Which one you first choose? በቅድሚያ የሚፈልጉት

Wednesday, August 27, 2014

ሱዳን ከኢትዮጵያ የምትገዛውን የኤሌክትሪክ ኃይል ለኤርትራ ለመሸጥ መዘጋጀቷ ተሰማ

ሱዳን ከኢትዮጵያ የምትገዛውን የኤሌክትሪክ ኃይል ለኤርትራ ለመሸጥ መዘጋጀቷ ተሰማ

ኢትዮጵያ በተዘዋዋሪ መሸጡ አያሳስበኝም አለች
የሱዳን መንግሥት ከኢትዮጵያ ለመግዛት ከተስማማው አንድ መቶ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ውስጥ መጠኑ ይፋ ያልተደረገ ኃይል ለኤርትራ ለመሸጥ ዝግጅት ላይ መሆኑ ተሰማ፡፡
የሱዳን የኤሌክትሪክ ኃይል ማሰራጫ ኩባንያን ዋቢ ያደረገው ኢነርጂ ቢዝነስ ሪቪው ድረ ገጽ ባስነበበው ዘገባ መሠረት፣ በምሥራቃዊ ሱዳን በኩል ከከሰላ ግዛት ተነስቶ ወደ ኤርትራ የሚዘረጋ የ45 ኪሎ ሜትር የኤሌክትሪክ ኃይል ማስተላለፊያ መስመር መዘርጋት ተጀምሯል፡፡
ከሁለት ዓመት በኋላ ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቀው የህዳሴው ግድብ የኃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ጂቡቲ፣ ኬንያ፣ ሶማሊያ፣ ግብፅና አሁን ደግሞ ኤርትራ ተጠቃሚ ይሆኑበታል ተብሎ ስድስት ሺሕ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲያመነጭ በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡ ባለፈው ዓመት ሱዳንና ኢትዮጵያ የድንበር ተሻጋሪ ኃይል ማሰራጫ መስመርን በጋራ ማስመረቃቸው የሚታወስ ነው፡፡
ሱዳን ወደ ኤርትራ ልትሸጥ ዝግጅት መጀመሯን በማስመልከት ሪፖርተር ያነጋገራቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ፣ የኃይል ሽያጭ ስምምነቱ በኢትዮጵያና በሱዳን መካከል የተደረገ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡ ‹‹ይህም ሆኖ ሱዳን ከኢትዮጵያ የገዛችውን የኤሌክትሪክ ኃይል ለማን እንደምታስተላልፍና ከማን ጋር እንደምትነግድ ለመቆጣጠር አንችልም፣ ሉዓላዊነቷም አይፈቅድልንም፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡
‹‹ሱዳን ከማን ጋር እንደምትነግድ በሉዓላዊነቷ ላይ ማዘዝ አንችልም፤›› ያሉት አምባሳደር ዲና፣ ሱዳን ከኢትዮጵያ የገዛችውን ኤሌክትሪክ ኃይል በተዘዋዋሪ መንገድ ለኤርትራ መሸጧ ላይ ችግር የለውም ብለዋል፡፡ ‹‹የምንፈልገው የአካባቢው አገሮች ሀብቱን ተጠቅመው በሰላም መጎራበታቸውን ነው፤›› ከማለታቸውም ባሻገር፣ የኤሌክትሪክ ኃይል ብቻም ሳይሆን ሌላውም የኢትዮጵያ ምርት ከኤርትራ ባሻገር ለማንኛውም አገር ቢቀርብ፣ ኢትዮጵያ ችግር እንደሌለባት አስታውቀዋል፡፡
በቅርቡ ለኤርትራ ቴሌቪዥን የተናገሩት ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ኢትዮጵያ ከህዳሴው ግድብ ከምታመነጨው የኤሌክትሪክ ኃይል የመግዛት ዕቅድ እንዳላቸው አስታውቀው ነበር፡፡ ፕሬዚዳንቱ የኤርትራ አውሮፕላን ማረፊያን ጨምሮ ትልልቅ የመንግሥት ተቋማት በኃይል አቅርቦት እጥረት ሳቢያ በአግባቡ አገልግሎት መስጠት እንደተሳናቸውና ኃይል ከኢትዮጵያ ለመግዛት መታቀዱን ተናግረዋል፡፡ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ ይህንን ከተናገሩ ከጥቂት ጊዜ ቆይታ በኋላ ኤርትራ በሱዳን በኩል ኃይል ለመግዛት መዘጋጀቷ ግን የፕሬዚዳንቱን መግለጫ ግራ የሚያጋባ አድርጎታል፡፡ በሱዳን አማካይነት ኤርትራ የኤሌክትሪክ ኃይል ልትገዛ ነው የሚለው መረጃ መረጋገጥ አለበት በማለት አምባሳር ዲና ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ሱዳን ከኢትዮጵያ ለምትገዛው ኃይል በኪሎ ዋት አወር 0.6 ዶላር እንደምትከፍል ይጠበቃል፡፡ በዚህ አነስተኛ መጠን ገዝታ ለኤርትራ በምን ያህል ዋጋ ልትሸጥ እንደምትችልና ምን ያህል ሜዋ ጋት ኃይል እንደምታቀርብላት ለማወቅ አልተቻለም፡፡

No comments:

Post a Comment

wanted officials