በድርቅ የተመቱት የሰቆጣ አካባቢ ነዋሪዎች ቀያቸውን ጥለው እየሸሹ ነው
ኢሳት (መጋቢት 30 ፥ 2008)
በሰቆጣ የተከሰተው ድርቅ እየተባባሰ በመምጣቱ ነዋሪዎች ቀዬአቸውን ጥለው በመሰደድ ላይ መሆናቸው ታወቀ።
ከፊሉ ነዋሪ ወደ ባህር ዳርና መቀሌ ሲሰደድ፣ 400 የሚሆኑ ደግሞ ደብረ-ብርሃን መድረሳቸው ታውቋል።
ረሃቡን ሸሽተው ምግብ ፍለጋ ደብረ-ብርሃን ከደረሱት የሰቆጣ ነዋሪዎች ውስጥ አንዱ ለኢሳት እንደተናገሩት በአሁኑ ወቅት በሰቆጣ የቀሩት የመንግስት ሰራተኞችና ዕድሚያቸው የገፉ አዛውንቶች ብቻ ናቸው።
ነዋሪው በርሃብ ከደረሰበት ችግር ባሻገር የሚጠጣ ውሃ ለማግኘት ሁለት ቀናት ያህል መጓዝ ግድ ሆኖ በመገኘቱና በአጠቃላይ ችግሩ ከቁጥጥር ውጭ በመሆኑ ነዋሪዎቹ ቀዬአቸውን ጥለው ለመሰደድ መገደዳቸውን መረዳት ተችሏል።
በሰቆጣ የገባውን ረሃብ ሸሽተው የሚላስ የሚቀመስ ፍለጋ ደብረ-ብርሃን ከተማ የደረሱት የድርቁ ሰለባዎች ወገኖቻቸው ድጋፍ እንዲያደርጉላቸውም ጥሪ አቅርበዋል።
የደብረ-ብርሃን ከተማ አስተዳደር ድጋፍ እንደሚያደርግላቸው ቃል በመግባት እንዳጽኗኗቸው የተናገሩት የድርቁ ሰለባዎች፣ ለአንድ ሰው በወር የሚሰጠው 6ኪሎ ዱቄት በመሆኑ በዚህ እንዴት እንዘልቃለን ሲሉ ስጋታቸውንም ገልጸዋል። በደብረብርሃን ከተማ የአስተዳደር ጽ/ቤቱና በስላሴ ቤተ-ክርስቲያን አካባቢ የሚገኙት የሰቆጣ የድርቅ ሰለባዎች ኢትዮጵያውያን ወገኖቻቸው እንዲደርሱላቸው ጥሪ አቅርበዋል።
No comments:
Post a Comment