Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Saturday, April 9, 2016

በጅጅጋ በጎርፍ አደጋ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 28 ደረሰ


በጅጅጋ ከተማ ዙሪያ ጥሎ የነበረውን ከባድ ዝናብ ተከትሎ በተከሰተው የጎርፍ አደጋ የሟቾች ቁጥር 13 እንደነበር ቢገለፅም ቁጥሩ በትንሹ 28 መድረሱን አሶሼይትድ ፕሬስ የተለያዩ መረጃዎችን ዋቢ በማድረግ ማክሰኞ ዘግቧል።
በዚሁ አደጋ ከ80 የሚበልጡ ነዋሪዎች ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን ግምቱ በትክክል ሊታወቅ ያልቻለ ንብረትም መውደሙ ታውቋል።
የከተማዋ ነዋሪዎች በእንቅልፍ ላይ እያሉ በደረሰው በዚሁ የጎርፍ አደጋ በትንሹ 55 ሰዎች የገቡበት አለመታወቁንና የነፍስ አድን ሰራተኞች ፍለጋቸውን ቀጥለው እንደሚገኙም ተውቋል።
በተመሳሳይ የጎርፍ አደጋ በአፋር ክልል መጋሌና ዳሎል ወረዳዎች በትንሹ አምስት ሰዎች የሞቱ ሲሆን ከ270 በላይ ቤቶችና ከ2ሺ በላይ ፍየሎች በጎርፍ ተወስደዋል።
የብሄራዊ አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን በበኩሉ ከባድ ዝናብ በደቡብ፣ አማራና ኦሮሚያ ክልሎች እንደሚቀጥልና ከአንድ ሚሊዮን በላይ ነዋሪዎችም ለአደጋው ተጋላጭ እንደሚሆኑ ማክሰኞ ገልጿል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከወራት በፊት በሃገሪቱ የአየር ጸባይ ለውጥን የተከተለ የጎርፍ አደጋ ሊከሰት ይችላል ሲል ማሳሰቡ ይታወሳል።
እሁድ ምሽት በጅጅጋ ከተማ ደርሶ በነበረው የጎርፍ አደጋ አንድ አባት ስድስት ልጆቻቸውንና ሁለት የቤተሰብ አባሎቻቸውን በጎርፍ ካጡ በኋላ በደረሰባቸው ሃዘን ራሳቸውም ከሰዓታት ቆይታ በኋላ መሞታቸው ይታወቃል።
በዚሁ አደጋ ጉዳይ የደረሰባቸውን ነዋሪዎች ለመርዳትም ርብርብ እየተካሄደ መሆኑን አሶሼይትድ ፕሬስ በዘገባው አመልክቷል።

No comments:

Post a Comment

wanted officials