ከወያኔ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ስልጠናዎች የተረዳነው:- ወጣቱ ለለውጥ ዝግጁ ነው፤ የቀረው ድርጅት ነው
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተመሠረቱበት ዓላማ የእውቀትና ጥበብ መበልፀጊያና ማስፋፊያ እና የምርምር ማዕከላት እንዲሆኑ ነው። እውቀትና ጥበብ እንዲበለፅጉ እና የምርምር ሥራዎች እንዲዳብሩ የአካዳሚ ነፃነት መኖሩ ቁልፍ ጉዳይ ነው። የአካዳሚ ነፃነት ሳይኖር መምህራኑም ተማሪዎቹም በነፃነት ማሰብ፣ አስቸጋሪ ጥያቄዎችን ማንሳት እና ለጥያቄዎቻቸው መልስ ለመሻት መመራመር አይችሉም። የአካዳሚ ነፃነት ሳይኖር የተለያዩ እይታዎችንና ንድፈሀሳቦችን በገለልተኛነትና በሀቀኝነት መመርመር አይቻልም። በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የአካዳሚ ነፃነት እንዲኖር ተቋማቱ ከፓርቲ ፓለቲካ ገለልተኛ መሆን ይኖርባቸዋል። አንድ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም የአንድ ፓርቲ ርዕዮተ ዓለም አራማጅ ከሆነ ተቋሙ የፓርቲው ካድሬዎች ማሰልጠኛ ሆነ ማለት ነው። ዛሬ በአገራችን የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገኙበት ሁኔታ ይህ ነው። የአገራችን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የወያኔ ካድሬዎች ማሰልጠኛ ሆነዋል። ይህ አጅግ አሳሳቢ ጉዳይ ነው።
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ወደ ህወሓት ካድሬ ማሰልጠኛነት መዝቀጥ አንድ ተጨባጭ ማስረጃ ሰሞኑን ለዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በፕላዝማ ቴሌቪዥን አማካይነት በመሰጠት ላይ ያለው ፕሮፖጋንዳ ነው። በዚህ ፕሮፖጋንዳ ያልተጠመቀ ተማሪ የሚቀጥለው ዓመት መደበኛ ትምህርት አይቀጥልም በማለት ተቋማቱ ለካድሬ ማሰልጠኛነታቸው እውቅና ሰጥተዋል።
በዚህ ብዙ የአገር ሀብትና ጊዜ በፈሰሰበት ቅስቀሳ፣ የወያኔ ካድሬዎች ዘረኛና ከፋፋይ ፓሊሲዎቻቸውን ማር ቀብተው ወጣቱን ለመጋት እየጣሩ ነው። ለፓርቲ ቅስቀሳ የመንግሥትን መዋቅር መጠቀም በራሱ ወንጀል ቢሆንም ከዚህ በላይ ጉዳት ያለው ደግሞ የፕሮፖጋንዳው ይዘትና ዓላማ ነው። ወያኔ/ኢሕአዴግ ሁሉንም ነገር የሚያውቅ፤ ሁሉንም ነገር ማድረግ የሚችል ተደርጎ የተዘጋጀው ፕሮፖጋንዳ በትውልድ ላይ የሚያስከትለው የእውቀትና የሥነ ልቦና ኪሳራ ከፍተኛ ነው።
በዚህ “ስልጠና” ተብሎ በሚሞካሸው ርካሽ ፕሮፖጋንዳ አማካይነት አድርባይ የሆነው ወያኔ ወጣቱን ለአድርባይነት እያዘጋጀው ነው። የወያኔ ዓላማ የኢትዮጵያ ወጣት መስሎና ዋሽቶ አዳሪ እንዲሆን ማድረግ ነው። የስልጠናው ዓላማ ወጣቶች ለግል ሕወታቸው ምቾች ሲሉ የወያኔ አባላትና ደጋፊዎች እንዲሆኑ ማድረግ ነው። የስልጠናው ዓላማ “ወይን ለኑሮ” ተቀባይነት ያለው የኑሮ ዘይቤ ለማድረግ ነው። ይህ ደግሞ የከፍተኛ ትምህርትን መሠረተ ሀሳብን ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያዊነት ነፃነት-ወዳድ ባህልንም የሚፃረር ነው። በዚህም ምክንያት ወያኔ የወጣቱን ትውልድ ላይ አዕምሮ ለማላሸቅ የሚነዛውን ፕሮፖጋዳ መቃወም የኢትዮጵያዊያን ሁሉ የዜግነት ግዴታ ነው።
ደግነቱ በአብዛኛዎቹ የስልጠና አዳራሾች እየሆነ ያለው ወያኔ ያሰበውና የተመኘውን አይደለም። የኢትዮጵያ ወጣት የወያኔን ዘረኛ ፕሮፖጋንዳ የሚጋት እንዳልሆነ እያስመሰከረ ነው። በብዙ አዳራሾች የወያኔ ካድሬዎች ሊመልሷቸው ከማይችሏቸው ጥያቄዎች ጋር ተፋጠው እንዲያፍሩ ተደርገዋል። ወጣቶች፣ “የታለ የምታወሩለት እድገት ?” “ቻይና በሠራው እናንተ የምትፎክሩት ለምንድነው?“ “ፍትህ የት አለ?” “የአንድ ብሔር የበላይነትን ነው እኩልነት የምትሉት?” እያለ ካድሬዎችን እያፋጠጠ ነው። ወጣቱ አፈና በበዛበት ሁኔታ ውስጥም ሆኖ መሠረታዊ የሆኑ ጥያቄዎችን ለማንሳት መድፈሩ፤ በአንዳንድ አዳራሾች ደግሞ በጩኸት የፕሮፖጋንዳውን ሥራ ማወኩ ወጣቱን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያዊያንን ሁሉ የሚያኮራ ተግባር ነው።
ወያኔ፣ ወጣቱን አድርባይነትን ለማስተማር ያዘጋጀው ስልጠና የወጣቱ ቆራጥነትና አርበኝነት ማሳያ ሲሆን፤ ፍርሃት ለማስፈን የተጠራ ስብሰባ ድፍረትን አደባባይ ሲያወጣ ማየት የሚያኮራ ነው። ወጣቱ በዚህ ስልጠና ላይ ባሳየው ድፍረት ለለውጥ ምን ያህል ዝግጁ እንደሆነ አሳይቷል። አሁን የጎደለው ድርጅት ነው። የወጣቱ ለለውጥ ዝግጁ መሆን አንድ ትልቅ የምሥራች ነው። ይህ ዝግጁነት በድርጅት መደገፍ ደግሞ ተከታትሎ መምጣት ያለበት ሥራ ነው። የወጣቱ የመንፈስ ዝግጅትና ድርጅት ከተቀናጁ የወያኔ ውድቀት ቅርብ ነው።
ወጣቱ ከተቃውሞ ባለፈ ሊሠራቸው የሚገቡ በርካታ ጉዳዮች ከፊቱ ተደቅነዋል። ከሁሉ አስቀድሞ ድርጅት ወሳኝ ጉዳይ እንደሆነ ሊጤን ይገባዋል። ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ በወያኔ አገዛዝ ሥር ባለችው ኢትዮጵያ ውስጥ ምስጢራዊና ማዕከላዊነትን ያልጠበቁ ትናንሽ ስብስቦች ይበልጥ ውጤታማ ይሆናሉ ብሎ ያምናል። ስለሆነም ግንቦት 7፣ እያንዳንዱ ለሀገሩ፣ ለነፃነቱ፣ ለክብሩ፣ ለፍትህ ግድ ያለው ወጣት ከሚመስሉትና ከሚያምናቸው ጥቂት ወዳጆቹ ጋር በምስጢር እንዲደራጅ አጥብቆ ይመክራል። የተደራጁ ስብስቦች ግንቦት 7ን ማግኘት ወይም ግንቦት 7 እነዚህን ስብስቦች ማግኘት አስቸጋሪ አይሆንም። የኢትዮጵያ ወጣት ለለውጥ ዝግጁ ነው። የጎደለው ድርጅት ነው። የጎደለውን ማሟላት ደግሞ የሁላችንም ግዴታ ነው።
ግንቦት 7:የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ፣ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች በወያኔ ስልጠናዎች ላይ ተቃውሞ ለማሰማት በመድፈራቸው የተሰማውን ደስታ ይገልፃል። ይህ ክስተት ወጣቱ ለለውጥ የተዘጋጀ እንደሆነ በአመላካችነት ወስዶታል። ይህ የለውጥ ፍላጎት በድርጅት ካልታገዘ ውጤት ስለማያመጣ ወጣቱ በትናንሽ ሕዋሶች ራሱን እንዲያደራጅ ይመክራል። ይህንን ካደረግን የወያኔ ፋሺስታዊ አገዛዝን የምናስወግድበት ጊዜ ሩቅ አይሆንም።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!
No comments:
Post a Comment