6ኛ ፓትርያርክ እናስመርጣለን ተብሎ የይስሙላ ምርጫ በማድርግ አባ ማትያስን መሾም ሽር ጉድ በሚባልበት ወቅት ይህ ሒደት ሕገ ቤተክርስቲያንን የጣሰ ወይም ያልተከተለ ከመሆኑ የተነሣ ማኅበረ ቅዱሳን የዚህ አስቂኝ ጨዋታ ተካፋይ መሆኑ በእጅጉ አስከፍቶኝ በወቅቱ እስኪ ግልጽ ያልሆነልኝ ነገር ካለ ብየ ዋና ጸሐፊውን ሔጀ አናግሬው ነበር፡፡
ምላሹ ምንም ሊያሳምነኝ አልቻለም፡፡ ብዙ አወራን ተከራከርንም፡፡ የገባኝ ነገር ምንድን ነው ማኅበሩ የሰጥቶ መቀበልን ጨዋታ ለመጫወት መገደዱን ነው፡፡ ስለሆነም ምን አልኩት የሰጥቶ መቀበል መርሕ የሚሠራው ለፖለቲካ እንጅ ለቤተክርስቲያን አይደለም፡፡ ምክንያቱም ሰጥቸ እቀበላለሁ ሲባል መርከስ፣ መንጠብ፣ የማይገባ ነገር መፈጸም፣ ከማይገባ ግብር ጋር መተባበር ይመጣልና በእነዚህ ድርጊቶችም እግዚአብሔር የሚቀየምበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ ከእሱ እጅ ያጣነውን ከሌላ እጅ ልናገኘው የምንችል ይመስል እንዲህ ማሰብ በፍጹም ክርስቲያናዊ አስተሳሰብ አይደለም፡፡
ስለሆነም ይህ ጨዋታ ለፖለቲካ (ለእምነተ አሥተዳደር) እንጅ ለቤተክርስቲያን አይሠራም አያዋጣም፡፡ ቤተክርስቲያን ላይ የሚሠራው “በጊዜውም አለጊዜውም ጽና” 2ጢሞ. 4፤2 በሚለው ቃሉ መሠረት ጸንቶ የእግዚአብሔርን መጠበቅ ነው፡፡ ለማየት ያብቃህ እኒህ ሰውዬ ከአባ ጳውሎስ የባሱ የከፉ ቤተክርስቲያንን አዋኪ፣ ችግር ፈጣሪ ነው የሚሆኑት፡፡ ብየው ነበር፡፡ ያልኩት አልቀረም ሰውየው ማሰብ ማገናዘብ የሚባል ነገር የሌላቸው አቅለ ቀላል ተኩላነታቸውን ማሳየት ሲጀምሩ ብዙም አልቆዩም ነበር፡፡
ከሦስት ሳምንታት በፊት ባለፈው ወር ሚያዚያ 23 ቀን የማኅበረ ቅዱሳን የጥናትና ምርምር ክፍል የአድዋን ድል አስመልክቶ አንድ ያዘጋጀው ዝግጅት ነበር፡፡ በዝግጅቱ ሁለት ጥናት አቅራቢዎች ጥናታቸውን እንዲያቀርቡ ተደርጎ ነበር፡፡ አንደኛው በጎንደር ዩኒቨርስቲ የታሪክ መምህር ሲሆኑ ሌላኛው እዛው ከማኅበሩ ነበሩ ያቀረቡት፡፡ጥናት አቅራቢዎቹ በተሰጣቸው ርእሰ ጉዳይ ላይ በጥሩ ሁኔታ ጥናታቸውን አቅርበዋል፡፡
- የቅኝ ገዥዎችን ቅኝ የመግዛት ፍላጎት ሊፈጥሩ የቻሉ ምክንያቶች
- የቅኝ ገዥዎች ዓላማና ፍላጎት
- የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ነጻነታችን ላለማስደፈር ለመጠበቅ ያደረጉት ተጋድሎ
- የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን አስተዋጽኦ በአድዋ ድል ላይ
በሚሉ ነጥቦች ላይ ባላቸው አጭር ጊዜ ጥሩ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ ጥናት አቅራቢዎቹ ጥናታቸውን ካቀረቡ በኋላ ከታዳሚው ጥያቄዎችና አስተያየቶች ቀረቡና ምላሽ እንዲሰጡም ተደርጎ ነበር፡፡ በርከት ያሉ ታላላቅ ሰዎች ግሩም ግሩም የሆነ የየራሳቸውን ሐሳብ አስተያየት ሰጥተው ነበር፡፡ ከጥያቄዎችና አስተያየቶች በኋላም እኔ አንድ ያስተላለፍኩት ማሳሰቢያ ነበር፡፡ ማሳሰቢያውም በወቅቱ ያልታወሱኝን አኃዞች ጨምሬበት ይሄንን ይመስል ነበር፡-
““ እኛ ኢትዮጵያዊያን ነጻነታችንን ለመንጠቅ የተደረጉብን ተደጋጋሚ የጠላት ወረራዎች ጦርነቶች ውጊያዎች ተደርገው ተፈጽመው ነገር ግን ሳይሳኩ ቀርተው ከሽፈው ያለፉ ያበቃላቸው ውጊያዎች ጦርነቶች ወረራዎች እንደሆኑ ማሰባችን ከፍተኛ ዋጋ እያስከፈለን ነው፡፡ ይህ አስተሳሰባችን ልናደርገው የሚገባንን መከላከልና የመልሶ ማጥቃት ዝግጅት እንዳናደርግ አድርጎ እያስማረከን ውድ ዋጋም እያስከፈለንም ይገኛል፡፡
የአድዋውም ሆነ የኋለኛው የማይጨው ጦርነቶች ያኔ ተፈጽመው ያለቁ አይደሉም! እስከአሁንም የቀጠሉና ግባቸውን እስኪመቱ ድረስም ወደፊት የሚቀጥሉ ናቸው፡፡ እርግጥ ነው የሚጮህ የመሣሪያ ድምፅ የለም፡፡ ጦርነቱ ግን ተጧጡፎ ቀጥሏል እየተሸነፍንባቸውም ነው፡፡
በዚህም ምክንያት እንደምታዩት በአሁኑ ሰዓት እኛ ኢትዮጵያዊያን እንደ አንድ ሀገር ሕዝብ ሁሉ በሀገር ጉዳይ ላይ የጋራ መግባባትና የጋራ ጥቅም እንዳይኖረን አድርገውናል፡፡ ሌላው ቀርቶ ዓለም በሚያደንቀውና በቅኝ ገዥዎች በተገፉ የዓለም ሕዝቦች ዘንድ በከፍተኛ ደረጃ አክብሮት በተቸረውና በሚደነቀው በዚህ እያከበርነው ባለነው የአድዋ ድል እንኳን አንዳይነት የሆነ አመለካከትና አስተሳሰብ እንዳይኖረን አድርገውናል፣ በሀገራችን ታሪክ እሴቶች ማንነት ጉዳይ ላይ ምንቅርቅራችንን አውጥተውት ብዙዎቹን በሀገር ታሪክ ማንነት እሴቶች ላይ በጠላትነት እንዲሰለፉ ማድረግ ችለዋል፣ ከገዛ ዩኒቨርስቲዎቻችን (መካናተ ትምህርት) የታሪክ ትምህርት እንዲሰረዝ ማድረግ ችለዋል፣ የሀገሪቱን ሕልውና በቋፍ እንዲሆን አድርገዋል ሌላው ቀርቶ የሚገርማቹህ ነገር ለየካቲስ 12 የሰማእታት መታሰቢያ የቆመውን ሐውልት ገላጭ አካላቱን ሁሉ እያወላለቁ እየሸራረፉ አጉድለውታል አበላሽተውታል እዚህ ድረስ ወርደው ነው ሥራቸውን እየሠሩ ያሉት፡፡
በማኅበረ ቅዱሳን ላይ ከሁለት አቅጣጫ (ከቤተ ክህነትና ከቤተ መንግሥት) እየተሰነዘረ ያለው ጥቃትም የዚህ ጦርነት አንዱ አካል ነው፡፡ የእነዚህ ጥቃቶች የማዘዣ ማዕከላት የሮማ ቤተመንግሥትና የቫቲካን ቤተክህነት ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን በጣሊያን ወረራ ከባድ ኪሳራ ደርሶባታል፣ ከባድ ዋጋ ከፍላለች፣ከሁለት ሽህ በላይ አብያተክርስቲያናት እንዲቃጠሉ ተደርጓል፣ በገዳማቶቿ የነበሩ ከዐሥር ሽህ በላይ መነኮሳቷ በፋሽስት ጣሊያን ወታደሮች በጥይት ተደብድበው ወይም በሰይፍ ተቀልተው እንዲገደሉ ተገርገውባታል በቁጥር ከሚታወቁት ውስጥ መጥቀስ ቢያስፈልግ በደብረ ሊባኖስ 732፣ በማኅበረ ሥላሴ 515፣ በደብረ ዳሞ 2116፣ በዝቋላ 211፣ በመርጦለማርያም 363፣ በአሰቦት 91፣ በአዲስ ዓለም 143፣ በምድረከብድ 60 ያለቁ ሲሆኑ የነበሩባቸው ገዳማትም በፋሽስቱ ወታደሮች ተመዝብረዋል ተዘርፈዋል፣ ቁጥራቸው ከማይታወቁት ደግሞ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው በጣና ሐይቅ ገዳማት የነበሩ መነኮሳት፣ ዓመታዊ ክብረ በዓል በሚከበርበት ወቅት በተለያየ ቦታ በአውሮፕላን (በበረርት) ቦምብ (ፈንጅ) ዘንቦበት ያለቀው ሕዝብ ለምሳሌ በጎጃም ደብረ መዊዕ ወዘተረፈ.
ከሁሉም ደግሞ ቤተክርስቲያንን የጎዳት ካለቁት አባቶች ውስጥ ቤተክርስቲያን እስከዛሬ ልትተካቸው ያልቻለቻቸው ወደፊትም ይተካሉ ተብለው የማይታሰቡ ሊቃውንቶቿ በተሸከርካሪ እየተጎተቱ፣ በጥይት እየተደበደቡ፣ በሰይፍ እየተቀሉ አረመኔያዊ በሆነ ሁኔታ ተፈጅተው እንድታጣቸው መደረጉ ነው፡፡
ቫቲካን በሰጠችው ቡራኬ በተፈጸመው የግፍ ወረራ ይህ ሁሉ ግፍ እንደተፈጸመ ስለሚታወቅ እንዲሁም ቅዱስ ቃሉ “ከማያምኑ ጋር በማይመች አካሄድ አትጠመዱ፤ ጽድቅ ከዓመፅ ጋር ምን ተካፋይነት አለውና? ብርሃንም ከጨለማ ጋር ምን ኅብረት አለው? ክርስቶስስ ከቤልሆር ጋር ምን መስማማት አለው? ወይስ የሚያምን ከማያምን ጋር ምን ክፍል አለው?” 2ኛ ቆሮ. 6፤14 በሚለው ሐዋርያዊ ግዝት፣ ከዚያም በኋላ እነ ዲዮስቆሮስ ቄርሎስና አትናቴዎስ ታላላቅ የቤተክርስቲያን መሪዎችና ሌሎችም ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ባስተላለፉት ግዝት ምክንያት የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ከቫቲካን ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት አልነበራትም፡፡
ከሁለት ዐሥትት ዓመታት ወዲህ ግን መጀመሪያ አባ ጳውሎስ አሁን ሰሞኑን እንዳያቹህት ደግሞ አባ ማትያስ ከዚህች እጇ በዐሥር ሽዎች በሚቆጠሩ ንጹሐን ዜጎቻችን ደም ከተጨማለቀ የቫቲክን “ቤተክርስቲያን” ጋር ቅዱስ ቃሉን እንዲሁም የእነ ቅዱስ ዲዮስቆሮስን ቅዱስ ቄርሎስና ቅዱስ አትናቴዎስን እንዲሁም የሌሎችን ሊቃውንተ ቤተክርስቲያንን ግዝት በመተላለፍ ዓላማውና ተልዕኮው ግልጽ ያልሆነ ግንኙነት መሥርተው ድብቅ የጥፋት ሥራቸውን ሲሠሩ ቆይተዋል እየሠሩም ይገኛሉ፡፡ ጭራሽም አባ ማትያስ በአደባባይ “እኛና ካቶሊኮች ልዩነት የለንም!” እስከማለት መድረሳቸው የሚታወቅ ጉዳይ ነው፡፡
በነዚህ ነውረኛ ግለሰቦችና አባሪዎቻቸው ተግባርም ቤተክርስቲያን ጥቅሟን እንድታጣ፣ ክብሯ እንዲደፈር፣ ያለቁ የንጹሐን ደም ደመ ከልብ ሆኖ እንዲቀር ተደርጓል፣ አስተምህሮዋ እየተቆነጻጸለ ይገኛል፡፡ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን በታሪኳ የገዛ አባቶቿ ናቸው በሚባሉ ግለሰቦችና ቡድኖች ክህደት ሲፈጸምባት ይሄ ክህደት የመጀመሪያው ነው፡፡
ቤተክርስቲያን በቫቲካን ቡራኬ በተፈጸመው ወራራና በአምስት ዓመቱ የወረራ ወቅትም በካቶሊክ ካህናት ለተፈጸመባት አረመኔያዊ ግፍና በደል ይቅርታ አልተጠየቀችም፣ ካሳም አልተከፈላትም፡፡ ይህ ባልተፈጸመበት ሁኔታ ከላይ የጠቀስኳቸው የቤተክርስቲያን መሪዎች አስቀድሞ የቅዱሳን አባቶች ግዝት ያለ በመሆኑና ቅዱስ ቃሉም ስለሚከለክል የእኛ ቤተክርስቲያን ቫቲካንን እንደ አቻ ቤተክርስቲያን ቆጥራ ልትመሠርተው የምትችለው ምንም ዓይነት ግንኙነት ባይኖርም እንደ ማንኛውም ተቋም እንኳን ቆጥረን እውቅና ሰጥተን ግንኙነት የመሠረትን ቢሆንም እንኳን ሀገርንና ቤተክርስቲያንን ውርደት ለማሸከም ታስቦ ካልሆነ በስተቀር ለቤተክርስቲያንም ሆነ ለሀገር ምንም ዓይነት አግባብነትና ጠቀሜታም የለውም፡፡
ሰዎቹ በመግለጫቸው ግልጽ እንዳደረጉልን ግንኙነቱ የተፈጸመው የቤተክርስቲያናችንን ግዝት በመተላለፍ የአቻ ላቻ ግንኙነት እንደፈጠሩ ነው ያስታወቁት፡፡ ሥጋታችንም ይሄ ነው፡፡ ግዝት ከመጣሱም በላይ ዕድሜ ዘመኗን ይህችን ቤተክርስቲያን ለማጥፋት ያልጣረችው የጥረት ዓይነት ከሌላት የጥፋት አካል ጋር ምን የሚያገናኝና የሚያወዳጅ ጉዳይ ኖሮ ነው ግንኙነቱ የተመሠረተው? የዓላማ አንድነት ከሌለ በስተቀር! ይሄም ግልጽ ሆኗል “እኛና ካቶሊክ ልዩነት የለንም!” በሚል ተገልጾ፡፡
እጅግ የሚገርመው ነገር ይሄ ሁሉ ሲሆን ቅዱስ ሲኖዶስ ተብየው በዚህ ጉዳይ ላይ ምንም ያለው ነገር አለመኖሩ ነው፡፡ ይህ ዛሬ በጨረፍታ በፈራ ተባ የተነገረ ቃል ነገ በይፋ በድፍረት መነገሩ የማይቀር መሆኑ ነው አሳዛኙ ዜና፡፡ ያኔ እንደ ማኅበረ ቅዱሳን ያሉ ተቋማት አስቀድመው እንዲጠፉ ካልተደረገ በስተቀር ታላቅ እንቅፋት የሚሆኑ በመሆናቸው ነው ከወዲሁ የግድ ማኅበረ ቅዱሳንን ማጥፋት እንዳለባቸው አምነው ታጥቀው የተነሡት፡፡ ለዚህም ነው ከላይ “በማኅበረ ቅዱሳን ላይ ከሁለት አቅጣጫ (ከቤተ ክህነትና ከቤተ መንግሥት) እየተሰነዘረ ያለው ጥቃትም የዚህ ጦርነት አንዱ አካል ነው፡፡ የእነዚህ ጥቃቶች የማዘዣ ማዕከላት የሮማ ቤተመንግሥትና የቫቲካን ቤተክህነት ናቸው” ስል የገለጽኩት፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን ይሄንን የሚያውቅ ይመስለኛል፡፡ የሚያውቅ ከሆነ የጦርነቱን ክብደትና ውስብስብነት በሚገባ በተረዳ መልኩ እየደረሰብን ያለውን ውጊያና ጥቃት ለመመከት በሚያስችል በቂ ዝግጅት ጥንካሬና ብቃት መሰለፍ እንችል ዘንድ ያለውን የተጋፈጥነውን ችግር ለሕዝበ ክርስቲያኑን አሳውቆ ያለብንን ጦርነት እንድንመክት የሚያስችል ዝግጅት እንዲያደርግና እንዲያሰልፈን አጥብቄ ማሳሰብ እወዳለሁ”” በማለት ነበር ማሳሰቢያውን የተናገርኩት፡፡
ማኅበረ ቅዱሳን ጥርስ ውስጥ የገባው አሁን አይደለም፡፡ “ለምን?” ለሚለው ጥያቄ በየመድረኩ የወያኔ ካድሬዎች የሚናገሩት “በሀገሪቱ የአንድነት ኃይል የሆነ መኖር አይችልም!” የሚል ሕግ ያለ ይመስል ካድሬዎቹ የሚናገሩት “ማኅበረ ቅዱሳን የአንድነት ኃይል (አንድነትን የሚሰብክ) ስለሆነ ነው እንዲጠፋ የምንፈልገው እንዲኖር የማንፈቅደው!” የሚል ነው፡፡ አያይዘውም “የአንድነት ኃይል ከሆኑት በፖለቲካው (በእምነተ አሥተዳደሩ) መስክ ያሉትን በሙሉ አዳክመናል ሰብረናል በትነናል፡፡ ከአንድነት አቀንቃኞች የቀረን ማኅበረ ቅዱሳን ብቻ ነው እሱን ሳንበትን ሳናጠፋ እንቅልፍ አንተኛም!” ሲሉ ይደመጣሉ፡፡
በእርግጥ እንዳሉትም ወያኔ በማኅበረ ቅዱሳን ላይ ጥርሱን የነከሰበት ምክንያት ይሄ ሊሆን ይችላል፡፡ ብቸኛው ምክንያት እንዳልሆነ ግን እርግጠኛ ነኝ፡፡ የቫቲካንና የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ግንኙነት እንዲፈጥሩ ትዕዛዝ ሰጥቶ እያስፈጸመ ያለው አገዛዙ እንደሆነ በግልጽ ይታወቃልና፡፡
በዛም ሆነ በዚህ በማኅበረ ቅዱሳን ላይ እየተሰነዘረ ያለው ጥቃት ምንጩ ከምዕራቡ ዓለም ዕኩያን እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ “ማኅበረ ቅዱሳን ለኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ሕግ ሥርዓትና ቀኖና መጠበቅ፣ ትውፊቶቿን እንዳይጠፉ ጠብቀው ለያዙት የአብነት ትምሕርት ቤቶች ህልውና ቀጣይነት የጸና አቋም ስላለውና አንዳች ነገር ብሎ ሕዝብ እንዲቃወም ለማድረግ ቢፈልግ ተደማጭነት ስላለው እሱ ባለበት ሁኔታ ምንም ዓይነት ሥራ ልንሠራ አንችልም!” የሚል ግንዛቤ ወስደዋል፡፡
ማኅበሩ እየደረሰበት ያለውን መከራ ለሕዝበ ክርስቲያኑ ይፋ ሳያደርግ ብዙ ተቀጥቅጧል፡፡ ይፋ አለማድረጉና ዋጋ እየከፈለበት ያለበት ጉዳይ ባለቤት ሕዝበ ክርስቲያኑ መሆኑን ለሕዝበ ክርስቲያኑ አለማሳወቁ ብዙ ዋጋ እያስከፈለው ይገኛል፡፡ ብዙ ከመቀጥቀጡ የተነሣም ዝሏል፡፡ ከመዛሉ የተነሣም በርካታ ዕንቁዎቻችንን ከእጁ ጥሏል፡፡
ለምሳሌ ለቤተክርስቲያን ከንዋዬ ቅድሳት የመጀመሪያው የሆነውን ዘፍ. 9፤9-17 መንግሥት ከቤተክርስቲያን ወስዶ የሀገሪቱ ሰንደቅ ዓላማ ያደረገውን ትእምርተ ኪዳኗን (ሰንደቅ ዓላማዋን) እንዲጥል እንዲተው ተደርጓል፣ እንደ “አንድ ሃይማኖት! አንዲት ጥምቀት! አንድ ጌታ!” ኤፌ. 4፤5 እና “ለቅዱሳን አንድ ጊዜ ፈጽሞ ስለ ተሰጠ ሃይማኖት እንድትጋደሉ እየመከርኋችሁ እጽፍላችሁ ዘንድ ግድ ሆነብኝ” ይሁ. 1፤3 ያሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን እንዳይጠቀም ተደርጓል፣ ቤተክርስቲያን ለዚህች ሀገር ባለ አደራ እንደመሆኗና የሀገርንና የሕዝብን አንድነት መስበክ ዐቢይ ተግባሯና ከሐዋርያዊ ተልእኮዋ አንዱ በመሆኑ ማኅበሩ የሀገር አንድነትን በሚሰብክበት ጊዜ “ፖለቲካ ነው በዚህ ጉዳይ ላይ ምንም ማለት አትችሉም!” እየተባለ ሊገናኙ የማይችሉ ነገሮች በግድ እየተገናኙ የሀገረ እግዚአብሔርን አንድነት እንዳይሰብክ በማዕቀብ ታስሯል፣ በወያኔ ካድሬ መሞላቱን እያየ ይሄም ለህልውናው አደጋ መሆኑን እያወቀ በዝምታ እንዲመለከት ተደርጓል ወዘተረፈ.
እነ አባ ማትያስና ይሄንን ዕኩይና ሰይጣናዊ ተልእኮ አንግበው አብረው እየተንቀሳቀሱ ያሉት መናፍቃኑ ግን “ለምንድን ነው ማኅበረ ቅዱሳንን እንዲህ ጠምዳቹህ የያዛቹህት እሱን ሳናጠፋ አንተኛም! የሚያሰኛቹህ ቤተክርስቲያንን ምን ስለበደለ ነው?” ብለው “ቤተክርቲያንን እንዲህ እንዲህ አድርጎ ስለበደለ!” ብለው ሊጠቅሱት የሚችሉት አንዲትም ምክንያት ሊናገሩ አልቻሉም፡፡ ይሄም በመሆኑ ነው የማኅበሩ አመራር “ጥፋታችን ምንድን ነው? እባክዎን ያነጋግሩን?” ብሎ አባ ማትያስን ለማነጋገር በተደጋጋሚ ላቀረበው ተማጽኖ ያዘለ ጥያቄ በጎ ምላሽ ሊያገኝና ሰውየውን ለማናገር ዕድል ሳያገኝ የቀረው፡፡
ሰውየው ከመናፍቃኑ ጋር ግንባር ፈጥረው ይሄንን ሁሉ ጥቃት ሲፈጽሙ ለአንድም ጊዜ እንኳን “የሲኖዶሱን” ይሁንታና ፈቃድ ሳያገኙ እንዲያውም “የሲኖዶሱን” ወይም የቤተክርስቲያንን አቋም ዓላማና ጥቅም በተጻረረ መልኩ ነው ይሄንን ሕገ ወጥና ሥርዓት አልበኝነት የተሞላበት የውንብድና ድርጊት እየፈጸሙ ያሉት፡፡
ይሄም ምንን ያሳያል የዚህ የጥቃት ተልእኮ ፍላጎትና ትእዛዝ ከቤተክርስቲያን ውጪ መሆኑንና ባለቤቱ እራሳቸው አለመሆናቸውን ትእዛዝ ፈጻሚ መሆናቸውን ያሳያል “ትእዛዝ ሰጪውና የጥፋት ዓላማው ባለቤት ማን ነው?” የተባለ እንደሆን የጋራ ጥቅም ያስተባበራቸው መናፍቃኑና ወያኔ ናቸው፡፡
እንግዲህ ያለው ሀቅ ይሄ ነው፡፡ ሕዝበ ክርስቲያኑ ቤተክርስቲያን የተጋፈጠችውን አደጋ ጠንቅቆ በመረዳት አደጋውን ሊያከሽፍ በሚችል ደረጃ እራሱን አዘጋጅቶ እንቅስቃሴ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ ማኅበረ ቅዱሳንን ለማፍረስ ለማጥፋት የሚወሰድን ማንኛውም ዓይነት እርምጃ በቸልተኝነት ተመልክተን በዝምታ ለማሳለፍ ከፈቀድን ግን ያለ ምንም ጥያቄና መልስ ይህችን ቤተክርስቲያን ካቶሊካዊትና ፕሮቴስታንታዊት እንድትሆን ፈቀድን ማለት እንደሆነ እያንዳንዱ ክርስቲያን ጠንቅቆ ሊውቅ ይገባል፡፡
እኛ ምእመናን ከግብጽ ቤተክርስቲያን ምእመናን ልንማረው የሚገባ አንድ ተቃሚ ተሞክሮ አለ፡፡ በአምስተኛው መቶ ክ/ዘ እንደኛ ዓይነት ችግር ገጥሟቸው ነበር፡፡ የቁስጥንጥንያው ንጉሥ መርቅያንና የሮማው ፓፓ ተማክረው ፓትርያርካቸውን ዲዮስቆሮስን አንሥተው አሰሩትና ፕሮቴሪየስ የተባለ የራሳቸውን ሰው ፓትርያርክ አድርገው ሾሙላቸው፡፡ ምዕመናን አንቀበልም ብለው አባረሩት፡፡
መርቅያን በምእመናን ምላሽ ተቆጥቶ ሁለት ሽህ ያህል ሠራዊት ላከባቸውና በግድ እንዲቀበሉ ለማድረግ ጥረት አደረገ ምእመናን ግን ቁጣቸው አይሎ በተፈጠረው ሁከት አዲስ የተሾመው ፓትርያርክ ተገደለ፡፡ በዚህም መሀል ዲዮስቆሮስ በእስር እንዳለ አረፈ፡፡ ለሦስት ዓመታት ያህል መንበሩ ክፍት ሆኖ ከቆየ በኋላ እራሳቸው ምእመናኑ ጢሞቴዎስን ሾሙት፡፡ እሱም ጥሩ አባት ሆኖ አገለገላቸው፡፡ የታወከችው ቤተክርስቲያንም ተረጋጋች፡፡ እኛ ግና እራሳችንን ወደን ለሥጋችን አድልተን ቅድስት ቤተክርስቲያንን ለጭራቆች አሳልፈን ሰጠን፡፡ ከእንግዲህ ግን ቢበቃስ?
ሕዝበ ክርስቲያኑ አስቀድሞ በአባ ጳውሎስ አሁን በአባ ማትያስ እየተደረገ ያለውን የእብደትና የጠላት ሥራ ማመን ተቸግሮ በሰፋ ትዕግሥት ማሳለፉ ቤተክርስቲያንን በርካታ ዋጋ እያስከፈለ ሰዎቹንም ለመለጠ ድፍረትና የዕብደት ሥራ እያበረታታ ይገኛል፡፡ ይህ ሁኔታ በዚህ መቀጠል የለበትም!
ለዚህች ሀገርና ሕዝብ ተቆርቋሪ ቤተክህነትና ቤተ መንግሥት በዚህች ሀገር ቢኖር ኖሮ ትውልዱ እንዲህ በሱስ ማጥ ውስጥ ሰምጦ ሀገር ተረካቢ ትውልድ አጥታ በመከኑ ዜጎች እየተሞላች እየከሰረች ባለችበት ዘመን ከማንም ምንም ሳይጠብቁ በራሳቸው መዋጮ ማኅበር መሥርተው ሀገራዊና ሃይማታዊ የዜግነት ግዴታቸውን ለመወጣት የሚታትሩ የተማሩ ወጣቶች ማኅበር በዚህች ሀገር መኖሩ ጮቤ ሊያስረግጣቸው ሊያስደስታቸው ሊያረካቸው ምን እንርዳቹህ? በምን እንደግፋቹህ? ሊያሰኛቸው እንጅ ሊያበሳጫቸው ሊያስከፋቸው እንዴት አድርገን? ምን አሳበን? ባጠፋናቸው ሊያሰኛቸው ባልቻለ ነበር፡፡ አእምሮ ቢኖራቸው ማሰብ ቢችሉ ማኅበረ ቅዱሳን በቢሊዮኖች (በብልፎች) የሚቆጠር ብር ቢፈስ ሊገነባ የማይችል የሀገር ሀብት መሆኑን መረዳት በቻሉ ነበር፡፡
እንግዲህ ውሳኔው የሕዝበ ክርስቲያኑ ነው፡፡ ኧረ ባያድለን እንጅ እንደዜጋ የሌላውም ዜጋ ጉዳይ ነበር፡፡ ሕዝበ ክርስቲያን ሆይ! ቤተክርስቲያንንና ሀገርህን ለዚህች ሀገርና ሕዝቧ ጥንተ ጠላቶች ለባዕዳንና ለተቀጣሪ ባንዶች አሳልፈህ ሰተህ ታስበላታለህ ወይስ እንደ እናት አባቶችህ ዋጋ ከፍለህ ትታደጋታለህ?
እስኪ እባካቹህ በሀገሩ የምትታፈሩ የምትፈሩ ታላላቅ ሰዎች አረጋዊያን ሽማግሎች ካላቹህ ቤተክህነቱንም ሆነ ቤተ መንግሥቱን “ማኅበረ ቅዱሳን እንዲጠፋ ያስፈረደበት የተላለፈው በሕግ የሠፈረ ወንጀሉ ምንድን ነው?” ብላቹህ እስኪ ጠይቁ እባካቹህ!፡፡ እኛ ዜጎች ሀገራችንን ሕዝባችንንና ቤተክርስቲያናችንን እንዳናገለግል “አትችሉም!” የማለት መብትና ሥልጣን ያለው ማንና እንዴትስ ሆኖ? በምንስ ምክንያትና በየትኛውስ ሕግ ነው? ቤተክርስቲያንና ሀገር የሕዝብ ሆነው ሳለ እንደግል ንብረቱ ቆጥሮ ከቤተክርስቲያንና ከሀገር ጥቅም በተጻራሪ ለግል ጥቅሙ ሲል ሕገ ወጥና ሥርዓት አልበኝነት የተሞላ የግፍ ድርጊት እየፈጸመ እንዲፋንንብን መብት የተሰጠው ማንና ከማንስ ነው? ይሄንን ዓይን ያወጣ ግፍና በደልንስ ሕዝብ እንዴት ነው ሊታገስ የሚችለው???
ልዑል እግዚአብሔር የዚህችን ሀገርና ቤተክርስቲያን ሰላምና ደኅንነት ይመልስልን!!! ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
No comments:
Post a Comment