ኢሳት (ሚያዚያ 5 ፥ 2008)
ካለፈው ህዳር ወር ጀምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በኢትዮጵያ ጸጥታ ሃይሎች ቢገደሉም፣ አለም አቀፍ ማህበረሰቡ ዝምታን መምረጡ እንዳሳዘነው የሰብዓዊ መብቶች ጠባቂ ድርጅት (Human Rights Watch) ትናንት ባወጣው መግለጫ ገለጸ።
በኦሮሚያ ክልል የታየው ተቃውሞ ከምርጫ 97 በኋላ ከተቀሰቀሱት የፖለቲካ ቀውሶች ትልቁ እንደሆነ የገለጸው የሰብዓዊ መብቶች ጠባቂ ድርጅት (Human Rights Watch)፣ ይህ ተቃውሞ ግን በአለም አቀፍ መድረክ ያገኘው ተሰሚነት እጅግ አነስተኛ እንደሆነ ገልጿል።
የሰብዓዊ መብቶች ጠባቂ ድርጅት (Human Rights Watch) የመረጃ ምንጮችን ጠቅሶ እንደዘገበው በአሁኑ ሰዓት ከኦሮሚያ ክልል የሚወጣ መረጃ ባለመኖሩ ምን እየተደረገ እንደሆነ ለማወቅ እጅግ ከባድ ነው።
መንግስት የመረጃ ዝውውርን ለማገድ የሚዲያ አፈና አጧጡፎ ባለበት በአሁኑ ሰዓት፣ አብዛኞቹ የማህበራዊ ሚዲያ ድረገጾች ጭምር በአገር ውስጥ እንዳይታዩ እንደተደረገና፣ ባለፈው ወር ሁለት የውጭ ጋዜጠኞችም ጭምር የታሰሩበት ሁኔታ ተፈጥሮ እንደነበር የሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ ትናንት ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል።
የሰብዓዊ መብቶች ጠባቂ ድርጅት በኦሮሚያ ክልል በሚኖሩ 100 ኢትዮጵያውያን ላይ ያደረገው ጥናት እንደሚያመለክተው፣ የመንግስት ጸጥታ ሃይሎች ሰላማዊ ሰልፈኞች ናቸው ብለው በጠረጠሯቸው ሰዎች ላይ ሲተኩሱ፣ የዘጠኝ አመት ህጻናት ጭምር እንዳሰሩና፣ ካሰሯቸውም በኋላ ስቃይ ይፈጽሙባቸው እንደነበር መመስከራቸውን በሪፖርቱ አካቷል።
በኢትዮጵያ ውስጥ በአስቸጋሪ ሁኔታ የሚሰሩት ጥቂት የመገናኛ ብዙሃንና ዘጋቢዎችም አሰቃቂ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ለመዘገብ ያልፈደሩበት ምክንያት በእስር ከመሰቃየት፣ አገር ለቅቀው ከመሰደድና ራሳቸውን ሳንሱር ከማድረግ አንዱን መምረጥ ስለነበረባቸው እንደነበር ሪፖርቱ ያብራራል።
ለቃለመጠይቅ የሚደፍሩ ጥቂት ኢትዮጵያውያን ከፍርሃት የተነሳ ለውጭም ሆነ ለአገር ውስጥ ጋዜጠኞች በመንግስት ፖሊሲ ላይ ትችት እንደማያቀርቡና፣ ትችት ያቀረቡት ግን እንደታሰሩና እንደተንገላቱ የሰብዓዊ መብቶች ጠባቂ ድርጅት (ሂውማን ራይትስ ዎች) በሪፖርት አስፍሯል።
ከውጭ የሚተላለፉ የሳቴላይት ቴለቪዥንና ሬዲዮ ጣቢያዎች ስርጭት እንዳይሰማ የኢትዮጵያ መንግስት የጸጥታ ሃይላት በማሰማራት በግለሰቦች ቤት የተተከሉትን የሳተላይት መቀበያ ሳህኖችን እንደሰባበረና፣ በሁዋላም የሳተላይት አቅራቢ ድርጅቶች ውላቸውን እንዲያቋርጡ እንዳስገደዳቸው ትናንት የወጣው አጭር ሪፖርት አትቷል።
በኦሮሚያ በተቀሰቀሰው ተቃውሞ የመረጃን ክፍተትን በመጠኑም ቢሆን የሞላው የማህበራዊ ሚዲያ መሆኑን በሪፖርቱ ላይ ያሰፈረው የሰብዓዊ መብቶች ጠባቂ ድርጅት (ሂውማን ራይትስ ዎች)፣ በአመጹ ሰዓት የቆስሉ ሰዎችን የቀረጹና ቪዲዮዎችን በፌስቡክ ያሰራጩ ስዎችን የመንግስት ጸጥታ ሃይሎች እየተከታተሉ እንዳሳደዷቸው ሪፖርቱ ያስረዳል።
ይህንን ለመግታት ሲባል የኢትዮጵያ መንግስት የድምጽና ምስል ስርጭት ግልጋሎት የሚሰጡ ማህበራዊ ሚዲያዎችን እንደዘጋ ሰብዓዊ መብቶች ጠባቂ ድርጅት ገልጿል። በመሆኑም ህጻናትን ጨምሮ በኢትዮጵያውያን ላይ የተፈጸሙት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ለአለም አቀፍ ማህበረሰብ ሳይደርሱ ቀርተዋል ብሏል።
የሰብዓዊ መብቶች ጠባቂ ድርጅት የኢትዮጵያ መንግስት በዚህ አይነት ሸፍጥ በተሞላበት ሁኔታ ለረጅም ጊዜ ሊቀጥል እንደማይልች በሪፖርቱ ላይ አስፍሯል።
የኢትዮጵያ መንግስት በኦሮሚያ ለተፈጸመው የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ከአጋር ድርጅቶችና አገሮች ጋር በመሆን፣ ነጻና ገለልተኛ አጣሪ ቡድን እንዲያቋቁም መክሯል። የህዝቡን መብት ለማፈን የወጡትንና የመገናኛ ብዙሃን ነጻነትን የሚጋፉ ህጎች የኢትዮጵያ መንግስት እንዲሽራቸውም ጠይቋል። ይህ ሳይሆን ቀርቶ በኦሮሚያ እየሆነ ያለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ከቀጠለ፣ በኢትዮጵያ አንድነት፣ ሰላምና ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚያሳድር የሰብዓዊ መብት ድርጅት ሪፖርት አብራርቷል።
No comments:
Post a Comment