ለነዋሪዎች አማራጭ የለም!
“ከተማዋ የሕዝብ መጸዳጃ ቤት ሆናለች”
በአዲስ አበባ ያለው የመጸዳጃ ቤት ችግር ከልክ ያለፈና መሆኑን የእንግሊዙ ዘ ጋርዲያን ጋዜጣ ዘገበ። ሐሙስ በወጣው የጋዜጣው ድረገጽ ላይ እንዳስነበበው ከ3 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ በሚኖርባት አዲስ አበባ ውስጥ ለሕዝብ መገልገያነት የዋሉት መጸዳጃ ቤቶች 63 ብቻ መሆናቸውን ዘግቧል። አማራጭ ያጡ የከተማዋ ነዋሪዎች ደግሞ ከተማዋ ወደ መጸዳጃ ቤትነት እየተለወጠች መሆኗን በምሬት ገልጸዋል።
ጋርዲያን “Wash Ethiopia Movement” የተባለ አገር በቀል ድርጅት ጠቅሶ እንደዘገበው በከተማዋ ከ10 ቤተሰቦች 9ኙ የጉድጓድ መጸዳጃ ቤት እንደሚጠቀሙና መቀመጫ ባለው መጸዳጃ ቤት የሚጠቀሙት ከ25 ቤተሰቦች አንዱ ብቻ መሆኑን ተናግሯል። በዘገባው መሠረት የከተማዋ ባለሥልጣናት የዛሬ ዓመት ይገነባሉ በሚል የ100ሚሊዮን ብር ዕቅድ የተያዘላቸው መጸዳጃ ቤቶች እንዳሉ መናገራቸውን ጠቅሷል።
በተመሳሳይ ሁኔታ 1ሺህ መጸዳጃ ቤቶችን ለመገንባት የዛሬ ዓመት ተይዞ የነበረ ዕቅድ እስካሁን ተግባራዊ እንዳልሆነ ጋዜጣው የመንግሥት ባለሥልጣንን ጠቅሶ ሲጽፍ ወደፊት መጸዳጃ ቤቶቹ እስኪሰሩ ድረስ በመንገድና ፎቅ “እየተዋበች” ያለችው ከተማ ነዋሪ የት ሄዶ ሊጸዳዳ እንደሚችል ባለሥልጣኑ ስለመናገራቸው የጠቆመው የለም። ይህ የመጸዳጃ ችግር “በአምስቱ ዓመት የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ባለራዕያዊ ዕቅድ” ውስጥ ስለመካተቱ ከገዢው “አውራ ፓርቲ” ባለሥልጣናት የተነገረ ነገር ስለመኖሩ የተገለጸ ነገር የለም። የአዲስ አበባ የመጸዳጃ ቤት ጉዳይና ሽታ አምስት ከንቲባዎችና ሁለት ጠቅላይ ሚኒስትሮች ተፈራርቀውበታል።
ጋዜጣው በቀን 200 ሰዎች ስለሚጠቀሙባቸው 4 መጸዳጃ ቤቶች ሲዘግብ “ለመጠቀም አስቸጋሪ፣ ለሴቶች የማይመቹ፣ ንጽህናቸው ያልተጠበቀና ጠረናቸው እጅግ የሚሰነፍጥ” መሆኑን አስረድቷል። የመጸዳጃ ቤቶቹ ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል ወ/ሮ ብርሃኔ በመጸዳጃ ቤቶቹ ንጽህና ጉድለት ምክንያት ከጥቂት ወራት በፊት በጠና ታምመው ሆስፒታል መግባታቸውን ገልጸዋል። በርካታ ያካባቢው ነዋሪዎችም በተስቦ፣ በተቅማጥና በሌሎች ተላላፊ በሽታዎች እንደሚጠቁ ተናግረዋል። መጸዳጃ ቤቶቹ የወንድና የሴት ተብለው ካለመከፋፈላቸው በተጨማሪ በተለይ ለሴቶች የሚመቹ ባለመሆናቸው አንዳንድ ሴቶች በፖፖ ቤታቸው እየተጠቀሙ ወደ መጸዳጃ ቤቶቹ እያመጡ እንደሚደፉ በግልጽ አስረድተዋል።
ሌላው አየካባቢው ነዋሪ የሆኑት አቶ ግርማ ታደሰ ማኅበረሰባቸው ለቁሻሻ ፍሳሽ ማስወገጃ በወር ሁለት ጊዜ ያህል 1200 ብር እንደሚከፍሉ ገልጸው ይህም ሆኖ ግን መጸዳጃ ቤቶቹ “በተለይ ለልጆች ጤናም ሆነ ንጽህና የማይመቹ” መሆናቸውን በመግለጽ መጸዳጃ ቤቶቹ በቶሎ ስለሚሞሉ ከዚያ በሚወጣው ጠረንና ፍሳሽ ምክንያት በርካታ ሰዎች እንደሚታመሙ ተናግረዋል። የሁለት ዓመት ልጃቸውን ብሌን ግርማ በእጃቸው እንደያዙ አስተያየታቸውን የሰጡት አቶ ግርማ “ልጄ እነዚህ መጸዳጃ ቤቶች ውስጥ እንድትጠቀም አልፈልግም፤ ስለኑሯችን ሳስብ በጣም አዝናለሁ፤ ግን ምርጫ የለንም” ብለዋል።
በ2006ዓም ታህሳስ 2ቀን “መፀዳጃ ቤት አልባዋ አዲስ አበባ” በሚል ርዕስ በወጣው የአዲስ አድማስ ጦማር ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት ገዳም ሰፈር ተወልደው ያደጉት የ62ዓመት አዛውንቱ አቶ አሰፋ ታዬ ናቸው። መጸዳጃ ቤትን በተመለከተ የእርሳቸውን ዘመን ካሁኑ ጋር በማነጻጸር አቶ አሰፋ ሲናገሩ እንዲህ ብለው ነበር፡-
“ያኔ እንዲህ እንደዛሬው ቅጥ አንባሩ የጠፋበት ዘመን አልነበረም። ያኔ እንዲህ እንደአሁኑ በቤተክርስቲያን ደጃፍ እንደልብ መፀዳዳት ፈጽሞ የማይታሰብ ነገር ነበር። በየጥጋጥጉና በየሜዳው የሚፀዳዱ ሰዎችን ይዘው የሚያስቀጡ ደመወዝተኛ የሚባሉ ሰዎች ነበሩ። ህብረተሰቡም እራሱ ፈሪሃ እግዚአሃብሔር ያደረበት፣ ሜዳ ላይ መፀዳዳት የሚያሳፍረውና እርስበርሱ የሚከባበር ስለነበር ከተማዋ እንዲህ እንደዛሬው የህዝብ መፀዳጃ ቤት አትመስልም።
“አሁን አሁንማ አፍንጫው ሥር ሲፀዳዳ እፍረት የማይሰማውን የከተማ ነዋሪ ማዘጋጃ ቤቱ የሚያበረታታውና አይዞህ የሚለው ይመስላል። ማዘጋጃ ቤቱ እንኳንስ የከተማዋን ጽዳትና ውበት ሊጠብቅና ሊቆጣጠር ቀርቶ የራሱን ደጃፍ ከህዝብ መፀዳጃ ቦታነት ሊከለክልና ሊያስጥል አልቻለም። አላሙዲን የልጆቻችን ኳስ መጫወቻ የነበረውን ሰፊ ሜዳ ወስደው ሲያጥሩ እንዴት ያለ ሆቴልና መዝናኛ ቦታ ሠርተው አካባቢውን ሊያሣምሩልን ነው። ተመስገን አይናችን ጥሩ ነገር ሊያይ ነው ብለን ተደስተን ነበር። ምን ዋጋ አለው። ይኸው ሃያ ዓመት ሙሉ በአጥር ተከልሎ የመፀዳጃና የመዳሪያ ቦታ ሆኗል።
“እኔ የሚገርመኝ ማዘጋጃ ቤቱ እዚሁ ዓይኑ ሥር ያለውን የሠገራ ክምር ማጽዳት አቅቶት፣ የከተማ ጽዳት፣ የአካባቢ ጽዳት እያለ መለፍለፉ ነው።
“የድሮዎቹ ደመወዝተኞች የአካባቢውን ንጽህና ለመጠበቅና ህብረተሰቡ በተገቢው ቦታ መፀዳዳት እንዳለበት በማስተማሩ ረገድ ሰፊ ሥራን ይሰሩ ነበር። የዛሬዎቹ ደንብ አስከባሪዎች ግን ከሱቅ በደረቴዎች ጋር ሌባና ፖሊስ ሲጫወቱ ነው የሚውሉት። ‘መሽናት ክልክል ነው’ ብሎ በመፃፍና በመለጠፍ ብቻ ምንም ለውጥ ማምጣት አይቻልም። የግንዛቤ ለውጥ ለማምጣት መስራት አለበት። እንደውም እኮ ሰው የሚፀዳዳው “መሽናት ክልክል ነው” የሚሉ ጽሑፎች በተለጠፋባቸው ቦታዎች ላይ ነው።
“እናም ባለስልጣናቱ በዚህ ጉዳይ ላይ ቢያስቡበት ጥሩ ነው። ፎቅና መንገድ መሥራት ብቻ አንድን ከተማ ሊያሣድጋት አይችልም። ንጽህናዋምወሳኝ ነው። የከተማዋ አስተዳደር በዚህ ጉዳይ ላይ ትኩረት ሰጥቶ ካልሰራ በስተቀር አሁን እንዲህ ከፍተኛ ወጪ እየወጣበት የሚሰራውና ብዙየተባለለት አዲሱ የባቡር ሐዲድ መፀዳጃ ላለመሆኑ ማረጋገጫ የለንም።”
አዲስ አድማስ በወቅቱ ባሰፈረው ዘገባ እንደ መፍትሔ የዶርዜ ሃይዞና የሸበዲኖ ወረዳ ነዋሪዎች ይህን ብሎ ነበር። “በእነዚህ ወረዳዎች እጅግ አሣፋሪው ተግባር ሜዳ ላይ መፀዳዳት ነው። እነዚህ ቦታዎች “ሜዳ ላይ ከመፀዳዳት የነፃ” (Open defecation Free) ተብለው በተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማት ሽልማት ተሰጥቷቸዋል። የአካባቢው ነዋሪዎች ሜዳ ላይ መፀዳዳት እጅግ አሣፋሪ ተግባር መሆኑን ያምናሉ። ይህንን አሣፋሪ ተግባር ላለመፈፀም በእጅጉ ይጠናቀቃሉ። ይህንን እምነታቸውን ጥሶ መንገድ ላይ የሚፀዳዳ ሲያዩ በዝምታ አያልፉትም። ነዋሪዎቹ እንዲህ አይነት “አደጋ” በአካባቢያቸው ሲፈፀም የሚጠራሩበት የራሣቸው የሆነ የኮድ መጠራሪያ ድምፅ አላቸው። ይህንን ጥሪ የሰማ የአካባቢው ነዋሪ ሁሉ ጥሪው ወደተደረገበት ቦታ በፍጥነት ይሄዳል። ሰውየው (ሴትየዋ) መፀዳዳታቸውን እስኪጨርሱ ድረስ ይጠብቁና ሠገራውን በፕላስቲክ ከረጢት ውስጥ እንዲከት ያስገድዱታል። በሠገራው ላይ የሰውየው ሙሉ ስም ይፃፍበትና በዋናው መንገድ ላይ ይንጠለጠላል። “የእከሌ ሰገራ ነው” የሚለውን ፅሁፍ የሚያነበው የአካባቢው ነዋሪ ህዝብ ለሰውየው የሚሰጠው ግምት እጅግ ያነሰና የወረደ ይሆናል። ይህም ድርጊቱን በፈፀመው ሰው ሞራልና ስብህዕና ላይ ከፍተኛ ውድቀትና በአካባቢው ነዋሪዎች ዘንድም መገለልን ያስከትልበታል። ማንም ሰው ይህ እንዳይደርስበት ሜዳ ላይ ከመፀዳዳት ይቆጠባል። አዲስ አበቤዎች ከዚህ ምን ይማሩ ይሆን?”
ጋርዲያን ያወጣውን ዜና በማስከተል አስተያየታቸውን በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ያሰፈሩት የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን) ዋና ዳይሬክተር አቶ ኦባንግ ሜቶ (Where is the ‘double-digit growth and rapid development the ethnic apartheid regime of the TPLF/EPRDF vouching about?) “አፓርታይዳዊ የዘር አገዛዝ የሚከተለው ህወሃት/ኢህአዴግ የድርብ አኻዝ ፈጣን ዕድገት አስመዝግቤአለሁ እያለ የሚለፍፈው የት ነው ያለው? እውነቱ በግልጽ ሊነገር ይገባል፤ በግልጽ መነጋገር አለብን፤ አለበለዚያ ያፈኑት ነገር ፈንድቶ ዓመጽና አለመረጋት ከዚያም አልፎ ጥቃት የታከለበት ሊሆን እንደሚችል” የማኅበራዊ ቀውሱ ሊያስከትል የሚችለውን ችግር ጠቁመዋል።
ለጎልጉል: የድረገጽ ጋዜጣ በፌስቡክ በኩል አስተያየት የሰጡ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች እንደገለጹት በተለይ በኮንዶሚኒየም የሚኖሩና ከመጀመሪያው ፎቅ በላይ ያሉ ነዋሪዎች በከተማዋ ካለው የውሃ ዕጥረት ጋር ተዳምሮ የመጸዳጃ ጉዳይ እጅግ አሳሳቢ እንደሆነባቸው ተናግረዋል። ውሃ በሚመጣበት ጊዜ እንኳን ኃይሉ ደካማ ስለሚሆን የመጸዳጃ ቤት ንጽህና ከፍተኛ ችግር እንደፈጠረባቸው ተናግረዋል። በዚህም ምክንያት በየአካባቢያቸው በሚገኙና በጋዜጣው ላይ እንደተጠቀሱት ዓይነት ንጽህናቸው ላልተጠበቀ የኅብረት መጸዳጃቤቶች አማራጭ ማድረጋቸውን አስረድተዋል። ከቤታቸው ይዘው የወጡትን በመስሪያ ቤቶቻቸው አጠናቀው የሚመጡና በራሳቸው መንገድ ለችግራቸው አማራጭ መፍትሔ የፈጠሩም ቁጥራቸው ጥቂት እንዳልሆነ ይነገራል።
No comments:
Post a Comment