Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Wednesday, April 6, 2016

የብሪታኒያ ፓርላማ የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ጉዳይን በልዩ ሁኔታ ለመከታተል ወሰነ


ኢሳት (መጋቢት 28 ፥ 2008)
የብሪታኒያ ፓርላማ የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ በእስር ላይ የሚገኙትን የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ጉዳይን በልዩ ሁኔታ ለመከታተል ወሰነ።
የሃገሪቱ መንግስት የዜጋውን መብት ለማስጠበቅ የተቻለውን ሁሉ አላደረገም ሲሉ የቀረቡ አቤቱታዎችንና ተቃውሞዎችን ዋቢ በማድረግ ኮሚቴው የአቶ አንዳርጋቸው ፅጌን ጉዳይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ለመከታተል እንደወሰነ የብሪታኒያ መገናኛ ብዙሃን ረቡዕ ዘግበዋል።
የብሪታኒያ መንግስት ለሰብዓዊ መብት መከበር በቂ ትኩረት አለመስጠቱን የተቸው የፓርላማው የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ ሃገሪቱ በሰብዓዊ መብት አያያዝ የጎደፉ ስም ያላቸውን ሃገራት ለማውገዝ እንኳን አለመድፈሩ ስጋትን እንዳሳደረም አመልክቷል።
የአውሮፓ ፓርላማና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አቶ አንዳርጋቸው ፅጌን ከእስር እንዲለቀቁ ጥያቄን ቢያቀርቡም፣ የብሪታኒያ  መንግስት ተመሳሳይ ጥያቄን አለማቅረቡም በኮሚቴው ትችት ቀርቦበታል።
በእነዚህና በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ በሃገሪቱ መንግስት ላይ ተቃውሞን ያቀረበው ኮሚቴው የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ጉዳይን ጨምሮ ሌሎች አበይት ጉዳዮችን በልዩ ሁኔታ ለመከታተል እንደወሰነ ይፋ አድርጓል።
በቅርቡ በኢትዮጵያ ጉብኝት ያደርጋሉ ተብለው የሚጠበቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዴቪድ ካሜሩን የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ጉዳይን ልዩ ትኩረት ሰጥተው እንዲያነሱም የተለያዩ አካላት ግፊት እያደረጉ እንደሆነም ታውቋል።
ከአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ጉዳይ በተጨማሪ የብሪታኒያ ፓርላማ የውጭ ጉዳዮች ኮሚቴ በግብፅ በእስር ላይ የሚገኝን የአንድ የአየርላንድ ታዳጊ ወጣት ጉዳይንም በልዩ ሁኔታ እንደሚከታተለው ገልጿል።
ታዳጊ ወጣቱ ከሶስት አመት በፊት በካይሮ ከተማ በተካሄደ አንድ የተቃዋሚ ሰልፍ ላይ ተሳታፊ ሆኗል ተብሎ በቁጥጥር ስር ውሎ የሚገኝ ሲሆን የሞት ቅጣት ይተላለፍበታል ተብሎ ተሰግቷል።
የብሪታኒያ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋም የሆነውና የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ጉዳይን የሚከታተለው ሪፕሪቭ ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ማያ ፎያ ፓርላማው የሰብዓዊ መብት ጉዳዮች በልዩ ሁኔታ ለመከታተል መወሰኑ ተገቢና ወቅታዊ መሆኑን አስታውቀዋል።
የብሪታኒያ አጋር የሚባሉት ኢትዮጵያ ግብፅ ተደጋጋሚ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እየፈጸሙ እንደሆነም ሃላፊዋ አክለው ገልጸዋል።

No comments:

Post a Comment

wanted officials