በሶማሊ ክልል 24 ወረዳዎች ለረሃብ ሊጋለጡ እንደተቃረቡ ተመድ ገለጸ
ኢሳት (መጋቢት 30 ፥ 2008)
በኢትዮጵያ ተከስቶ ያለው የድርቅ አደጋ መባባስን ተከትሎ በሶማሊ ክልል ብቻ ለረሃብ ሊጋለጡ የተቃረቡ ወረዳዎች ቁጥር 24 መድረሱን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አርብ አስታወቀ።
በዚሁ የድርቅ አደጋ ከቀያቸው የሚፈናቀሉ ሰዎች ቁጥርም መጨመርን አሳይቶ እስከ ባለፈው ወር ድረስ በክልሉ ከ 147 ሺ በላይ ሰዎች ከመኖሪያ ቤታቸው መሰደዳቸውን ድርጅቱ ይፋ አድርጓል።
የሶማሊ ክልል በድርቅ ከተጠቁት ስድስት ክልሎች አንዱ ሲሆን፣ ግጭቶችና የጎርፍ አደጋዎች ተጨማሪ ችግርን እየፈጠሩ መሆናቸውም ታውቋል።
በክልሉ ባሉ ግጭቶች 17ሺ 238 ሰዎች ከመኖሪያ ቀያቸው መፈናቀላቸውን የገለጸው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የግጭቱ መንስዔ ከመግለጽ ተቆጥቧል። በድርቁ ሳቢያ ከተፈናቀሉ ሰዎች መካከልም ወደ 30ሺ አካባቢ የሚሆኑት ህጻናት ሲሆኑ የተፈናቃይ ሰዎች ቁጥር እያደገ መምጣቱም ተገልጿል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ጨምሮ የተለያዩ አለም አቀፍ የእርዳታ ተቋማት በሃገሪቱ ተከስቶ ያለው የድርቅ አደጋ ወደ ረሃብ ሊለወጥ ይችላል ሲሉ በማሳሰብ ላይ ናቸው።
በሶማሊ ክልል ወደ ረሃብ ደረጃ ሊሸጋገሩ አንድ ደረጃ ከቀራቸው 24 ወረዳዎች በተጨማሪ 45 ወረዳዎች ልዩ ክትትልን የሚፈልጉ ተብለው በሁለተኛ ደረጃ መፈረጃቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በሪፖርቱ አመልክቷል።
በክልሉ የሚገኙት የፋፋን እና ሲቲ ዞኖች በዚሁ የድርቅ አደጋ ክፉኛ ጉዳት ኣየደረሰባቸው የሚገኝ ሲሆን፣ በሌሎች ክልሎች የሚገኙ በርካታ ወረዳዎች በአስከፊ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኙ ለመረዳት ተችሏል።
ለተረጂዎች እንዲደርስ የታሰበ የእርዳታ እህል በጎረቤት ጅቡቲ ወደብ ቢደርስም በወደቡ ተፈጥሯል የተባለው መጨናነቅ የእርዳታ እህሉ ለተረጂዎች በወቅቱ እንዳይደርስ ተጽዕኖ ማሳደሩም ታውቋል።
የእርዳታ እህሉ በሚፈለገው ሰዓት ለተረጂዎች ባለመቅረቡ ምክንያት በርካታ ሰዎች ለምግብ እጥረት ተጋልጠው እንደሚገኙ የእርዳታ ድርጅቶች ይገልጻሉ።
የመንግስት ባለስልጣናት በበኩላቸው በጅቡቲ ወደብ ለሳምንታት ወረፋን ሲጠባበቁ የነበሩት ከ10 በላይ መርከቦች የእርዳታ እህላቸውን ለማራገፍ ወደ ሱዳንና ሶማሊላንድ (በርበራ) ወደብ በማቅናት ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
No comments:
Post a Comment