Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Tuesday, April 19, 2016

የግዕዝ ፊደል የዩናይትድ እስቴትስ የባለቤትነት መብት ኣገኘ



ዋና መሥሪያ ቤቱ ብራይተን ኮሎራዶ የሆነው የኢትዮጵያ ኮምፕዩተሮችና ሶፍትዌር ቍጥሩ ዘጠኝ ሚሊዮን ዘጠኝ መቶ ኃምሳ ሰባት የሆነ የዩናይትድ እስቴትስ የባለቤትነት መታወቂያ (ፓተንት) መጋቢት ፳፱ ቀን ፳፻፯ ዓ.ም. ማግኘቱን ኣስታወቀ። (http://patents.com/us-9000957.html) ፓተንቱ የተሰጠው ለፈጠራውና የኩባንያው ባለቤት ለዶ/ር ኣበራ ሞላ ሲሆን ኩባንያው የእርሳቸውንና የባለቤታቸው የሠናይት ከተማ ነው።



“ኣብሻ” ሥርዓት በመባል በታወቀው ኣዲስ ዘዴ መጀመሪያ መርገጫ ላይ ያሉት ቀለሞች የሚከተቡት እያንዳንዳቸው በኣንድ መርገጫ ሲሆን ሌሎቹ በሁለት መርገጫዎች ብቻ ነው። ይህ ኮምፕዩተሮች፣ የእጅ ስልኮችና ተመሳሳይ መሣሪያዎች ውስጥ የእንግሊዝኛ ፊደላት ከሚከ ተቡበት ኣንዳንድ ዘዴዎች ጋር የተቀራረበ ነው። በተጨማሪም ቍጥሩ 20090179778 (http://www.google.com/patents/US20090179778) የሆነውን የፈጠራውን ገለጻ የኣሜሪካ መንግሥት ከኣተመበት ሓምሌ ፱ ቀን ፳፻፩ ዓ.ም. ወዲህ የዶክተሩን ጽሑፍ የጠቀሱ ስድስት ኣዳዲስ የኣሜሪካ ፓተንቶች ለሌሎች ተሰጥተዋል።

የእዚሁ (Ethiopic Character Entry) የባለቤትነት መታወቂያ ቍጥሩ ET/P/2009/111 የሆነ ከኢትዮጵያ ለዶክተር ኣበራ ሞላ እንደሚሰጥ ጥቅምት ፳፱ ቀን ፳፻፰ ዓ.ም. (September 9, 2015) ለጠበቃዎቻቸው ተጽፏል።

ግዕዝ ከዓለም ጥንታዊ ፊደላት ኣንዱ ሲሆን ኢትዮጵያውያን ከሺ ዘመናት በላይ ተጠቅመውበታል። የማተሚያ መሣሪያ ወደ ኢትዮጵያ በ፲፱፻፬ ዓ.ም. ገደማ እስከገባበት ድረስ ፊደሉ የሚከተበው በእጅ ጽሑፍ ብቻ ነበር። በኮምፕዩተር ቴክኖሎጂ መፈጠር የተነሳ ዶ/ር ኣበራ የግዕዝን ፊደል ለመጀመሪያ ጊዜ ኮምፕዩተራይዝ ሲያደርጉ እያንዳንዱ ቀለም በሁለት መርገጫዎች እንዲከተብ በ፲፱፻፹ ዓ.ም. ኣቅርበው በግዕዝ ፊደል በኮምፕዩተር መጠቀም በግዙፍ ተስፋፍቷል። ከእዚያም ወዲህ ብዛቱ ወደ ፭፻ የሚጠጋው የግዕዝ ቀለም እያንዳንዱ የእራሱ ቍጥር እንዲኖረው ለተቋቋመ ዩኒኮድ (Unicode) የሚባል ድርጅት ቀርቦ በዓለም ደረጃ ዕውቅና ኣግኝቷል። ትክክለኛዎቹና ሁሉም የግዕዝ ቀለሞች የዩኒኮድ መደብ ውስጥ እንዲገቡ ዶክተሩ ትልቅ ኣስተዋጽዖም ኣድርገዋል። http://www.ethiopianstories.com/component/content/article/55-science-a-technology/125-dr-abera-molla

ኣስቸጋሪ ሆኖ የቆየው ግን በኮምፕዩተር መርገጫዎች ቍጥር ማነስ የተነሳ ቀለሞቹን ከሁለት መርገጫዎች በኣነሰ በኮምፕዩተር የመክተብ ከባድነት ነበር። ይህ በእንዲህ እንዳለ እያንዳንዱ ቀለም በሁለት መርገጫዎች የሚከተቡበትን እናሻሽላለን ብለው ሌሎች ከኣቀረቧቸው ዘዴዎች መካከል በማውስ ቀስት መልቀም፣ ኣንዳንዶቹን ቀለሞች ከሦስት እስከ ስምንት መርገጫዎችን በመጠቀም ለመክተብ መዘጋጀት፣ ባዶ ስፍራ ቃል መካከል መጨመር፣ የግዕዝን ፊደል በላቲን ፊደል ኣጻጻፍ ለመክተብ እስፔሊንግ መማር፣ የማይጽፏቸው ቃላት መኖርና ፊደል መቀነስ ይገኙበታል። ኣዲሱ ፈጠራ ኢትዮጵያውያንን ከእነዚህ ችግሮችና በኣድልዎ ከመከፋፈልና መዳከምም ኣላቋል። በፓተንት ማመልከቻው እንደተጠቀሰው የፈጠራው ኣስፈላጊነት ግዕዝን በቀላሉና በቀለጠፈ ዘዴ መክተብ የሚያስችል ዘዴ ስለኣልነበረ ነው። የዓማርኛ ቀለሞችን በብዙ መርገጫዎች መክተብ የተጀመረው እንግሊዝኛ ለቃላቱ የሚጠቀምበትን የእስፔሊንግ ዘዴ ለዓማርኛ ፊደል መክተቢያ እንዲሆን ኣንዳንዶቹ ስለፈለጉና ስለኣልተሳካም ነው። እንግሊዝኛ ቃላትን እንጂ ቀለሞቹን በእስፔሊንግ ኣይከትብም። ግዕዝ ድምጻዊ ፊደል ስለሆነና እንደ እንግሊዝኛው ዓይነት የእስፔሊንግ ችግር ስለሌለው ተገልጋዩ ኣሠራሩን በግሉ ተምሮ መጠቀም ይችላል። ፈጠራው ቀላልና ትክክለኛ ስለሆነ መረዳት ከኣለማስቸገሩም ሌላ ዓማርኛ በብዛት የሚጠቀምባቸው ሳድሳን ቀለማት የሚከተቡት በኣንድ መርገጫ ነው። በእዚህ ኣዲስ የፈጠራ ግኝት የተነሳ ኣንድን ኃሳብ በዓማርኛ ወይም ሌሎች የግዕዝ ፊደል ተጠቃሚ ቋንቋዎች በቀላሉ ማቅረብ ተችሏል። ምክንያቱም የኣብሻ ሥርዓት ኮምፕዩተር ለእንግሊዝኛ ቀለሞች ከሰጠው ኃይል የበለጠና የረቀቀ በመሆኑ ግዕዝ ኣዲስ ኃይል ስለኣገኘ ነው። የመርገጫዎቹ ቁልፎች ኣመዳደብ የተመረኰዘው የእንግሊዝኛው ላይ ስለሆነ የግዕዝ ተጠቃሚው ኣከታተብ በቀላሉ በመማር ከኣንድ ገበታ መክተብ ይችላል። ግዕዙን በኣንድና ሁለት መርገጫዎች በግዕዝ ፊደል የመክተብ ኣስፈላጊነት የግዕዝና ላቲን ኣከታተቦች ግንኙነት ስለሌላቸው ነው። ስለዚህ ማንኛውንም የግዕዝ ቀለም በሦስት መርገጫዎች መክተብ ጊዜና ጉልበት ማባከን ነው። የተሳሳቱ ኣከታተቦችና ቀለሞች መጠቀም ተለምደው መቸገርና ማስቸገርንም ያስቀራል። የግዕዝና የላቲን ፊደሎችን ቀላቅሎ መሥራትና መፈለግ ይቻላል። የእንግሊዝኛው የጽሕፈት መሣሪያና ኮምፕዩተር ብዙ ፓተንቶች ሲኖሩት ይህ ፓተንት ለግዕዝ ፊደል የመጀመሪያው ነው።

በግዕዝ ፊደል በእየራሳቸውና በሚጋሯቸው ቀለሞች ከሚከተቡ ቋንቋዎች መካከል ቢለን፣ ቤንች፣ ሙርሲ፣ ምኢን፣ ሱሪ፣ ቅማንት፣ ቋራ፣ ትግረ፣ ትግርኛ፣ ዲዚ፣ ዳውሮ፣ ጉሙዝ፣ ጉራጌ፣ ጋሞ ጎፋ፣ ግዕዝ፣ ካይላ፣ ኩንፈል፣ ኣውንጂ፣ ኦሮሚፋ፣ ዓማርኛ እና ጫምታንግ ይገኙበታል። ዶ/ር ኣበራ ለግዕዝ ፊደል ፈር-ቀዳጅ ተመራማሪ ብቻ ሳይሆኑ ለግዕዝ ኣስፈላጊ ናቸው ብለው ከሠሯቸው ኣዳዲስ ቀለሞች መካከል የግዕዝ ኣልቦ፣ ብር፣ ሣንቲም፣ መብት፣ ንግድ፣ የተመዝግቧል፣ ማጥበቂያና ሌሎች ምልክቶች ኣሉ። የኮምፕዩተሩን የላቲን ምልክቶች ለግዕዝ ጥቅም ኣውለውና ከተዘርዘሩት ቋንቋዎች ቀለሞች ጥቅም ኣልፈው መርገጫዎቹ ተርፈዋል። የዶክተሩ የግዕዝ ፊደል ተመጣጣኝ የሆነ የእራሱ የእንግሊዝኛ ፊደልን ያካትታል።

ፓተንት እየተጠበቀ ነው በሚል ማስጠንቀቂያ ኩባንያው ከግዕዝኤዲት ዶት ኮም (http://www.geezedit.com) ድረገጽ ግዕዝኤዲት ክፍል ሁለትን ለጥቂት ዓመታት ለገበያ ሲያቀርብ ቆይቷል። ኢንተርኔት ላይ ነፃ የዓማርኛ መክተቢያ ከ፳፻፬ ዓ.ም. ጀምሮ ለዊንዶውስና ማክ ኮምፕዩተሮች ኣቅርቧል። (http://freetyping.geezedit.com) በ፳፻፮ ዓ.ም. ኣፕል የኣይኦኤስ 8 ሥርዓቱን በመክፈት ሌሎች መክተቢያዎቻቸውንና ፊደሎቻቸውን እንዲያስገቡ ስለፈቀደ ኩባንያው የግዕዝኤዲትን (GeezEdit App) ቁስ (ኣፕ) ለኣይፎን 6 እና ኣይፓድ ኣቅርቧል። የኣይፎን 4ኤስ እና 5 ሥርዓት ወደ ኣይኦኤስ 8 ከተሻሻለ በግዕዝኤዲት ቁስ መሥራት ይቻላል። ቁሱ የዓማርኛ ቀለሞችን በኣንድና ሁለት መርገጫዎች እንደሚከትበው ዓይነት የሌሎች ቋንቋዎች መክተቢያዎችም ወደፊት ይከፈታሉ። ነፃው ግዕዝኤዲት፣ ለዊንዶውስ የሚሸጠውና ግዕዝኤዲት ቁስ ሦስቱም የሚከተቡት በፓተንትና እየተጠበቁ በኣሉ ፓተንቶች በተጠበቁ የኣከታተብ ዘዴዎች ነው። ቁሱ ከሚያስከትብባቸው ፕሮግራሞች መካከል ቴክስት፣ ኢ.ሜይል፣ ሜሴጅስ፣ ፌስቡክ፣ ትዊተር፣ ኖትስ፣ ማይክሮሶፍት ወርድ፣ ኦፊስ ስዊት፣ ፔጅስ፣ ጉግል፣ ያሁ ፣ ቢንግ፣ ዊኪፒዲያና ኋትስኣፕ ይገኙበታል። የዓማርኛው ቁስ ኣጠቃቀሙን ከእንግሊዝኛው ሥርዓት ጋር ስለሚጋራ በሁለቱም ፊደላት መሥራት ያስችላል። የእስማርት (ረቂቅ) ስልኩ በዓማርኛ ቋንቋ እንዲሠራ መምረጥ ይቻላል። ዓማርኛ ኣብዛኛው ሕዝብ የሚጠቀምበት የኢትዮጵያ ፊደል ሲሆን ፈጠራው የኣናሳ ቋንቋዎች ቀለሞች በብዙ መርገጫዎች እንዲከተቡ የሚደረገውን ግፊትና ፊደል ስለበዛ መጻፍ እንዳያስቸግሩ ይቀነሱ የሚባለውን ኣስተሳሰብ ሊያስቀር ይችላል። የግዕዝኤዲት ቁስ እዚህ ይገኛል፦ https://itunes.apple.com/us/app/geezedit/id935624754?mt=8
ግዕዝ ድምጻዊ ፊደል ስለሆነ ኣንድን ኃሳብ በጥቂት ቀለማትና ስፍራ በጥራት የማቅረብ ችሎታ ሲኖረው ፈጠራው ተጨማሪ ኃይል ሰጥቶታል። ለምሳሌ ያህል በፈጠራው ጥቅም የተነሳ በዓማርኛ “ዘ ኲክ ብራውን ፎክስ ጀምፕስ ኦቨር ዘ ሌይዚ ዶግ።” የሚለውን በእንግሊዝኛ “The quick brown fox jumps over the lazy dog.” እንደሚጻፈው ሁለት ገበታዎች ኣያስፈልጉትም። እንዲሁም “ሐመር ኋይት ሃውስ ሦስት ቋንቋ ትዕግሥት ጨካኝ” ምሳሌ 23 የዓማርኛ ቀለሞች በኣብሻ ሥርዓት የሚከተቡት በ32 እስከ 34 መርገጫዎች ሲሆን እንደ ሌሎቹ ከ50 በላይ የዓማርኛ መርገጫዎችን መጠቀም ኣያስፈልግም። በተጨማሪም የዓማርኛውን ኃምስ “ጬ” በኣራትና ኣምስት መርገጫዎች መክተብ የጉራጌኛ ወይም የጉሙዝ “ጬ”ዎች በእንግሊዝኛ እስፔሊንግ መክተብ እስከ ሰባትና ስምንት መርገጫዎችን መጠቀም ስለሚያስከትል የኣናሳ ቋንቋዎች ተጠቃሚዎች እንዳይቀየሙ ፈጠራው ይራዳል። ምክንያቱም በፈጠራው የተነሳ ማንኛውንም የግዕዝ ቀለም በኣንድና ሁለት መርገጫዎች መክተብ ስለተቻለ ነው።

በላቲን ኣከታተብ ሥርዓት 26ቱ መርገጫዎች የተመደቡት ለእያንዳንዱ ቀለም ሲሆን ለ37ቱ የግዕዝ ቀለሞችም ዶክተሩ ግዕዝን ዲጂታይዝ (Digitize) ሲያደርጉ ለእያንዳንዱ ቁልፍ ተመድቦላቸዋል። ግዕዝ በላቲን 26 መርገጫዎች ካልተጻፈ ብለው ጥቂቶቹ የቁልፍ እጥረት ከፈጠሩ በኋላ ይኸንኑ ችግር የዝቅ (ሺፍት) ገበታ ላይ በመድገም ግዕዝ የማያውቀውን የእስፔሊንግ ችግር መፍጠር የሚፈልጉም ኣሉ። ግዕዝ ኮምፕዩተራይዝ ሲደረግ ፓተንቱ ኣሁንም ስለኣልተሰጠ የተለያዩ መክተቢያዎች ቀርበው ሕዝቡ ሲበሳጭ የነበረውን ኣዲሶቹ ፓተንቶች እንዲያስቀሩ ማስተዋልና መጠንቀቅ ኣስፈላጊዎች ናቸው። የፓተንቶቹ መኖር ኢትዮጵያውያን ኣዳዲስ የግዕዝ ቴክኖሎጅዎችን ፈጥረው እንዲገነቡቧቸውና ፓተንቶች እንዲያገኙ የሚረዱ የጥበቡ መጀመሪያ መሠረቶች ናቸው። ይኸን ተረድቶና መከተል ከትውልዱ ይጠበቃል።

ዶክተሩ ግዕዝ በኮምፕዩተር እንዲሠራ ሲፈጥሩ ሁለት መርገጫዎችን በመጠቀም መክተብ የሚቻለው ስድስት ቀለሞችን ብቻ ሲሆን ኣዲሱ ፈጠራ ይኸንኑ ወደ 14 ቀለሞች ከፍ ኣድርጎታል። ስለዚህ ቃላት ይመስል የግዕዝ ቀለሞችን በእንግሊዝኛ ፊደል እስፔሊንግ መክተብ ወይም የእንግሊዝኛ ኣክሰንቶች እንደሚከተቡት መንፏቀቅ ኣያስፈልግም። ምክንያቱም የዝቅ መርገጫን መጠቀም ሳያስፈልግ ሁሉንም የግዕዝ ቀለሞች ከኣንድ ሰሌዳ ብቻ መጠቀም ስለተቻለ የምሁራን የፓተንትን ጥቅም ማወቅና ማሳወቅ የእራሳቸውንና የኣገሪቱን መብቶች ለመጠበቅ ስለሚራዳ ነው። ዶክተሩ በምርምራቸው በመራቀቅ ኣዳዲስ ፈጠራዎቻቸውን በማቅረቡ ቀጥለውበታል።

http://patents.justia.com/patent/20150212592
የዶክተሩ ሙያ እንስሳት ሕክምና ሲሆን በመስኩም ትላልቅ ኣስተዋጽዖዎች ከማድረግ ሌላ ፓተንቶችም ኣሏቸው። ለተጨማሪ መረጃ ኢ.ሜይሉGeezedit@aol.com ነው።

No comments:

Post a Comment

wanted officials