Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Friday, April 29, 2016

የትግራይ ደንበር የት ላይ ነው? ከ ዶክተር አንዳላማው




ከርዕሱ ጋር በተያያዘ ፕሮፌሰር አለሜ እሸቴ ያቀረቡትን ጽሑፍ በቅርቡ እዚህ ገጽ ላይ ለጥፌው እንደነበር ያያችሁ እንደምትኖሩ እገምታለሁ፡፡ በዚያ ጽሑፍ መሠረት ወልቃይትና ፀለምት ወደ ትግራይ (በዚያን ጊዜው አጠራር ወደ ኤርትራ) የተጠቃለሉት በፋሽስት ኢጣልያ ውሳኔ እንደነበረና ዓላማውም በአካባቢው እየተጠናከረ የነበረውን የአርበኞች እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር የሚያስችል ሁኔታ ለመፍጠር መሆኑን ተረድተናል፡፡ ጉዳዩን አስመልክቶ የተካሄደው ስብሰባ አጀንዳ ራሱ ውሳኔው ለጊዜው (temporary) እንደሆነ ይገልጻል፡፡
ኢትዮጵያን እንደገና ለማዋቀር... በብሔረሰብ ክልሎች በመክፈል የመጀመሪያውን እርምጃ የወሰዱት ጣልያኖች ስለነበሩ፤ ባቋቋሟቸው ክልሎች ውስጥ ደግሞ የኤርትራው ክልል ከፍ ያለ ቦታ የተሰጠው ስለነበረ ገና ከመጀመሪያው ይህን አካባቢ ለአማራ የሚተውበት ምክንያት የነበረ አይመስለኝም፡፡ ይህ ጽሑፍ ሃሰት ነው የሚል ማስረጃ እስካልቀረበ ድረስ “የቀዳማይ ወያነ እንቅስቃሴ ከተመታ በኋላ በንጉሡ ውሳኔ የትግራይ መሬቶች ለጎንደር ተሰጡ” የሚለው ትረካ ስህተት ነው ብለን መደምደም እንችላለን፡፡
ወደ ዋናው ጉዳይ ስንገባ ህወሓት ስልጣን ከያዘበት ጊዜ አንስቶ በጣም አጨቃጫቂ ሆነው ከዘለቁት ጉዳዮች አንዱ ከሰሜናዊው ጎንደር ተቆርሰው ወደ ትግራይ የተካለሉት አካባቢዎች ጉዳይ መሆኑን እንረዳለን፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የተለያየ አመለካከቶች እንደሚንፀባረቁ ማውራት ጥቅም ላይኖረው ይችላል፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ወገኖች ያልሰሟቸው ነጥቦች ሊኖሩ ስለሚችሉ ልጠቃቅሳቸው ፈለግኩ፡፡
1. በ1990 አካባቢ (ጊዜውን እርግጠኛ አይደለሁም) ባህርዳር ላይ ተደርጎ በነበረ የብአዴን ካድሬዎች ስብሰባ ላይ ተነሳ ተብሎ በከተማው የተናፈሰ ወሬ ነበረ፡፡ በዚህ ወሬ መሠረት ከስደት ተመላሽ የሆኑ ኢትዮጵያውያን በመተማና በሁመራ መካከል እንዲሰፍሩ ይደረጋል፡፡ እንዳጋጣሚ ሆኖ ከነዚህ መካከል አብዛኞቹ የትግራይ ልጆች ስለነበሩ ከጥቂት ጊዜ በኋላ “ልጆቻችንን በትግርኛ ማስተማር ስለምንፈልግ መንግሥት ይህን አገልግሎት ያሟላልን” ብለው ይጠይቃሉ፡፡ በአካባቢው የነበሩ የብአዴን ካድሬዎች ጥያቄውን ይዘው በባህርዳሩ ስብሰባ ላይ ይገኛሉ፡፡ “ልጆቻቸውን በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው ለማስተማር ያቀረቡት ጥያቄ ተገቢ ነው፤ ይሁን እንጅ ከተወሰኑ ዓመታት በኋላ በአካባቢው የሰፈረው ሕዝብ ትግርኛ ተናጋሪ ስለሆነ ወረዳችን ወደ ትግራይ ይካለል ቢሉስ?” በሚል መልክ ያቀርቡታል፡፡ በዚያ ጊዜ ከፍተኛ ጭቅጭቅ እንዳስነሳና በአመራሩና በካድሬዎች መካከል “አንተ፣ አንተ” እስከመባባል እንዳደረሰ ሰምተን ነበር፡፡
2. በ1992 ታኅሣስ ወር ጎንደር ላይ ከአሜሪካ የመጡ የአካባቢው ተወላጆችና የብአዴን አመራር አባላት የተሳተፉበት: በጎንደር ልማት ላይ ያተኮረ ስብሰባ ተካሂዶ ነበር፡፡ ከአሜሪካ ከመጡት የጎንደር ተወላጆች አንዳንዶቹ “የወልቃይት ጉዳይ መፍትሔ ሳያገኝ ስለጎንደር ልማት ማውራት ጥቅም የለውም” በሚል መንፈስ በምሬት የተሞላ አስተያየት ሰንዝረዋል፡፡ በዚህ ጊዜ ከብአዴን ሰዎች የተሰጣቸው መልስ “በእኛ አመለካከት የወልቃይት ጉዳይ የተዘጋ ርዕስ ነው፤ ሕዝቡ ትግርኛ ተናጋሪ በመሆኑ በትግራይ ክልል ስር መሆኑ ትክክል ነው ብለን እናምናለን” የሚል ነበር፡፡ ጥያቄውን ለማርገብ ግን “'አይ፣ አከላለሉ የሕዝብን ፍላጎት አያንፀባርቅም' የሚል ወገን ታች ወርዶ ከሕዝቡ ጋር መወያየት፣ ካስፈለገም ሕዝበ-ውሳኔ እንዲካሄድ መጠየቅ ይችላል” የሚል ሃሳብ ተሰንዝሮ ነበር፡፡
3. በ1995 አካባቢ (ይህንንም ትክክለኛውን ጊዜ ዘንግቸዋለሁ) የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ለክልሉ ሕፃናት ተጨማሪ ኢትዮጵያዊ ቋንዎችን ስለማስተማር ጥናት አካሂዶ ነበር፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የሕዝብ አስተያየት ምን እንደሚመስል ለመቃኘት ጎንደር ላይ ስብሰባ ይጠራል፡፡ እንደሰማነው ለተሰብሳቢዎቹ የተወሰነ ገለጻ ከተደረገ በኋላ “ልጆቻችሁ ትግርኛ ቢማሩ ምን ይመስላችኋል?” የሚል ጥያቄ ይቀርባል፡፡ የሕዝቡ መልስ ቁጣ የተቀላቀለበት ነበር ተብሎ ተነግሮኛል፡፡ አነጋገራቸው “ዛሬ ወልቃይትን አስወሰዳችሁ፣ ነገ ደግሞ ጠቅላላዋን ጎንደርን በትግራይ ስር ልታደርጓት ፈልጋችኋል ማለት ነው” የሚል ነበር፡፡ ጉዳዩ ከፍተኛ ቁጣ ከማስከተሉ የተነሳ በጊዜው የነበረው የትምህርት ቢሮ ኃላፊ በቪኦኤ የአማርኛ ክፍል ቃለመጠይቅ ተደርጎለት ነበር፡፡
4. አሁን በቅርቡም ‘ደንበር ተሻግራችሁ አረሳችሁ፤ ከዚህ ክልል ፈቃድ ሳታገኙ እዚህ ማረስ አትችሉም፣ ወዘተ.’ አይነት ውዝግቦች እንደተነሱና ደም እስከመፋሰስ እንደደረሰ ይወራል፡፡
በእኔ አመለካከት የነዚህ ችግሮች ምንጭ የፌዴሬሽኑ አወቃቀር ነው፡፡ የፌዴሬሽኑ አካላት የሆኑት ክልሎች (ቢያንስ የተወሰኑት) የተመሠረቱት አንቀጽ 39ን ታሳቢ አድርገው ይመስለኛል፡፡ አንቀጽ 39ን ተግባራዊ ለማድረግ የመጀመሪያው ጥያቄ “የክልሉ ደንበር የት ነው?” የሚለውን መመለስ ስለሆነ ያንን ‘በሰላሙ ጊዜ’ መጨረስ ግድ ይላል፡፡ በተጨማሪም አንቀጽ 39ን አንድ ቀን ልጠቀምበት እችላለሁ ለሚል ክልል ‘አሁን ያለው ሁኔታ አገርነትን የመለማመጃ ጊዜ ነው ወይ’ የሚል ስጋትም አለ፡፡
መፍትሔ አለው?   ከ ዶክተር አንዳላማው
---------------------
የማያዋጣው የመፍትሔ ሃሳብ ውዝግብ በተነሳባቸው አካባቢዎች ሁሉ ውሳኔ-ሕዝብ ማካሄድ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ለምን ቢባል ውሳኔ-ሕዝብ ለማካሄድ መጀመሪያ ድምፅ የመስጠት መብት ያላቸውን ወገኖች መለየት ስለሚያስፈልግ ጥያቄው በዚህ ላይ ተቀርቅሮ እንደሚቀር አያጠያይቅም፡፡ (የሞሮኮና የምዕራብ ሰሃራን ምሳሌ ማየት ይበቃል፡፡ ውሳኔ ሕዝቡ እስካሁን ያልተካሄደው ሞሮኮና ፖሊሳሪዮ ማን ድምፅ ይስጥ በሚለው ላይ ስላልተስማሙ ነው፡፡) በበኩሌ ‘ገምት’ ብባል እነዚህ አካባቢዎች ወደ ትግራይ መካለላቸውን የሚቃወሙ ወገኖች ‘ከ1983 በኋላ ወደ አካባቢው የመጡ ሰዎች ድምፅ የመስጠት መብት ሊኖራቸው አይገባም’ እንደሚሉ አስባለሁ፡፡
ተግባራዊ ሊሆን ይችላል ብዬ የማስበው የመፍትሔ ሃሳብ….
1. ቋንቋን ብቻ መሠረት ያደረገውን የክልሎች አመሠራረት በጥልቅ ፈትሾ የተሻለ አደረጃጀት መፍጠር (የድሮዎቹን ክፍላተ ሃገር መነሻ ማድረግ የሚቻል ይመስለኛል፡፡)
2. በተለያዩ ክልሎች የሚኖሩ የአንድ ብሔረሰብ አባላት የሚገናኙበት የባህል ማዕከላት ማቋቋም፡፡ እነዚህ ማዕከላት የየብሔረሰቡን ባህልና ቋንቋ የማጥናት፣ የመንከባከብና የማዳበር ዓላማ ቢኖራቸው ይጠቅማል፡፡
3. ‘ለአንድ ብሔረሰብ አንድ ክልል’ የሚለውን መነሻ ሃሳብ መሰረዝ (ከስዊትዘርላንድ መማር እንችላለን)
4. እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በቋንቋው የመጠቀም፣ በአካባቢ መስተዳድሮች በመራጭነትም ሆነ በተመራጭነት ያለገደብ የመሳተፍ መብቱን ማስከበር
5. ወላጆች “ልጆቻችን በዚህ ቋንቋ ይማሩልን” የሚል ጥያቄ ሲያቀርቡ ያንን ማሟላት የመንግሥት ግዴታ መሆኑን መቀበል፡፡
6. ክልሎች፣ ወረዳዎችና ቀበሌዎች ነዋሪዎቹ የሚጠቀሙባቸውን ቋንቋ/ዎች መሠረት አድርገው የየራሳቸውን የሥራ ቋንቋ/ዎች አውጀው መጠቀም፡፡ (ይህ አሁንም መሬት ላይ ያለ አሠራር ነው፡፡)
7. በፌዴራል ደረጃ ተጨማሪ ቋንቋዎች የሥራ ቋንቋ የሚሆኑበትን ዘዴ መቀየስ፡፡
-------
የያዘውን የወረወረ… በሚለው እሳቤ ያቅሜን ያህል ይህችን ሃሳብ አቅርቤያለሁ፡፡ የእናንተን ለመስማት ደግሞ ጓጉቻለሁ፡፡ በሰከነ መንፈስ እንደምንወያይ ተስፋ በማድረግ አስተያየቶቻችሁን እጠብቃለሁ፡፡

  ከ ዶክተር አንዳላማው https://www.facebook.com/endalamaw.aberra?fref=ufi


No comments:

Post a Comment

wanted officials