅሶአል፡፡ የግጭቱ መንስኤ ህዝቡ በኢኮኖሚ ተጠቃሚ አለመሆኑ፣ የተፈጥሮ የግጦሽ መሬታቸውን መነጠቃቸው፣ መንግስት የሚያካሂደው የስኩዋር እርሻ ልማት የአካባቢውን ነዋሪዎች መሬት አልባ ማድረጉ እንዲሁም የአደን ክልከላ መሆናቸውን ሪፖር አመልክቶአል፡፡
በአማራ ክልል በጭልጋ ወረዳ ደግሞ ከቅማንት ጥያቄ ጋር በተያያዘ ፖሊስ በሰልፈኞች ላይ በወሰደው እርምጃ 6 ሰዎችን የገደለ ሲሆን፣ በርካቶችን አቁስሎአል፡፡በህዳር ወር ደግሞ ከአዲስ አበባ ማስተር ፕላን ጋር በተያያዘ፣ በኦሮምያ በተነሳው ተቃውሞ የጸጥታ ሃይሎች ከመጠን በላይ ሃይል መጠቀማቸውንና ግጭቱም ሪፖርቱ እስከተጠናከረበት እስከ ጥር ወር መቀጠሉን ጠቅሶአል፡፡
በጥቅምት 2014 ደግሞ በጋምቤላ የታጠቁ ሃይሎች 126 ፖሊሶችንና ነዋሪዎችን የገደሉ ሲሆን፣ ግጭቱም በመዠንገር ተወላጆችና በጸጥታ ሃይሎች መካከል መካሄዱን ገልጾአል፡፡
በማእከላዊ እስር ቤት ውስጥ ከፍተኛ የሆነ አሰቃቂ ድብደባ በመፈጸም፣ እስረኞች መረጃዎችን እንዲያወጡ ይገደዳሉ የሚለው ሪፖርቱ፣ እስረኞቹ እጆቻቸው ለፊጥኝ ታስሮ እንደሚንጠለጠሉ፣ ለርጅም ጊዜ እጆቻቸው በገመድ እንደሚታሰሩ፣ ውሃ እየፈሰሰባቸው እንዲሰቃዩ እንደሚደረጉ፣ የቃላት ማስፈራያ እንዲደርሳቸው ና ለብቻቸው ተነጥለው እንዲታሰሩ እንደሚደርግ ጠቅሶአል፡፡
ምንም እንኩዋን አገሪቱ 6 የፌደራልና 120 የክልል እስር ቤቶች ቢኖሩዋትም፣ ሌሎች ይፋ ያልሆኑ እስር ቤቶች በደዴሳ፣ ብር ሸለቆ፣ ጦላይ፣ ሆርማት፣ ባሌ፣ ታጠቅ፣ ጅጅጋ፣ ሆለታና ሰንቀሌ ይገኛሉ ብሎአል፡፡
መንግስት ከውጭ የሚተላለፉ የሬዲዮና የቴሌቪዥን ጣቢያዎችን ማፈን መቀጠሉን ሪፖርቱ ገልጾአል፡፡ መንግስትን ይቃወማሉ የሚባሉ ድረገጾች መዘጋታቸውን ከእነዚህም መካከል የግንቦት7፣ ኦነግ እና ኦብነግ ድረገጾች እንደሚገኙበት የሚገልጸው ሪፖርቱ፣ አልዘጂራና ቢቢሲ ሳይቀሩ አልፎ አልፎ ይዘጋሉ ብሎአል፡፡ በውጭ አገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ለመሰለል ፊን ፊሸር የሚባል ሶፍት ዌር መግዛቱም በሪፖርቱ ተጠቅሶአል፡፡
መንግስት ለስርአቱ ታማኝ ለሆኑት ብቻ የትምህርት እና የስራ እድል እንደሚሰጥ ሪፖርቱ አመልክቶ፣ የፓርቲ ስብሰባዎችን አንሳተፍም ያሉ መምህራን ከስራ እንደሚባረሩ እንዲሁም የተለያዩ እድገቶችና ጥቅሞች እንደሚቀርባቸው አትቶአል፡፡ በኦሮሞ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ላይ የሚደረገው ክትትልና ቁጥጥር እንዲሁም እስራት መቀጠሉን ሪፖርቱ አመልክቶአል፡፡
በአገር ውስጥ የሚታየው የህዝብ መፈናቀል ከዚህ በፊት ከነበሩት አመታት በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሮ እስከ ጥር ወር ድረስ 505 ሺ 104 ሰዎች ተፈናቅለዋል፡፡
በሪፖርቱ የቀረቡት የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እጅግ በርካታ በመሆናቸው ለወደፊቱ እንዳስፈላጊነቱ እየጠቀስን እናቀርባለን፡፡

No comments:

Post a Comment

wanted officials