ዐውደ ርእዩ እንዲታይ ተፈቀደ
ታግዶ የነበረው ዐውደ ርእይ እንዲታይ መፈቀዱ ተሰማ፡፡ የእገዳ ትእዛዙ የተሰጠው ከማን እንደኾነ በተደጋጋሚ ለማወቅ የተደረገው ጥረት በመጨረሻ ተሳክቶ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር የማኅበሩ አመራር ባደረገው ውይይት መፈቀዱ ዐቢይ የደስታ ዜና ነው፡፡ ከደኅንነት ስጋት ጋር በተያያዘ እንደታገደ ይገመታል፡፡ ለጊዜው ያገድሁት እኔ ነኝ ብሎ የሚቀርብ አካል አለመኖሩ ግራ አጋብቶ የነበረ ቢኾንም ይመለከታቸዋል ተብለው ከተገመቱት የመንግሥት አካላት ጋር የተደረጉ ውይይቶች መፍትሔውን ወልደውታል፡፡
በእርግጥ አሁን መፈቀዱ ብቻውን የት፣ እንዴት እና መቼ ይታያል? የሚለውን አይመልሱ ይኾናል፡፡ ምክንያቱም የዐውደ ርእይ ማዕከሉ ቀደም ሲል በተያዙ የትንሣኤ ዋዜማ የግብይት መርሐ ግብሮች እንደተጨናነቀ ስለሚታወቅ፡፡ ይሁን እንጂ የዝግጅት ልዑካኑ እስከመጨረሻው ያሉትን አማራጮች ለማየት እና ሙከራ ለማድረግ ወዲያ ወዲህ ተፍ ተፍ እያሉ ይገኛሉ፡፡ ከተሳካላቸው በወርኀ ጾሙ ጊዜ ውስጥ ለማሳየት የሚቻልበትን ሁኔታ ለማመቻቸት ይህ ካልኾነ ግን በበዓለ ሃምሳ እንዲታይ ለማድረግ ይታሰባል፡፡
ረድኤተ እግዚአብሔር ታክሎበት ማዕከሉን ቀደም ብለው ከያዙት አካላት ጋር ውይይት በማድረግ ጥቂት ቀናት ተገኝተው አሁን ቢታይ እንዴት ደስታችን ሙሉ በኾነ፡፡ ይኽም ባይኾን ግን መፈቀዱ ብቻውን የሚሰጠው ትርጉም እጅግ ከፍ ያለ ነው፡፡ የእገዳው መነሣት የሚሰጠው የትርጉም ጓዝ ከማስደሰትም ባለፈ መልእክትም አለው፡፡
ከሁሉ በላይ የአጽራረ ቤተ ክርስቲያን ዓላማ እና ምኞት እጅግ ከፍተኛ ኪሣራ ውስጥ መግባቱ ስንመለከት እና ጨብጠነዋል ብለውት የነበረው ጉዳይ ድሮውንም ቢኾን በእጃቸው እንዳልነበረ ማስመስከሩ፣ እነዚህ አጽራረ ቤተ ክርስቲያን (የሩቆችን ትትን የቅርቦች መኾናቸውን ሳንዘነጋ) ከመቼውም ጊዜ በላይ የሚያንገበግባቸውን የማኅበሩን ውድቀት ሊመለከቱ ቀርቶ ተቃራኒው ሲኾን ለማየት ሲገደዱ ወድደን ብቻ ሳይኾን ፍቅሩ አገብሮን እግዚአብሔርን እንድናመሰግነው ያደርገናል፡፡
ከአሁን አሁን ገፋነው ሄደልን ወጣልን ብለው ሲመኙ እግዚአብሔር የበለጠ እግሮቹን በጽኑ ዓለት ላይ ሲያቆማቸው እያዩ፣ ጨብጠነዋል ሲሉ እያመለጣቸው፣ አበቃለት ከሰመ ሲሉ እየፈካባቸው ታላቅ የራስ ምታት ኾኖባቸዋል፡፡ በተለይም በሐራጥቃ አሰላለፍ የሠለጠኑ እና እንደ ቅድሚያ የትግል አማራጭ አድርገው የቀየሱት የማኅበሩን ጥፋት ማየት እንደ ግብ ይዘውት ይልፉ እንጂ ጠብ አላለላቸውምና፡፡ አልገባቸውም እንጂ እየታገሉ ያሉት ከአንድ ማኅበር ጋር አይደለም፡፡ ትግላቸው ስንት የመከራ እና የግፍ ዘመናትን አልፋ በእሳት እየተፈተነች ለእሳቱም እሳት የኾነችውን ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ እርሷ ደግሞ ከምድር እስከ ሰማይ የተዘረጋ የማይነቀነቅ መዋቅር ያላት ናትና በአልፎ ሂያጆች አትበገርም፡፡
ሐራጥቃዎች ሺህ ጊዜ ጨበጥነው ሲሉ እልፍ ጊዜ የሚያመልጣቸውን ትግል በመጀመራቸው ጸጸታቸው እየበረታ ኪሳራዎቻቸውን በመቁጠር ላይ እንዲጠመዱ አድርጋቸዋለች፡፡ ሰልፉ የእግዚአብሔር ነውና!
ሁለተኞቹ የቅርብ አጽራረ ቤተ ክርስቲያን አዝማደ ሙሰኞች ሲኾኑ የእነርሱም ጥረት ሌላ ነበረ፡፡ ጊዜ የሰጠው ቅል እንዲሉ ድንጋይ ለመስበር ወቅታዊ የሥልጣን ቁመናቸውን በመጠቀም ዐውደ ርእዩ እንዲታገድ የአቋም መግለጫ እስከማውጣት ደርሰው ነበረ፡፡ ሰልፉ የእግዚአብሔር ነበረና አመከነባቸው እንጂ! አሳገድነው እያሉ ጥቂት ሳያማስኑበት በአጭሩ አስቀረባቸው፡፡ በገንዘብ ምርኮ ከሚያበዙት ይልቅ እግዚአብሔር በእንባ የሚማርኩትን መረጠ፡፡ ሣር ነጭታ እንደጠገበች ዕዋል ባናፉበት አንደበታቸው ይናገሩት ዘንድ አሳጣቸው፡፡ በእነዚህ ሁለት አካላት ላይ ተፈቀደ የሚለው ዜና እንደ መብረቅ አናት የሚሰነጥቅ፣ እንደ እሳት የሚፋጅ፣ እንደ ንዳድ ብርክ ብርክ የሚያስብል የቁም መቅሰፍት ነው፡፡
በእርግጥ የዐውደ ርእዩ ዓላማ ከተሳካ ቆየ፡፡ ለመድረክ ሳይበቃ ዓላማውን ቀድሞ ያሳካ ዐውደ ርእይ ተብሎ ይመዘገብ ዘንድ ይገባዋል፡፡ ምናልባትም ብቸኛው ባለታሪክ ሊኾን እንደሚችል እገምታለሁ፡፡ ግን ሁለተኛ ግቡ ሳይዘገይ ቶሎ በመታየቱ እግዚአብሔርን ከልባችን እናመሰግነዋለን፡፡ ሁል ጊዜም ቀድመህ የምትዋጋልን ጌታችን ሆይ ለዘለዓለሙ እናመሰግንሃለን እያልን ሥራችንን እንቀጥላለን፡፡ መፈቀዱ ባይታይም እንኳ ዐቢይ ድምጽ አለው፡፡ ፍጹም የሚኾነው ደግሞ ሲታይ ነውና እርሱ እንዲሳካ እንጸልያለን፡፡
No comments:
Post a Comment